Tidarfelagi.com

ፅነፈኝነትን መፍጠር (Radicalization)!

ፅንፈኝነት በምታምንበት አቋም ላይ ጫፍ መድረስ ነው። በዚህ ዓለም ላይ በያዝከው ጫፍ አቋም ላይ ተንጠላጥለው የጫፍ ጫፍ እንድትደርስ የሚያበቁ አንድ ሺህ ምክንያቶችን ጧት ማታ በገፍ እየሰጡ ጫፍ የሚያስረግጡህ የፅንፈኝነት ፈጣሪዎች አሉ።

ለምሳሌ ሁሉም ኢተዮጵያዊነትህን አፍቃሪ ሕዋሳትህ እስኪያልቁብህ ድረስ አሰቃይተው፣ ቀምተው፣ ረግጠው፣ ዘርፈው፣ አስረው… ሁሉንም መጥፎ ነገሮች ፈፅመውብህ “ኢትዮጵያዊነቴ ከመከራ በቀር ምን አስገኘልኝ?” እንድትል የሚያስገድዱህ የፅንፍ ፈጣሪዎች አሉ። ኢትዮጵያዊነትህን ተቀብለህ በኢትዮጵያዊነትህ ተደስተህ ለመኖር የሚያስችሉ ምክንያቶችህን በየተራ አንድ በአንድ የሚጨርሱብህ ሰዎች።

ኢትየጵያዊነትህን ስታስብ በዓለማቀፍ የእርዳታ ለጋሽ ሀገራትና ተቋማት ፊት ሁሌ የደረቀ ገላ ያላቸው ህፃናት ምስሎች ለማሻሻጫነት እየቀረቡ “አስቸኳይ” እርዳታ ሲለመንልህ ይታሰብሃል?
ኢትዮጵያዊነትህን ስታስብ በየጎዳናው የተዘረሩ ውር ውር የሚሉ በሰው ልጅ ክቡር ፍጡርነት ያለህን እምነት የሚሸረሽሩ ወገኖችህን ታያለህ? – እና ኢትዮጵያዊነትህን ትረግማለህ?
ኢትዮጵያዊነትህን ስታስብ ያለማንም ከልካይ ሰውን እንደ ከበሮ የሚደልቁ አረመኔ ፌዴራል ፖሊሶች፣ አጋዚዎች፣ ስናይፐሮች፣ ሲለዩዎች.. ይታሰቡሃል?
ኢትዮጵያዊነትህን ስታስብ ባመንክበት ነገር አፍህን ሞልተህ ብትናገር የሚደርስብህ መገፋት፣ እንግልት፣ ድብደባ፣ ማሰቃየት፣ መገረፍ፣ መሰደድ፣ መታሰር፣ መገደል… ይመጡብሃል?
ኢትዮጵያዊነት ሲባል አብሮ ከኖርክበት ቀዬ መፈናቀል ይታሰብሃል? ረሃብ ያስጨንቅሃል? የህልውናህ ቀጭን ክር እንዳትበጠስ ለምድረ “ዶማ” ባለጊዜ አንገትህን ደፍተህ የምትብከነከነው ነገር ይታሰብሃል?
ኢትዮጵያዊነትህን ስታስብ የአንተም ድርሻ ያለበትን፣ የአንተ የሆነውን፣ የህዝብህ የሆነውን.. ሌሎች በባለጊዜ ኃይል ተደግፈው እንደ መዥገር እየመጠመጡ ሲበለፅጉ… አንተ ግን በድህነትና በመብት እጦት ህይወትህ ተመጥምጦ ሲያልቅ.. ይታሰብሃል?
ኢትዮጵያዊነትህን ስታስብ ከሀቀኞች ይልቅ ሙሰኞችና ዘራፊዎች፣ ወመኔዎችና ቀማኛዎች ከብረው የመኖራቸው ነገር ያንገበግብሃል?
በቃ ኢትዮጵያዊነትህን ስታሰብ … ኢትዮጵያዊነትህን ከምታከብርና ከምትወደው ይልቅ.. ፈፅመህ ኢትዮጵያዊነትህን እንድትረግም፣ “ያለመታደል ነው” እንድትል፣ በኢትዮጵያዊነትህ እንዳትኮራ የሚያደርጉህ በቂ – ከበቂም በላይ – ምክንያቶች በየዕለቱ “readymade” ሆነው በገፍ ቀርበውልሃል?
ወንድሜ እመነኝ። እህቴ እመኚኝ። ወገኔ እመነኝ። ይሄ የምንኖርበት ሥርዓት (ኢህአዴግና ተረፈ-ምርቱ).. ሁሉንም ኢትዮጵያዊነትህን የምትጠላበትን፣ የምትረግምበትን ምክንያቶች ሁሉ በገፍ ያዘጋጀልህ.. እና በላይ-በላዩ የሚግትህ… ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ ፅንፈኝነትን (anti-Ethiopian radicalization) ጧት-ማታ የሚያመርት ሥርዓት ነው።

በዚህ ሥርዓት ብዙ ፀረ-ኢትዮጵያ እና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ፅንፈኝነትን የመፍጠር ሥራዎች ተከናውነዋል። በድንገቴ አይደለም። በአጋጣሚ አይደለም። የጎንዮሽ ውጤት ሆኖም አይደለም። ሆነ ተብሎ ነው ይህ የ “ራዲካላይዜሽን” ሥራ ያለመታከት የተሠራው።
የፀረ-ኢትዮጵያ ራዲካላይዜሽኑ በአንድ በኩል ሠርቷል። ውጤቱን እያጨድን ነው። ገና ወደፊት ብዙ መከራ ያሳፍሰናል።

በሌላ በኩል ግን አ ል ተ ሳ ካ ም ! ! ! !
በዚህ ሁሉ ፅንፈኝነትን ለመፍጠር በሚዘንብ መከራ መሐል – “ኢትዮጵያዬ !” ብለው አንዲቱን ምስኪኒቱን ሀገራቸውን ከተዘፈቀችበትና ከተደገሠላት መከራ ለማውጣት ልባቸውን አፅንተው የቆሙ እልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያን – ዛሬም አሉ። በፅናት። በውበት። በግርማ። እና በሀገር ፍቅር ደምቀው!!!!!
ፈጣሪ አምላክ የኖህ መርከቡን ኢትዮጵያን ፈፅሞ አይተዋትም!
ኢትዮጵያ ታበፅዕ እደዊአህ ሀበ እግዚአብሔር።
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ ትዘረጋለች።
ፅንፈኝነት ተፈጥሮላትም – ሙከራው ያልተሳካባት፣ የማይሳካባት – እናት ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...