Tidarfelagi.com

‹‹እግዚአብሔር ለሚረሱት ሁልጊዜ ማስታወሻ ይልካል››

ብዙዎቻችን፣ ከልጅነታችን አንስቶ ‹‹ የጭንቅ ጊዜ ሳይመጣ በጉብዝናችሁ ወራት ፈጣሪያችሁን አስቡ›› ብንባልም አንደበታችን ለፀሎት፣ ጉልበታችን ለስግደት የሚዘጋጀው መከራ ከፊታችን ሲደቀን ብቻ ነው።

አመዛኙ ፀሎታችን ‹‹ከዚህ ፈተና አውጣኝ››፣
አብዛኛው ልመናችን ‹‹ይሄን የመከራ ጊዜ በድል አሻግረኝ›› ነው።
ሲጎድለን ‹‹ይሄን ጨምርልኝ›› ክፍተት ሲታየን ‹‹ይሄንን ሙላልኝ ›› እንጂ ሲሞላልን የምስጋና ፣ ሲተርፈን የማካፈል፣ ፈጣሪን የማስደሰት ዝንባሌው የለንም ።

በዚህ ዓለምን አንድ ባደረገ አስጨናቂ ወረርሽኝ ሰአትም የምናየው ይሄን ይመስለኛል። እግዚአብሔር እንደ ልማዱ ለረሱት ማስታወሻ መላኩም ይመስለኛል።

ማስታወሻው ሰርቷልና የጭንቅ ጊዜ መጥቷልና ስለ ፈጣሪያቸው የሚያስቡ በዝተዋል፣ ለፀሎት የሚንበረከኩ ጉልበቶች ጨምረዋል፣ ምህረትን የሚለምኑ በቁጥር ልቀዋል።

ስለዚህ ነገር ሳስብ የዳኛቸው ወርቁ ‹‹አደፍርስ›› መፅሃፍ ላይ ወይዘሮ አሰጋሽ ተቸግሮ ሊበደር ፊታቸው ኩስስ ብሎ ለቆመ ጭሰኛቸው የነገሩት ትዝ አለኝ…ቃል በቃል ባይሆንም ለዚህ ይስማማል የምለውን ቀንጭቤ እና ቅርፅ አስይዤ ከታች አስቀምጬዋለሁ
‹‹…እግዚአብሔር …ሁሉን ያያል…ሁሉን ያውቃል…አዎ…አንዳንዴ የማይሰማ የማያውቅ መስሎ መታየትን ይመርጣል። የበደሉትን ሰዎች እግሮች ተምበርክኮ ያጥባል- እንደፈለጋችሁ- …እንደ ስሜታችሁ ኑሩ የሚል ይመስላል….
….አንድ ቀን የእሱን ታላቅነት፣ የእሱን ወሰን የለሽነት፣ የእሱን አይመረመሬነት፤ ዘንጋ ያልን ጊዜ ግን ድራሻችንን ሊያጠፋ። ሊያመጣው ውርጅብኙን።
…..ስልጣናችሁን በሚገባ አልተጠቀማችሁበትም- ለክብሬ የሚገባኝን አላቀረባችሁልኝም- ከምታገኙት ገንዘብ ጥቂት ጥቂት እያነሳችሁ ጧፍ እና ዕጣን፣ ….መገበሪያና ዣንጥላ በማቅረብ ፈንታ በሙሉ ተጫወታችሁበት…ለጠጅ አደረጋችሁት…ስለዚህ እኔም የምሰራውን አውቃለሁ ሊለን…
….አንበጣ፣ አመዳይ እና ቸነፈር የምትበሉትን አሳጥተው ችጋር እንዲነዙባችሁ.አደርጋለሁ ሊለን…
…ጥጋብ የነፋውን… ዱለኛውን…..ጭራውን እንደውሻ እንዲወሽቅ አደርጋለሁ ሊለን…….!
ሊያመጣው የጭቃ ጅራፉን!….››
ብቻ ምን ዋጋ አለው? …ዛሬ ላይ ይሄ ሁሉ የገባን ፣ ግርማ ሞገሳችንን ከትከሻችን ስለተገፈፈ፣ ውጥናችን በእንጥልጥል ስለቀረ፣ ኑሯችን በድንገት ስለተመሳቀለ እንጂ ነገር ሁሉ እንደ ነበር ቢቀጥል ኖሮ ያው…እንደ ለመድነው ኩራት እንደነፋን እንኖር ነበር…
ይሄኛውንም የመከራ ጊዜ በምህረቱ ብዛት እናልፍና…
እንደ ልማዳችን በእብሪት ተሞልተን ፈጣሪን እንዘነጋና፣ እግዚአብሔር ደግሞ ሌላ ማስታወሻ ለመላክ ይገደድ ይሆናል…

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...