(ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ)
በቀደም እለት : ” ወንድ ልጅ አይጣ” የሚል ጥቅስ ግንባሩ ላይ የተፃፈበት ሃይገር ባስ ተሳፈርሁ።
” ሃይገር ባስ ” ባለም የመጨረሻው መናኛ አውቶብስ ነው። ቻይና ላፍሪካ ቺስታ ሀገሮች አንድ ባቡር በሸጠች ቁጥር ምራቂ አድርጋ የምትሰጠው ሃይገር ባስን ይመስለኛል። ደረጃ መዳቢዎች ከጋሪ ከፍ ከባጃጅ ዝቅ አድርገው ይመድቡታል። ባሱ ሁሌም በሰውና በጥቅስ የተሞላ ነው። አስር ሰው ከባሱ ሲወርድ አይተህ ” እፎይ ግልግል” ብለህ የተለቀቀ ወንበር ለመውረስ ስትጣደፍ በምትኩ ሰላሳ ሰው ተግተልትሎ ገብቶ እንደ ጉም ያፍንሃል።
ተሳፋሪው አንዱ ባንዱ ላይ ከመጣበቁ የተነሳ ካውቶብሱ ስትወርድ የታጠቅከውን ቦላሌ ሳይቀር ጥለህ ልትወርድ ትችላለህ።
በሃይገር ባስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ሙዚቃ አይከፈትም። ከተከፈተ አየሩን የሚቆጣጠሩት ኬኔዲ መንገሻና አረጋህኝ ወራሽ ናቸው።
ከማሃል ካሉት ወንበሮች ባንዱ ላይ ቁጭ ብየ ያውቶብሱን ባጥ የሙጥኝ ብለው የቆሙትን ተሳፋሪዎች ብብት በማየት እየተዝናናሁ ነው። መአት አይነት ብብት ይታየኛል። ትኩስ መላጣ ብብት – እንዲያው ከምበል ደፋ የሚል ጎፈሬ ያለው ብብት-ዶዶራንት የጠገበ ዘመናዊ ብብት-ላብ የሚያካፋ : ዳይፐር የሚሻ ብብት- በጠረኑ : ጎረምሳ አይጥ መግደል የሚችል ብብት-በጣም ከመጎድጎዱ የተነሳ ቢያጮልቁበት የባለቤቱን ሳንባ የሚያሳይ ብብት።ወዘተ ብብት።
ብብት መሾፍ ሲሰለቸኝ ሞባይሌን አውጥቸ መጎርጎር ጀመርሁ። አጠገቤ ያለው ሰውየ የስልኬ እስክሪን ላይ ተመስጦ ቀረ። ልገላምጠው ፈልጌ ለመገላመጫ የሚሆን ክፍት ቦታ የለም።
“ወንድሜ! ኧረ ተፋታኝ ! ሞባይሌ ያራት ኪሎ የማስታወቂያ ሰሌዳ መሰለህ እንዴ?? !!”
ልለለው ፈልጌ ነበር። “መተው ነገሬን ከተተው “ብየ ዝም አልሁ። ለነገሩ ብሳፈጠውስ ምን አመጣለሁ? ባሬላ ሲሸከም በኖረ መዳፉ ትንሽ ገፋ ቢያረገኝ በመስኮት ወጥቼ ተከታዩ አውቶብስ ውስጥ ልገባ እችላለሁ።
“ሸማቾች ላይ ስንደርስ ታወርደኛለህ ”
የሚል የሴት ድምፅ ሰማሁ። ወደ ድምጡ ስዞር ባሮጌ አንሶላ ህፃን ልጅ ያዘለች ሴትዮ በቆመችበት ትወዛወዛለች ። የልጁ ግማሽ ሰውነት እኔ ላይ ስላረፈ : ተጋግዘን አዘልነው ማለት ይቻላል። አሳዝናኝ ወንበሬን ለቀቅሁላት። በለቀቅሁት ወንበር ከበስተጀርባየ ቆሞ የነበረ ጎረምሳ ” አመሰግናለሁ” ብሎ ተቀመጠበት።
የታዘለው ልጅ አውቶብሱን በለቅሶ መቀወጥ ጀመረ።
” አባብይው እንጂ” አልኳት።
“ተወው አልቅሶ አልቅሶ ሲደክመው ሞተር ያጠፋል”
“ምነው ጨከንሽበት!! ያብራክሽ ክፋይ አይደለም እንዴ?”
“አደለም!! ስኳር ቅድሚያ የሚሰጠው ልጅ ላለው ነው ስለተባለ ተጎረቤት ተውሸው ነው!”
በሹፌሩ በጋቢና መስታውት መአት አይነት ጥቅስና ስእል ተገጥግጧል። ” ደንበኛ ካልቀበጠ ንጉስ ነው”ይላል አንዱ ጥቅስ። “የክረምትን ፀሀይ የባዳን ጥርስ አትመን” ይላል ሌላው። ሹፌሩ ጥቅስ አጥብቆ ከመውደዱ የተነሳ:-
” ለሀያልም ሀያል : ላጥቂም አጥቂ አለበት
አሰንብተኝ አምላክ: ባይኔ ጉድ ልይበት”
የሚል ጥቅስ ግራ ክንዱ ላይ ተነቅሷል።
“ስማ የሾፌሩ መስታወት በጥቅስና በስእል ተሸፍኗል:
መንገዱን እንዴት እያየ ነው ሚነዳ?” አልሁት ወያላው ባጠገቤ ሰቅስቆ ሲያልፍ።
” አትጨነቅ ጄለሴ!! ” አለኝ ወያላው” ሾፌሩ አራት አመት በዚህ መስመር ስለነዳ መንገዱ አይጠፋውም ”
ጉርድ ሾላ ስንደርስ ባሱ ተበላሽቷል ተብሎ ተራገፍን።
የጎዳናውን ዳር ይዤ ሊፍት እየቀላወጥሁ ቆምኩ። የኮሌኔል አልፋ ባለቤት ወይዘሮ ሮዝ አዲስ ሞዴል ላንድሮቨር እየነዱ ዐይተውኝ እንዳላዩ አለፉኝ ። አልፈርድባቸውም። ለኔ ሊፍት መስጠት አንድ ደባሪ ትዝታ ሊቀሰቅስባቸው ይችላል።
ባንድ ወቅት እኔና ወይዘሮ ሮዝ ጂም ውለን ስንወጣ ሊፍት ፀደቁብኝ። ጋቢና ተቀምጨ እያወጋን ስንሄድ መብራት ያዘን። መብራት ላይ ኩዊን ላቲፋን የመሰለች ግድንግድ የጎዳና ተዳዳሪ : የመኪና መስኮት እያንኳኳች ትለምናለች። ለነገሩ ፊቷ ላይ ያለውን ኩራት ለተመለከተ ምትለምን ሳይሆን ድርሻዋን የምትጠይቅ ነው ሚመስል። ወይዘሮ ሮዝ መስታዉቱን አውርደው ሽልንግ ሰጥተው በመገላገል ፋንታ:-
” የቤት ሰራተኝነት ብቀጥርሽ ትሰርያለሽ?” አሉ
” ለምን አልሰራም ?!” መለሰች ኮረዳይቱ።
” ተያዥ አለሽ?”
ጎዳና ተዳዳሪቱ የሰጠችውን ምላሽ መዝግቤ ለትውልድ ባላስተላልፈው ደስ ይለኝ ነበር።🙈
” ያንቺን ጭገር ሲያበጥሩ ለመዋል ደሞ ምን ተያዥ ያስፈልጋል?”
የሚል ነበር ምላሿ።
ከብዙ ጥበቃ በሗላ አንድ አውቶብስ ያለሁበት ቦታ ደርሶ ቆመ። መላው ሰውነቴ ገብቶ ሳያልቅ ጉዞውን ተያይዞታል። ለመጀመርያ ጊዜ በስርአትና በጥሞና የተቀመጡ ተሳፋሪዎችን በማየቴ እየተገረምኩ።
” ሹፌር መገኛ ሲደርስ ታወርደኛለህ!”
አልሁ ወንበሬ ላይ ተደላድየ።
“ጌታው! ይሄ ቀራኒዮ መዳኒያለም የሚሄድ የንግስ አውቶብስ ነው። ከዚህ በሗላ ደብረሊባኖስ ሳንደርስ አንቆምም”
One Comment
ወደዉ አይስቁ አሉ ሃሃሃሃሃሃሃ ” ለሀያልም ሀያል : ላጥቂም አጥቂ አለበት
አሰንብተኝ አምላክ: ባይኔ የበዉቄን ጉድ ልይበት”