Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ሰባት)

«አንተ እረፍ ልመለስ! ያወቀ እንደሆነ ደግሞ ዲዳ ሆኖ ሀሁ ሳስቆጥረው ልክረም?» የሚለውን ሳቃቸው ያጀበውን ድምፅዋን ነው። ሳቃቸውን ሳይጨርሱ ብቅ ሲሉ መንቀሳቀስ አቅቶኝ እንደቆምኩ ነበር። > የሚለውን እንደፃፍኩ አቁሜ
« በመድሃንያለም !ውይ ምን ሆና ነው?» አልኩኝ ራሴው ቁዝም ብዬ
«ሰው! ሰው ሆና ነው! የትኛውስ ሰው ቢሆን እንዲህ አይደለም?»
«ይሄ ሰውነት አይደለም!!» ለወሬ እየተቅለበለብኩ ኮንፒውተሩን መሬት ላይ አስቀምጬ በጉልበቴ መሬቱ ላይ ተንበርክኬ ወደእርሱ እየዞርኩ።
«ትክክለኛ ሰውነት ውስጥ ክህደት የለም። ሰውነት ተፈጥሮ ነውኮ እንዴ? ልክ እና ስህተትን በሚያሰላ ህሊና በሚባል ሞተር የሚዘወር ተፈጥሮ ነው። የማንበብህ ብዛት፣ ሀይማኖት፣ የልምድህ ክምችት አልያም ስልጣኔህ ወይም ህግ የሚሰጥህ ነገር አይደለም።»
«ህሊና ከጠቀስቻቸው ዝርዝሮች ተፅዕኖ በላይ አይደለም።»
«በሱ እስማማለሁ። ለዛ ነው ተፈጥሮ ነው ያልኩህ!! በመረጥከው መንገድ ልታሳድገው ወይም ደግሞ ልታዳፍነው ትችላለህ። ለምሳሌ የህሊናህን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ አልፈህ አንድን ነገር ስታደርግ በደጋገምከው ቁጥር የፀፀትህ መጠን ይቀንሳል። ያ ምናልባት ከዘረዘርኳቸው በአንዳቸው ተፅዕኖ ምክንያት ህሊናህን ላለመስማት ወስነሃል ማለት ነው እናም በሱኛው እሳቤህ ህሊናህን ትከድነዋለህ። በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሔርን በመፍራት ውስጥ በስነስርዓት እና በመልካም ሀሳቦች አዕምሮህን ስታበለፅግ የህሊናህን ቀይ መብራት በደንብ ለማዳመጥ ንቁ ትሆናለህ። በእርግጠኝነት ግን በምንም ተፅዕኖ ህሊናህን ብታዳፍን ሰውን መጉዳት ወይም ክህደት ሰውኛ አለመሆኑን ለመረዳት አትቸገርም።»
«ችግሩ አብዛኛው ሰውኮ ሰውን ለመጉዳት ብሎ አይጎዳም። ከሚጎዳው ሰው እና ከራሱ መምረጥ ሲኖርበት ግን እራሱን ያስቀድማል። ይሄ ደግሞ ትክክለኛ የሰው ስሜት ነው።»
«እና ማዕረግም ራሷን ነው የመረጠችው እያልከኝ ነው?»
«አዎ! ከእኔ ደስታ እና ከራሷ ደስታ መምረጥ ሲኖርባት ራሷን መረጠች ብዬ ነው የማስበው። እስኪ አስቢው ያን አዲስ? አይጨንቅም? ከጠዋት እስከማታው ማዕረግ፣ ደስታው ሀዘኑ ማዕረግ፣ መብላት መጠጣቱ ማዕረግ፣ መስራት ማወቁ ሁሉ ማዕረግ…….. በህይወቱ ከእርሷ ውጪ ምንም ግብ እና ዓላማ የሌለው ፍጡር! አይጨንቅም? በሱ ህይወት ውስጥ ያንን ሁሉ ሆኖ መኖርስ ነፃነትን ማጣት አልነበረም? እሷ ደግሞ በእንደዛ ዓይነት አጥር የማትያዝ ፣ ነፃነቷን የምትወድ ፣ እንደስሜቷ መብረር የምትፈልግ ፣ እሳትም ቢሆን ሞክራ መፈተን የምትፈልግ ዓይነት ነበረች። ከዓመት ዓመት አንድ ዓይነት ቀን ያለው ዱዝ ደስታ ወይስ የራሷን አድቬንቸረስ ቀን መምረጥ ነበረባት። ራሷን መረጠች። »
«አንተ የምርህን ነው? እሺ ንገረኝ ከዛ በኋላ የተፈጠረውን?»
« አልራበሽም? የሆነ ነገር ከበላን በኋላ አንፅፍም?»
«አልራበኝም! ከዛ በኋላ የሆንከውን ካልሰማሁ ደግሞ መብላት አልፈልግም። መፃፉን በኋላ እንፅፈዋለን። ንገረኝ! ከዛስ?» ለወሬ ስቁነጠነጥ ትንፋሼ ፊቱን የሚሞቀው ያህል ቅርበት ላይ እንዳለሁ ያወቅኩት እጁን በአንገቴ አዙሮ ማጅራቴ መጨረሻጋ ያሉትን ድፍት ያሉ ፀጉሮች ሲነካካቸው ነው። (ከግንባርሽ ይልቅኮ ከጀርባሽ ነው ቤቢ ሄር ያለሽ ይለኝ ነበር ድሮ)
«ከምኑ በኋላ?» አለኝ እጁ ምን እንደሚያደርገኝ ስለሚያውቅ ፈገግ ብሎ።
«ከወንድምህ ጋር ከሰማሃት በኃላ……. ከዛ ግን ይሄን እጅህን አሳርፈው እና ነው» ብዬ እጁን አንስቼ ወደቦታው እየመለስኩት።
«አውርቼም፣ መንካት ተከልክዬም? እሺ የሆነውን ላውራሽ ግን እጄ የፈለገበት ይረፍ?»
«የፈለገበት ማለት?»
«ሃሃሃሃ አይዞሽ የማወራውንም እንድትሰሚኝ ስለምፈልግ የሚያደነቁርሽ ቦታ አልከውም! ሙች ከአንገትሽ አላልፍም!»
«ልለፍ ብትልስ……….» ብዬ ሳልጨርስ እጁን የነበረበት መልሶ ወሬውን ቀጠለ።
«ለመጀመሪያ ጊዜ ፓኒክ ያደረግኩት ያኔ ነው። በእርግጥ የሄድኩበት ሆስፒታል ያልተስማማው ምግብ በልቶ ነው ነበር ያለኝ። (ሳቅ ነገር አለ።) ግርግሩ ሰክኖ ሆስፒታል መጣች። <ውጪልኝ ላይሽ አልፈልግም!> ብዬ ስጮህባት አባቴ እንኳን መኖሩን ከምንም ሳትቆጥረው <ተመስገን ቢያንስ ማውራት ትችላለህ> ብላ አጠገቤ እንደደረሰች በጥፊ ነው ያጮለችኝ።» ብሎ ፍርስ ብሎ ሳቀ
«እንዴ?» አልኩኝ ሳላስበው።
«ጥፊዋንም የማጣጥምበት መልስም የምሰጥበት ጊዜ ሳትሰጠኝ እሷ ማውራቷን ስትቀጥል አባቴም እንደእኔ ግራ ገብቶት ነው መሰለኝ ዝም አለ። አስተውሎ ላየን እኔ ቺት አድርጌባት እንጂ እሷን ከወንድሜጋ ይዣት አይደለም የሚመስለው። ስታወራ ግልብ ናት አላልኩሽም?
<ምን ልሁን ነው የምትለው? አንድ ሴት የሌላ ወንድ ከንፈር ሳመችብኝ ብለህ መተንፈስ እስኪያቅትህ ትንፈራፈራለህ? ለሴት ብለህ በራስህ ላይ ተስፋ የምትቆርጥ ጅል ነህ? ገና 24 ዓመትህኮ ነው። ከዚህ በኋላ ሌላ አስር ሴት በህይወትህ ውስጥ ልትመጣ እንደምትችል አታውቅም? እድለኛ ካልሆንክ ደግሞ አስሯም ልብህን ሰብራው ልትሄድ ትችላለች። መጀመሪያ ራስህን ውደድ። ከእኔ ጋር ያሳለፍካቸው አመታት ከምንም እና ከማንም በላይ ራስህን መውደድ ካላስተማሩህኮ አከሰርከኝ! ይሄ ስታነበው የከረምከው መፅሃፍ ምንም ብስለት ካልጨመረልህ ለምንድነው ጊዜህን የምታባክነው? ምን አይነቱ እንከፍ ነው በአባቢ ሞት? ምን ይጠበስ? አዎ ወንድምህን ስሜዋለሁ! እ? ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ጉልበትህን አቅፈህ ስታለቅስ እና ስትጃጃል ልትኖር ነው? ወይስ አሁንም ደግሞ የሆነ ሰው መጥቶ እስኪያነሳህ pause አድርገህ ልትጠብቅ ነው?>
እኔስ የማወራበት አቅሙም ወሬውም አፌ ላይ ስላልነበረ በዛ ላይ እሷ የጭንቅላቴም የአካሌም አዛዥ ስለነበረች ዝም ብዬ ከመስማት ውጪ ምርጫ አልነበረኝም። የገረመኝ አባቴ ደስ ያለው ነበር የሚመስለው። እሷ ያለችውን ማለት ፈልጎ በሆነ ምክንያት ያቃተው እና እሷ የልቡን የተናገረችለት ነበር የሚመስለው። የሆነው እና ያልሆነው ተምታታብኝ። ሀሳቤን እና እውነቱን አወጫበረችብኝ። ጉንጬን እንደመነካካት ነገር አድርጋኝ። ደግሞ እናታዊ በሆነ ሹክሹክታ

<በህይወትህ የሚፈጠር ነገር ሁሉ ያንተ ጥፋት ወይም ሀላፊነት አይደለም። it’s just life! Mess is just one of life’s package! ያንተ ሀላፊነት ወይም ጥፋት የሚሆነው የተፈጠረው ነገር ላይ ሙጭጭ ብለህ እዬዬ ማለት ወይም አቧራህን አራግፈህ መነሳት የቱን መምረጥህ ነው። የተፈጠረው ነገር የእኔ ምርጫ እንጂ ያንተ ጥፋት አይደለም> ብላ አባቴን አልፈራችውም። ከንፈሬን ስማኝ ተነሳች! ያለችው በወቅቱ ይግባኝ አይግባኝ አላውቅም። ቅድም ከወንድሜጋ ተሳስማ ከነበር አሁን እኔን መሳሟ ልክ ይሁን አይሁን ለማስላትም ፋታ አልሰጠችኝም። ከንፈሯ ሲስመኝ ማሰብም አይሆንልኝም። ዝም ብዬ ፈዝዤ ነበር የማያት ……… ደግሞ ወደ መጀመሪያ ቁጣዋ ተመልሳ
<እእ! ራስህን ለመጥላት እኔን ሰበብ እንድታደርግ አልፈቅድልህም! ራስህን ማንሳትህን ሳላረጋግጥ ከህይወትህ ወደየትም አታርቀኝም! እንዳትለፋ! ነገ በተለመደው ሰዓት እንገናኛለን!> ብላኝ ወጣች። እሺም እንቢም አታስብለኝም! በእኔ ላይ አዛዧ ራሷ እንደሆነች ታውቅ ነበር።» ብሎ ስለእርሷ ተመስጦ ሲያወራ አቁሞ የነበረውን መነካካቱን ቀጠለ።
«አሁንም ድረስ ትወዳታለህ?» አልኩት ሳላስበው። ስለእርሷ ሲያወራ ሳቁ ፣ ፈገግታው ፣ ዓይኖቹ ፣ የድምፁ ለዛ ……. የፊቱ ፀዳል …. በፍቅር የተሞላ ነው።
«አልጠላትም! ህይወቴን በሁለቱም ዋልታ የቀየረች ሴት ናት! ያኔ የነበረኝ ስሜት አሁንም መኖሩን ከሆነ ማወቅ የፈለግሽው። የለኝም! ከዛ በኋላ ብዙ ነገር ተፈጥሯል።»
«እሺ ከዛ በኋላ ለሌላ ሴት እንደዛ ሆነህ ታውቃለህ?»
«እንደዛ ይሁን የተለየ አላውቅም! የዝቅታን መጨረሻ፣ የጨለማን ድቅድቅ ፣ የሞትን ያህል ፍርሃት ዓይነት ጭንቅ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጋኝ የምታውቅ ሴት አለች።» አለኝ በዓይኖቹ ሙሉ ዓይኖቼን እያየ
«ደስ የሚል ስሜትኮ አይደለም የነገርከኝ ወይም ፍቅር አይደለም።!» አልኩት የሚላት ሴት እኔ መሆኔን ልቤ እየጠረጠረ። ድምፄ ደግሞ ምናባቱ ያልሞሰሙሰዋል? ቅድም ደህና አልነበር?
«እንዳለመታደል ሆኖ ስሜትሽ ከባለቤቱ ካንቺ ይልቅ በስሜት ለተቆራኘሽው ሰው ሲያጎበድድ ደስ የሚል ስሜት አይደለም።» ድምፁን ቀይሮ ወዲያው «አልራበሽም?» አለ
«እንዴ? አልጨረስክልኝምኮ ከዛስ?»
«አያልቅም trust me! እያረፍን ይሻላል።»
«እሺ በነገታው ሄድክ ወይስ ቀረህ? እሱን ንገረኝ።»
«አልገባሽም! ና ብላኝ ልቀር አልችልም። ራሴንኮ አላዘውም ነበር! Ofcource ሄድኩላት። ያውም ላያት እየናፈቀችኝ!»
«oh my God! የዓመታት ፍቅራችሁንኮ ነው ያረከሰችው? ወንድምህን ነው የሳመችው!»
«እሱን የማስብበት ክፍተት አልሰጠችኝም ነበር በሰዓቱ! ወንድሜን ከሳመችው በኋላ ሳመችኝኮ ……. ልኩ እና ስህተቱን አማታችብኝ። ከክብሬ ከኩራቴ ከወንድነቴ በላይ ከእሷ ጋር ያስተሳሰረኝ ስሜት ያይል ነበር። ሁሌም ራስሽን እስከማታዢው ድረስ ከሰው ጋር ያለሽን ግንኙነት ካጠበቅሽው የራስሽ የሆነ ነገር አይኖርሽም! ራስሽን ጨምሮ!!»
«እሺ ከዛስ?»
« ግልብ ናት አላልኩሽም? እውነቱን ነገረችኝ። < አንተ ህይወትህ የተለመደ እና ደባሪ ነው። እኔ ደግሞ unpredictable የሆነ ቀን እንዲኖረኝ ነው የምፈልገው። አልዋሽህም አፈቅርሃለሁ። ታሳዝነኛለህ። ግን ለእኔ ያ በቂ አይደለም። ወንድምህ ደግሞ ነፃ ነፍስ ያለው አደገኛ ነገር ለመሞከር የማያመነታ ደፋር ሆኖ አገኘሁት እና ሳበኝ። ከፈለግክ እመነኝ ካልፈለግክ ተወው ከመሳሳም ውጪ ምንም ያደረግነው ነገር የለም። እንዴት እንደምነግርህ ጨንቆኝ እንጂ እነግርህ ነበር። የሚጠቅምህ እውነቱን ብነግርህ ስለሆነ እውነቱን ልንገርህ አሁን ላይ ከማፈቅርህ በላይ ስለምታሳዝነኝ ነው አብሬህ ያለሁት። ያ ደግሞ ማናችንንም አይጠቅምም። ማንም ሴት ብትሆን ስለምታፈቅርህ እንጂ ያደረግክላት ነገር ይዟት ወይም ብትለይህ ትጎዳለህ ብላ አዝናልህ አብራህ ከሆነች ልክ አይደለም። ፍቅረኛህ አልሆንም። ለመጨረሻ ዛሬ ከምስምህ ውጪ አልስምህም። በየቀኑ ግን አለሁ። በእኔ ምክንያት አይደለም እንድትወድቅ እንድትወላከፍ አልፈቅድልህም።>
ብላኝ የስንብት ያለችኝን መሳም ስማኝ ተለያየን። እንዳለችውም ከቀን ተቀን ህይወቴ አልጠፋችም። በየቀኑ እስፖርት መስራቴን፣ ስራ መግባቴን ፣ በጠዋት መንቃቴን……… በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ታረጋግጣለች። የመጀመሪያዎቹን ሳምንታት አጠገቤ ሆና ላልነካት መታገል ህመም ስለነበር ባትመጣ ሁሉ ደስ ይለኝ ነበር። እንድከፋ ወይም በሷ መሄድ ራሴን እንድጠላ ጊዜ አልሰጠችኝም። ከወንድሜ ጋር ፍቅረኛሞች ሆነው መቀጠላቸውን አልደበቀችኝም። እኔ እንዳላያቸው ወይም እንዳላገኛቸው ስለምትጠነቀቅ ለመቅናትም እድል አልሰጠችኝም። ትኩረቴን ራሴን መስራት ላይ አደረግኩ። ብዙ ማንበብ እና ማሰላሰል ላይ አተኮርኩ። ለዓመታት ጓደኛዬ ሆነች። ከጊዜ በኋላ ከወንድሜ ጋር ተለያይተው ከሌላ ሰው ጋር ሆነች። አብሮ የፍቅር ጊዜ እንዳሳለፈ ወይም ወንድሜን መርጣ ትታኝ እንደሄደች አልያም በሷ ከአዘቅጥ ወጥቼ በሷው የሚያምን ልቤን እንዳጣሁ ……… ብቻ ብዙ እንደተኳኋነ ሰው ሳይሆን ልብ ለልብ እንደሚተዋወቅ ጓደኛ ብዙ አሳለፍን።»
«ቻልከው? ጓደኛ መሆኑን? »
«መሆኑን ሳይሆን ማስመሰሉን ቻልኩት። እሷ በህይወቷ ደስተኛ ነበረች። ጓደኛ ደግሞ ያን ደስታ አይበርዝም።»
«ከዛስ? እሺ?»
«ከዛ ያለው ብዙ ነው! እያረፍን!» ብሎኝ እጁን ከማጅራቴ አንስቶ ጉንጬን እንደመቆንጠጥ አድርጎ የቆነጠጠበትን እጁን ሳመው። ዘልዬ ተነሳሁ።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ስምንት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...