ሄኖክን ከተዋወቅኩ ጀምሮ ልቤን በደስታ ያዘለለ የፍቅር ጊዜ ትዝ አይለኝም። በሴት ወግ ፍቅሩ ይዞኝ የተጃጃልኩበት፣ ነጋ ጠባ ስለእሱ ያሰብኩበት፣ እንቅልፍ ነስቶኝ የተቸገርኩበት ወቅት ትዝ አይለኝም።
ትውውቃችን ተራ እና ቀላል፣ ለሰው ቢነግሩት አፍ የማያስከፍት- አ-ላስደናቂ ነበር።
በምኖርበት ህንፃ ላይ ለወራት ክፍት ሆኖ የከረመውን ባለአንድ መኝታ ክፍል ቤት ተከራይቶ ገባ።
ከሰነበተ በኋላ ፣ ስንገባ ስንወጣ በአዲስ አበቤ ጎረቤት ደምብ የከአንገት በላይ ሰላምታ ጀመርን። ትንሽ ሲቆይ ወሬያችን ከ‹‹ ሃይ-ታዲያስ-ደህና ዋልክ-ሰሞኑን ጠፋሽ-ብርዱ አልተቻለም አይደል›› ወደ‹‹-የእነዛ ሰዎች ልጆች ጫጫታ አንተንም አላስተኛ ይልሃል-አንቺንም ኪራይ ጨመሩብሽ እንዴ- መቼ ነው የራሳችን ቤት ኖሮን የምንገላገለው-›› ሰንብቶ ደግሞ፣ ‹‹ቢሮሽ ሩቅ ነው?እኔ እንኳን አንዲት አሮጌ መኪና አለችኝ…ካዛንችስ ከሆንሽማ መንገዴ ነው እሸኝሻለሁ….››አይነት ጨዋታነት አደገ።
ከዚያ በኋላ በአምስት አመት መሆን የሚገባው ነገር ሁሉ በአራት ወራት ተከናወነና ተአምር በሚመስል ፍጥነት ራሴን ሚስቱ ሆኜ አገኘሁት።
ግን የውል ባሌን ከተዋወቅኩ ጀምሮ ልቤን በደስታ ያነሆለለ የፍቅር ጊዜ ትዝ አይለኝም። በፍቅሩ ባልጃጃልም ግጣሜ ግን ነበር። ብቻዬን ነበርኩ ፤ አብሮኝ ሆነ። ኪራይ ቤት ነበርኩ፤ ተሟሙቶ የጨረሰው የማህበር ቤቱ ገባሁ። እግረኛ ነበርኩ፤ ባለመኪና ሆንኩ። በሰላሳ ሶስት አመቴ ሌጣ ነበርኩ፤ ጥንድ ሆንኩ። ሁለት ነበርን፤ አራት ሆንን።
ግን ይሄ ሁሉ ከአበደ ፍቅር ወይ ስሜትና ሽፍደት የተሰራ አይደለም። ከምክንያታዊነት እና ከውሳኔ ሰጪነት ባህሪዬ የመነጨ ትክክለኛ እና ጤናማ ምርጫ ነበር። ትዳሬ ይሄ ነው። ትዳሬ የስሌት እንጂ የስሜት አልነበረም፤ ሆኖም አያውቅም።
ባል እና ሚስትም አባትና እናትም ሆነን ስምንት አመት ሲሞላን ግን ሰላሳ ሰዎች በረዶ የበዛበት ሰላሳ ባልዲ ሙሉ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሱብኝ ይመስል በድንገት ባነንኩ። በድንገት በምክንያታዊነት የሚመራኝ አንጎሌ አንቀላፍቶ በድን ሆኖ የከረመው ልቤ የነቃ ይመስል አይነቁ አነቃቅ ነቃሁ።
ሄኖክን እንደማከብረውና እንደሚያስፈልገኝ እንጂ እንደማላፈቅረው ራእይ በሚመስል ሁኔታ ተከሰተልኝ።
ሄኖክ መጥፎ ወይ ክፉ ወይ ነዝናዛ ባል ሆኖ አይደለም።
እንዲያውም ብዙ ኢትዮጵያዊ ሴቶች ሚዛን ላይ ቢቀመጥ ‹‹ብረት መዝጊያ…›› ብሎም ‹‹የሰጠ›› የሚባል ባል ሊሆን ይችላል። ለምን ቢባል፣ ልጆቹን በስሙ ከማስጠራት አልፎ ጓደኞቼ እንደሚሉት ‹‹እንደ ሴት›› ይንከባከባል። ጡት ማጥባት ሲቀረው ሁሉን አድርጎላቸዋል-ሁሉን ያደርግላቸዋል- ሁሉን ሆኖላቸዋል- ሁሉን ይሆንላቸዋል።
ለምን ቢባል፣ ለፍቶ ባቆመው የማማከር ስራው በወር ከሰላሳ እስከ አርባ ሺህ (የተጣራ) ብር ቤት ይዞ ይመጣል። የሳምንት ቢራውን እና የነዳጁን ሲያስቀር ሁሉን ለእኔ ያስረክባል። የእኔን ከፀጉር ቤት እና ኮስሞቲክስ ወጪ የማታልፍ ገቢን ከቁጥር ይሰርዛል።
ለምን ቢባል፣ ቤት ሰርቷል። መኪና ገዝቷል። ከተራ ባልና ሚስት ንዝንዝ ማገዶ ውጪ ይህ ነው የሚባል እንከን ሳይዝ አብሮኝ ኖሯል።
ያም ሆኖ በአንጎሌ ሳይሆን በልቤ ማሰብ ስጀምር ኑሮዬ ቸከብኝ። ቀለም አጥቶ ነጭና ጥቁር፣ ከበሮ አጥቶ የሃዘን እንጉርጉሮ ሆነብኝ።
ፍቅር ማጣቴ፤ ደግነት እና ጥሩ ባልነቱ ሳይቀር፣ ሁሉ ነገር እንደክብሪት እንጨት ይጭረኝ እና እሳት ያደርገኝ ነበር።
ለአመታት ያልተለወጠው በጊዜ ሰሌዳ የሚያደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴው ያጨሰኝ ጀመር። አንዳንድ ቀን እንኳን እንደሌሎች ወንዶች መሸታ ቤት ማምሸት ሳያምረው በየቀኑ አስራ አንድ ተኩል አናቱ ላይ፣ ከስራ-ወደ-ቤቱ መምጣቱ ያበሳጨኝ ጀመር። እኔ ካልጠየቅኩት ራሱ አስቦ ሲኒማ ቤት ወይ ቲያትር ቤት ስለማይወስደኝ ያበግነኝ ጀመር። እኔ ከምገዛለት ልብስና ጫማ ውጪ ምርጫ ኖሮት-ወጣ ያለ ነገር አሰኝቶት አለመግዛቱ ያናድደኝ ጀመር። ነጋ ጠባ ለቁርስ ፍርፍር መብላቱ፣ አምቦውሃ ከኮካ ጋር ካልሆነ ለብቻው መጠጣት አለመሞከሩ፣ ትኩስ እንጀራን ይጠባበቃል እያለ መማረሩ፣ ጫማውን ድብን አድርጎ ማሰር ባለመቻሉ፣ወክ ስናደርግ አስር ጊዜ ልሰር ብሎ ማጎንበሱ አይነት-ጥቃቅን-ትርጉም አልባ መሰል ነገሮች ከፀሃይ ጎልተው እየታዩኝ ያጨሱኝ ጀመር። ሌላው ቀርቶ ልጆቹን አለቅጥ ማቅበጡ ልክ እንደ ክፉ ሴራ፣ እንደበደል ይቆረቁረኝ፣ በንዴት ያጦፈኝ ጀመር።
ፀባዬ ፍፁም ተለዋውጦ አንዴ አፈር አንዴ ሰው ስሆንበት ወራት ሲሞላ፣ ችሎኝ የነበረው ሄኖክ እያደር ያቄምብኝ፣ እየዋለ ክፉ-ደግ ይነጋገረኝ ጀመር። በእያንዳንዱ ነገር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት፣ በትንሽ-በትልቁ ጥፊና ቡጢ ሲቀር በቃላት መቧቀስ የሰርክ ቀለባችን ሆነ።
በፊትም አልጣመኝ አሁን ደግሞ ይብሱን መረረኝ። አንገሸገሸኝ።
ብቸኛ እረፍትና መሸሸጊያዎቼ ሴት ጓደኞቼ ነበሩ።
ለአመታት እያደር በሚታደስ ፍቅር ሳይሆን በፀና ‹‹የትብብርና መተሳሰብ መንፈስ›› ላይ ቆሞ የነበረው ቤቴ እና ትዳሬ እላዬ ላይ መፍረስ ሲጀምር የማኪያቶ እና እራት-ከ-ወይን-ጋር ጊዜዎቻችን ማወራረጃ የኔና ሄኖክ ወሬ ብቻ ነበር። ቀናት ሲደራረቡ ግን ለችግሬ መፍትሄ ለመወረወር ይሽቀዳደሙ የነበሩት ጓደኞቼ በነገሬ እያደር መባባስ፣ በፀባዬ መለዋወጥ እና ውሳኔ አልባ ክርክሮቼ ወይ በሁሉም ሊሆንም ይችላል ተሰላችተው ‹‹ደሞ-ጀመራት›› ይሉኝ ጀምረዋል።
ግን ዛሬም ከእነዚህ አሰልቺ እና መንታ ከሚመስሉ ቀናት ባንዱ፣ ራሳችንን ማስተናገድ እስክንጀመር በተለመድንበት አንዱ ካፍቴሪያ ተገናኘን።
ማኪያቶው እና ቡናው ቀርቦ ሲያልቅ፣ ‹‹ትላንት ምን እንዳደረገ ታውቃላችሁ?›. ብዬ የዘወትር እሮሮዬን ጀመርኩ
– ደሞ ምን አደረገ…? አለች ብሌን በፍጹም መሰላቸት
ሶስቱንም በለመድኩት አይነት አየት አድርጌ፣
– እኔ ስብሰባ ስላለኝ ሚጣን ከትምህርት ቤት ቀድመህ ሂድና ውሰዳት ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? አልኩ ጮክ ብዬ አሁንም ሁሉንም አፈራርቄ እያየሁ
ሶስቱም ዝም አሉ።
– አትገምቱም? አልኩ ዝምታቸው ቢገባኝም ግልፍ እያለኝ
አሁንም ሶስቱም ፊታቸው ላይ ያለው ስሜት መናገር እየፈለጉ አፋቸው እንደተለጎመ እያሳበቀ ዝም ሲሉ እምባዬ በአይኖቼ እየሞላ በድንገት ቦርሳዬን አንጠልጥዬ ተነሳሁና፣
– ጋይስ…እንደሰለቻችሁ አውቃለሁ…ግን ጓደኞቼ ናችሁ…እንዲህ ልትመረሩብኝ አይገባም ነበር…ግዴለም…ልሂድላችሁ…ኢንጆይ ዩር ታይም…አልኩ ድምፄ እየተንቀጠቀጠ፣ ቃላቴ እየተነባበሩ።
ሁለቱ ባደረግኩት ነገር እንደተረበሹ እያስታወቀባቸው አፍጥጠው ሲያዩኝ ብሌን እጄን ያዘችኝ።
– ቁጭ በይ ሄለን የትም አትሄጂም…! አለችኝ ከየት እንዳመጣችው ባላወቅኩት ጥንካሬ ጎትታ ወደ ወንበሬ እየመለሰችኝ
– ልታወሩኝ ፈቃደኛ ካልሆናችሁ ምን እሰራለሁ? አልኩ እሷን ብቻ እያየሁ
– እኛ አናወራም አላልንም…ግን ስንት ጊዜ አወራን ስለዚህ….?ሚጡን ከትምህርት ቤት አላመጣም አለኝ- ባለፈው ዊኬንድ የት እንደነበር አላውቅም-ከፈለገ ከማንም ጋር ይተኛ- ስኬስ ካረግን 9 ወር አልፎናል- ማውራት አቁመናል- ደባል በሉት ኦልሞስት- እንደዛ ለልጆቹ የሚንሰፈሰፍ ሰውዬ ዛሬ ከኔ ጋር እልህ ተገባብቶ ችላ አላቸው….—-ስንት ጊዜ ነገርሽን ይሄን ሁሉ…ተሳሳትኩ? ብሌን እጄን እንደያዘች ጠየቀች።
አልተሳሳተችም።
ካለችው ውስጥ ቢያንስ እያንዳንዱን ነገር ሁለት ሶስት ጊዜ ለአመት ብዬዋለሁ። በየሳምንቱ ከአመት በላይ ጓደኞቼ ላይ የችግሬን ጭነት አራግፌያለሁ። በየቅዳሜው ከአመት በላይ ተማርሬያለሁ። በየሰባት ቀኑ ከአመት በላይ ትዳሬን የማፍረስ፣ ባሌን የመፍታትን ወሬ እንደ ጥጥ አዳውሬያለሁ። አባዝቻለሁ። ፈትያለሁ። አልፎ አልፎም ለብሼዋለሁ። መቋጨት ግን አቃተኝ።
ወይ መማረሬን አልተውኩ ወይ አልተፋታሁ። ወሬዬ ቋንጣ፣ እኔ ደግሞ አንድ አይነት ዘፈን የሚያሰማ ቴፕ ሆኛለሁ።
አብዝቼዋለሁ። አማርሬያቸዋለሁ።
– ይቅርታ…ልክ ነሽ..ልክ ናችሁ…አብዝቼዋለሁ አልኩ የብሌን እጅ ሳልለቅ በሃፍረት አንገቴን ደፍቼ
– ኖ….ሄሉዬ….አላበዛሽውም…እኛ የምንፈልገው ደስ እንዲልሽ ነው…ማለቴ ብትፈቺም አብረሽ ብንኖሪም…ማለቴ…ሄኖክ ጥሩ ሰው ነው…ችለሽ ብንኖሪ አሪፍ ነበር ግን ካልሆነ ምን ይደረጋል….ብሌን መለሰች።
ቲጂ እና መሲ አንገታቸውን በመስማማት ነቀነቁ።
ሶስቱም ጓደኞቼ አላገቡም። ሶስቱም ጓደኞቼ አልከበዱም። የጋብቻ እና የእናትነትን ጓዝ እና ግሳንግስ አያውቁትም። ሕይወታቸው የራሳቸው ነው። ካሻቸው ይውላሉ። እንዳሻቸው ያድራሉ። ያልጣማቸውን ይተፋሉ። የጣፈጣቸውን ይውጣሉ። ኑሯቸው በቃልኪዳን እና በልጅ አልታሰረም። ከትዳር እግረሙቅ ነፃ ናቸው። ከሃላፊነት ብረት ካቴና ሩቅ ናቸው። ስለዚህ በትዳር ላለች ሴት የመረረ ሁሉ ቶሎ እንደማይተፋ አይረዱም። ሁሉን ነገር ጣጥሎ ውልቅ ማለት አለመቻሉን አይገነዘቡም። የውሳኔዬን መዘግየት ምክንያት አይመትሩም።
ማታ የዘመመው ጎጆዬ ገብቼ ልጆቼን ራት አብልቼ ካስተኛሁ በኋላ በዝምታ እና በብርድ ከተዋጠው ሳሎኔ ቁጭ ብዬ ያልተከፈተ ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጫለሁ።
አራት ሰአት አካባቢ ፣ ዘልአለም የቆየሁ መስሎኝ የደነዘዘ እግሬን እየጎተትኩ አልጋ-ከለየንበት ዘጠኝ ወር ጀምሮ ብቻዬን ወደምተኛበት ክፍል ስሄድ የሳሎኑ በር ተከፈተ። ዞርኩ። ሄኖክ ነው።
ለሳምንታት እንዳደረግኩት ሰላምታም ሳልሰጠው መንገዴን ቀጠልኩ።
መኝታ ቤት ገብቼ በሩን መዝጋት ስጀምር የሰራተኛዋን ስም ጠርቶ እራት ሲጠይቅ ሰማሁ።
ይሄ ኑሮ ነው? ከዚህ ኑሮ ለመነጠል የምፈራው ለምንድነው? ይሄን መፈራረስ የጀመረ ጎጆ ፈፅሜ መደርመስ የምሰጋበት ምክንያት ምንድነው?