Tidarfelagi.com

ፎቶና ውዴታ

ፌስቡክ የተቀላቀልኩ ወደ 2012 አካባቢ ነው፤ እና ያኔ ከቤተሰቤ እና ከጎረቤት በቀር የሚያውቀኝ አልነበረም፤ የፌስቡክ አጠቃቀም ራሱ በቅጡ አልገባኝም ነበር፤ የሆነ ጊዜ ላይ ሁለት ሄክታር ቶክሲዶ ሱፌን ግጥም አድርጌ ለብሼ፤ ጆፌ አሞራ እሚያህል ክራቫት ጣል አድርጌበት፤ ፎቶ ተነሳሁና ፌስቡክ ላይ ለጠፍኩ ፤ ከዚያ ፈንድሻ እየበላሁ የህዝቡን ምላሽ ብጠብቅ ብጠብቅ ምንም የለም፤ ደብረማርቆስ ዘመድ ጠይቄ ስመጣ አስካለ የተባለች ልጅ “ላይክ“ አድርጋዋለች፤ ያኔ የላይክ ምልክት የነበረው አውራ ጣት በጣም ግብዳ ነበር! መንገድ ዳር ይዘኸው ብትወጣ ”ሊፍት’ የሚሰጥ መኪና ማስቆም ሁሉ ትችላለህ! ከመደሰቴ የተነሳ “ፎቶየን ስለወደድሽው አመሰግናለሁ“ የሚል መልክት ሰደድሁላት፤ ኢንቦክስ የላክሁላት መስሎኝ ግድግዳየ ላይ እንደለጠፍኩት ያወኩት “በውቄ የዛሬውን ግጥም ደግሞ ርእሱን ብቻ ነው የለጠፍከው’’ እሚል አስተያየት ሳነብ ነበር። አትፍረዱ! በሰም በታሸገ ኢንቬሎፕ ፅላሎ ወረዳ ከሚኖር የብእር ጉዋደኛ ጋር ደብዳቤ ስለዋወጥ ያደግክሁ ሰውየ፤ ኢንቦክስ ቢደናገረኝ አይገርምም።

ሴቶች በጠቅላላው፤ ቆንጆ ሴቶች በተለይ፤ ፎቶ ለጥፈው ውዴታ( ላይክ) ለመሰብስብ ችግር የለባቸውም፤ ፎቶ ሲነሱ ደሞ ፤ የሳምንት እቅድ ነድፈው በቂ በጀት መድበው በደንብ ተዘጋጅተው ነው፤ የመታወቂያ ጉርድ ፎቶ ለመነሳት ድሮን ሳይቀር እሚከራዩ አሉኮ! የኔ እናት የሩቅ ዘመድ ሲሞትባት ሀዘኑዋን ለመግለፅ ፊትዋን ትነጭ ነበር፤ የዘንድሮ ዝነኛ ሴቶች “በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ እናወግዛለን“ የሚል መልክት የሚያስተላልፍ ፎቶ ለመለጠፍ ፤ አራት ሰአት ሙሉ የቁንጅና ሳሎን ውስጥ ይቆያሉ።

ሰዎች ነን፤ እንድንወደድ እንፈልጋለን! አንድ ሺህ ጉዋደኛ ኖሮህ አስር ሰው ብቻ ፎቶህን ከወደደው ይደብርሀል፤ ከወደዱህ በላይ ጭንቅላትህን የሚቆጣጠረው ጥግ ላይ ቆመው፤ እንደ ሙናየ መንበሩ ከንፈራቸውን አጣመው፤ ባላየ የሚያልፉህ ሰዎች አሳብ ነው፤

ለማንኛውም ብዙ ሺህ ሰው ፎቶህን እንዲወድልህ ትፈልጋለህ? አማላይ ወይም ያንድ አሙስ ሰለብሪቲ መሆን አይጠበቅህም! የሚጠበቅብህ ይህ ነው፤ አዋሽን የሚያህ ያህል ባንዲራ ልበስ ፤ ግንባርህ ላይ ኤርትራን የሚያካትት የኢትዮጵያ ካርታ ተነቀስ! ከጀርባህ የታወቀ ባለታሪክ ሀውልት ወይም የገዳም ወይም የመስጊድ ምስል ቢኖር ቢኖር አይከፋም፤ የኢትዮጵያ ፊደል ምልክት ያለበት ቲሸርት ልበስ! የኢትዮጵያ ቁጥሮች የተፃፉበትን ሰሌዳ ደግሞ እንደፍሬው ሃይሉ አኮርድዮን አንገትህ ላይ አንጠልጥል! በቀኝ ክንድህ ላይ ከቅዱስ መፅሀፍ የተወሰደ ጥቅስ ጣል አርግበት ! ግራ ክንድህስ ለምን ስራ ይፈታል? ደም ለግስበት! ፤

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...