Tidarfelagi.com

አራት ነጥብ (።)

አራት ነጥብ (።)

ከቤት ስወጣ የሰፈሬ ሰዎች ሁላ ከዚህ በፊት አይቼው በማላቅ አግድም ወንበር ላይ በብዛት ተደርድረው ፀሀይ ይሞቃሉ። ፊታቸው ላይ ደስታ ባራት እግሩ ቆሟል።

የወንበሩ ቁመት ከዚህ በፊት አይቼ የማላውቀው አይነት ነው። ምቾቱም ሳይቀመጡ የሚገምቱት ነው። አንድ ቀን ቁጭ ብዬበት ዘላለም ቆሜ ልኑር የሚያስብል ዓይነት…

ከሰፈራችን የቀረ ሰው ያለ አይመስልም። በግርምት ቆሜ እያየኋቸው ከጋሽ ዘውዱ ጋር ዓይን ለዐይን ተገጣጠምን።

“አገኝ፣ ና እንጂ ወዲህ? ” ጠጋ ብለው ካጠገባቸው እንድቀመጥ እየጋበዙኝ።

“የምን ወንበር ነው? ”

“የእርግጠኝነት ወንበር ይባላል። ምስጋና ይግባውና የመንደራችን የእጨት ስራ ባለሙያው አቶ በእምነቱ ሸጋ ዘድርጎ ነው የሰራልን፤ ያውልህ ወዲያ ቁጭ ብሏል።

… አየህ ልጄ የሰው ልጅ እርግጠኛ ካለመሆን የበለጠ እርግማን የለበትም። እርግጠኛነት ከህይወታቸው የጎደለች ሁሉ ዋታችነት ነው ትርፋቸው፣ እረፍት አታይባቸውም። እርካታ አታነብባቸውም። ከዚህ ሁሉ መገላገያው የእርግጠኛነት ወንበር ላይ እንዲህ ጋለል ማለት ነው። ” በፈገግታ እያዩኝ ጋለል አሉ

ዙሪያውን አየሁ። መቲን አየኋት። ገረመኝ። የምወዳት በምታነሳቸው ጥያቄዎች ነበር። ጥያቄዎቿን በቅርብ ለማግኘት አስቤ ነው መሰል ግንኙነት ጀመርን። ዛሬ ግን እዚህ የእርግጠኝነት ወንበር ላይ ተመቻችታ ተቀምጣለች።
መጠየቅ ደከማት?
“ና ወዲህ” በሚል አይን ታባብለኛለች። ፊቴነወ ከሷ መለስኩ።
ወላጆች ህፃናት ልጆቻቸውን ጭምር ታቅፈው ቁጭ ብለው።

“እርግጠኝነትን ከማጣት ስቃይ ልጆቻችንን መጠበቅ አለብን። ከስርዓተ ነጥብ ሁሉ ተለይታ አራት ነጥብ የተባረከች ናት። ያንን የተባረከ ነገር ነው የምንሰጣቸው” አሉኝ ጋሽ ዘውዱ፣ ወደ ልጆቹ ማየቴን አይተው።
አዘንኩ።

መቲ ከኋላ ትጠራኛለች። ከዚህ ሰፈር እግሬን ማውጣት አለብኝ። ልቤንም።

“አብረኸን ብትቀመጥ ይሻልሃል። ብትሄድ ምንም አታገኝም። የመጠየቅ መንገድ መሄጃ እንጂ፣ መድረሻ የለውም። ” ቀጥለዋል ጋሽ ዘውዱ።

“እርግጠኛ ነዎት? ”

“ሃሃሃሃ አሁንማ እርግጠኝነት ወንበር ላይ ተቀምጬ? ምን ስሆን ልጠራጠር? ”

“ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን በርሶና በወንበሩ መካከል ያለው ልዩነት ይጠፋል፤ ወንበሩ ተሸክሞዎት ይሁን፣ ወንበሩ ላይ ተቀመጠው ለመለየት እርሶም ይቸገራሉ።
ወንበር ላይ የተቀመጠ ወንበር ይሆናሉ። ቂጡን ለእርግጠኝነት ንፋስ የገለበ ሁላ እንዲያ ነው። ይበሉ ደና ይሁኑ፣ በርግጠኝነት ደህነት ባይኖርም! ”

“አይ ልጅ አገኘሁ፣ ልጅነት እኮ ነው ይሄ ሁሉ፣ የህይወት ልምድ ማጣት! እርግጠኛ ነኝ ልጅነትህ ነው ይህን የሚያናግርህ፣ አለመብሰል ነው። ”

“ልጅነትን ያለመብሰል ሰፈር የጣላችሁት፣ በልጅነታችሁ የመብሰል አቅም ማነስ ስላለባችሁ አይመስሎትም ጋሽ ዘውዱ? ”

“በል መንገድህን ጀምር ልጄ! እዚህ የተቀመጥኩት ጥያቄ ጠልቼ መሆኑን ዘነጋኸው? መልስን ከሌላ ቦታ ፈልግ”

መንገዴን ከመጀመሬ በፊት ወደ መቲ አቅ ጣጫ ተመለከትኩ። እዛው ነች።እወዳታለሁ። ዘላለም መቀመጥና፣ ዘላለም መሄድ ግን ህብረት የላቸውም።

መንገዴን ጀመርኩ።
“መፃህፉ እንኳን ያመነ ይድናል ነው ” የሚለው አሉኝ፣ የአቶ ዘውዱ የመጨረሻ ንግግር

” እሱን ለማመን ይከብደኛል ጋሽ ዘውዱ፤ ቢሆን እንኳን የሚጠይቁትን ለመግደል እጁን የሚያፍታታ አምላክ አይኖርም! ”

እግሬን ከሰፈሩ አወጣሁ፤ ልቤንም!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • assefatedi@gmail.com'
    ቴዲ commented on February 24, 2016 Reply

    በጣም ይመቻል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...