የድሜ ነፋስ በገላየ : ተረማምዶ ኮበለለ
ልቤን ክንዴን እያዛለ
ያቀፍኩትን እየቀማ : የያዝኩትን እያስጣለ።
እድል በኔ ጨከነ ስል-በምረት እጅ ደባበሰኝ
አንቺ ነጥቆ ከቅፌ ላይ-በትውስታ ደሞ ካሰኝ።
አሰታወሰኝ
አስታወሰኝ።
ወድያው ታይቶ :ጠፊ ኩርፍያሽ
ገራም ሳቅሽ : ልዝብ ልፍያሽ
ያለም ዘፋኝ የማያውቀው
የግልሽ ዳንስ ውዝዋዜ
ትውስ ትውስ ባለኝ ጊዜ
ከግር ጥፍሬ
እስከ ጠጉሬ
ደስታ ነው የሚያቀልመኝ
ያንቺ ነገር ባሰብሁ ቁጥር :ፈገግታ ነው የሚቀድመኝ።
በሰጠሽኝ ፀጋ መጠን: የሰራሽኝ ጉድ አያልቅም።
እኔ ባንች ትዝታ እንጂ: በተራቢ ቀልድ አልስቅም።
ማፍቀር ማለት ለካ ፍቺው : መጃጃል ነው አውቆ ፈቅዶ
ከገደል ላይ መወርወር ነው ተጨፍኖ በራስ ፈርዶ።
አፈቀርኩሽ በየቀኑ :ተጃጃልሁኝ ደጋግሜ
ከገደል ላይ ተከስክሼ: ሞተ ሲሉኝ አገግሜ
ያጥንቶቼን ርጋፊ: እንደዛጎል ለቃቅሜ
እንደ ቆሎ : ጥርሴን ቅሜ
ያደረኩሽ ሲደንቀኝ: ያደረግሺኝ ሲገርመኝ
እፍረት ፀፀት አይደለም: ፈገግታ ነው የሚቀድመኝ !
አውቃለሁኝ ጊዜ ሂዷል :ታሪካችን ተጠቅልሏል።
በሄድንበት ጎዳና ላይ: የመለየት ዝናብ ጥሏል
በርምጃችን ምልክት ላይ: ረጃጅም ሰርዶ በቅሏል
ብቻ ምሾ ቢደረደር: የሆነውን ላይለውጠው
ለንባየማ ፊት አልሰጠው።
ያሳሳምሽ ለዛ ቀርቶ :እንደ እንጎቻ እሚጥመኝ
የነከሽኝ የቧጨርሽኝ: አገርሽቶ ቁስሉ ሲያመኝ
ፈገግታ ነው የሚቀድመኝ!!