ይሄ ኑሮ ነው? ከዚህ ኑሮ ለመነጠል የምፈራው ለምንድነው? ይሄን መፈራረስ የጀመረ ጎጆ ፈፅሜ መደርመስ የምሰጋበት ምክንያት ምንድነው?
በትዳሬ የደስታ ቅንጣት፣ የእርካታ ፍንጣሪ ሳይኖረኝ፣ ይሄ ምሶሶው የተንጋደደ ቤቴ ቢፈርስ አለም እላዬ ላይ የምትፈርስ የሚመስለኝ ስለምን ነው?
ለውሳኔ ምን አውሸለሸለኝ?
ሌሊቱን ሙሉ በእንቅልፍ ፈንታ የፍርሃቴን ሰበባ-ሰበብ ሳሰላስል፣ አንዱን ካንዱ ሳደባልቅ፣ አንዱን ከሌላኛው ስለይ አደርኩ። እላዬ ላይ ነግቶ ጸሃይ ለመውጣት ስትንጠራራ ግን ሁሉ ነገር ፍንትው ብሎ ታየኝ። በዚህ ቀዝቃዛ ትዳር፣ በዚህ በረዶ ቤት፣ በዚህ ሁኔታ የምቆየው በብዙ ፍርሃት ተሰቅፌ ተይዤ ነው።
አንደኛ….ሰው ምን ይለኛል?
ሰው ስል አባዬ እና እማዬ?
አንገቷን የደፋች፣ ድምፅዋ የማይሰማ፣ ለኑሮ መላ ከመምታት ውጪ ዋዛ ፈዛዛ የማታውቅ ሴት ልጅ አሳድገን ዳርን- የልጅ ልጅ አየን ብለው ቤተክርስትያን ደጃፍ እየሄዱ ምስጋና የሚያቀርቡ ወላጆቼን ሄጄ፤ ‹‹ትዳሬን ልበትን ነው› ብላቸው ምን ይሉኛል? ምን ያህልስ ያዝኑብኛል? በምን መጠንስ ያፍሩብኛል?ወሬው እንደ ተስቦ ተዛምቶ ትላንት ሆ ብለው የዳሩኝ ዘመዶቼ፣ ትላንት ማርያም በሽልም ታውጣሽ ብለው ምናምን ይዘው የጎበኙኝ ዘመዶቼ ሲሰሙስ ወላጆቼ ምን ያህል እንደ ጤፍ ያንሱ?
…ሰው ምን ይለኛል? ሰው ስል አለቃዬ አለማምጃቸው ብለው አምጥተዋቸው ከስሬ የሚሰሩ እነዛ ለጋ የቢሮ ልጆች…ስራ ላይ ኮስተር ስልባቸው፣ እንዲህ አይደረግም- ሁለተኛ እንዳትደግሙት ስላቸው ‹‹ይህቺ ደሞ…ባልና ልጆቿን እንኳን ማስተዳደር አቅቷት ተፋታ እኛ ላይ መጥታ ልቆጣጠራችሁ…እምቡር እምቡር ልበል ስትል አይደብራትም እንዴ›› አይሉኝም?
ሰው ብል ልጆቼስ…?እንዲህ ከሚያቀብጥ- ከሚወዳቸው አባታቸው ስለያቸው ለዘልአለም አያቄሙብኝም? ለዘልአለም ከእንጀራ እናትነት በታች አይመድቡኝም? ..በፍቅር ማጣት፣ በሞቀ ቤት ባለማደጋቸው ተንጋደደው አያድጉብኝም? በትምህርታቸው ደደብ፣ በባህሪያቸው ግዴለሽ፣ ከዚያ ደግሞ ወንዱ ልጄ ጭልጥ ያለ ዱርዬ እና ኪስ አውላቂ…ሴቷ ልጄ ማሬ ደግሞ…..(በስመአብ!)
ሁለተኛ….ከሄኖክ ብለያይ ለልጆቹ ብሎ ይሄን ቤት ቢተውልኝ እንኳን፣ ለልጆቹ ብሎ ተቆራጭ ቢያደረግልኝ እንኳን፣ ለልጆቹ ሲል መኪናውን ቢሰጠኝ እንኳን ለልጆቼ እንዴት ብዬ አባት መሆን እችላለሁ? ለእኔስ እንዴት ብዬ ወንድ ሆኜ ቤቴን ማስተዳደር እችላለሁ?
…ከአንጀት እናውራ ከተባለ የዘንድሮ ሴቶች ሊፕስቲክ ተቀብተን፣ ሚኒስከርት አድርገን፣ መኪና እየነዳን ወጥተን ቢሮ ውለን እየገባን፣ የስንቱ አለቃ ሆነን፣ ስንቱን ስብሰባ መርተን፣ ስንቱን ስትራቴጂ አርቅቀን እያፀደቅን ሁሉ ቤት ስንገባ ሴት ነን።
ዛሬም አለም ሲጀምር ዋሻ ውስጥ ቁጭ ብላ እሳት እያነደደች፣ ወጥ እየቀቀቀለች ልጆችን እንደምታሳድግ ያቺ የዋሻ ሴት ወንድ ያስፈልገናል…ግዳይ ጥሎ የሚመጣልን፣ ከክፉ ነገር የሚጠብቀን፣ የሚያስፈራንን የሚያስፈራራልን፣ አለ አይደል…ትንሽ የሚመስለውን ግን ችለን የማናደርገውን ሁሉ የሚያደርግልን ወንድ ያስፈልገናል።
ለምሳሌ እኔ ከሄኖክ ብለይ አምፖል ሲቃጠል ጠረጴዛ ላይ ቆሜ ልቀይር ነው? ሲጀመር ቁመቴ አይደርስም (ለዚህ ብዬ ከፍ ያለ ጠረጴዛ ልገዛ ነው?) ሲቀጥል ኤሌክትሪክ ሞቴ ነው….(ለዚህ ስል አምፖል ቀያሪ ወንድ ሰራተኛ ልቀጥር ነው? ወንድሞቼን አምፖል ጦሽ ብሎ በፈነዳ ቁጥር ልጠራ ነው?) …ከጎረቤት ጋር ብቻዬን ተጣልቼ ብቻዬን ተጫጩሄ ልኖር ነው? መኪና ሲበላሽ ጋራዥ ወስጄ ያልተበላሸውን ነገር በብዙ ብር ላሰራ፣ መኪናዬን አላግባብ ላስበልት ነው? ስጋ ቤት ሄጄ ደህናውን ስጋ ለይቼ ማዘዝ ስለማልችል ቅንጥብጣቢ በ300 ብር ልገዛ ነው? ቤቱን ሽጡና ተካፈሉ ብንባልና ኪራይ ቤት መግባት ቢኖርብኝ ቤት ለመቀየር ኮተቴን ይዤ ሰፈር ሰቀይር ‹‹እኛ ካላወረድን- እኛ ካልጫንን›› ብለው ከሚያስጨንቁኝ የሰፈር ስራ ፈት ዱርዬዎች ጋር ችዬ ልከራከር፣ ችዬ ልደራደር ነው? ነው ወይ?
…በሄኖክ ፍቅር ባልነድም አለም ትልቅ፣ እኔ እና ልጆቼ ግን ትንንሽ ነን…ያለ እርሱ እርዳታ ክምብል ብላ የምትደፋብን አለም ትልቅ እና አስፈሪ ነገር መስላ ትታየኛለች…
ሶስተኛ- ቃል ኪዳኔስ? ሳገባው ሞት እስኪለየን እንጂ ‹‹እንደማልወድህ ተገልፆልኝ ፍቺ እስክጠይቅ›› አላልኩም… በብዙ መመዘኛ ደህና ባል የሚባልን ሰው ‹‹ፍቅር የለኝም›› ብዬ መተው፣ በእግዜር ፊት የገባሁትን ኪዳን እንደዋዛ ማፍረስ ሃጢያት አይሆንም? ራስ ወዳድነት አይደለም? የሚያውቁኝ ሰዎች ሁሉ ደስተኛ እና የረጋ ትዳር እንዳለኝ ነው የሚያውቁት…በሁለት ጤናማ ልጆች የተባረከ፣ በራስ ቤት እና መኪና ላይ የቆመ፣ ከማይጠጣ-ከማይጨቃጨቅ-ከማይማታ ባል ጋር የታነፀ ረጋ ያለ እና ደስተኛ ትዳር እንዳለኝ ነው የሚታየው….ይሄን ሁሉ ነገር ‹‹በፍቅሩ አላበድኩም›› ብሎ እንደ አሮጌ ቁና አውጥቶ መጣል እብደት አይደለም?
ያጋቡን ሽማግሌዎች ፊት ቀርቤ ‹‹በቃኝ አፋቱኝ›› ብል የሚፈጠረውን ትእይንት አሰብኩት…
– በቃኝ አፋቱኝ…እላለሁ እኔ
– ምነው? ምን ተፈጠረ? ትዳር እኮ….(ምናምን ብለው አንድ መፅሃፍ ስለትዳር ውስብስብና ከባድነት፣ ቅዱስነት እና መባረክ ያወሩና) …‹‹ በይ ችግርሽን ሳታፍሪ አፍረጥርጠሸ ተናገሪ›› ይሉኛል…የዚያን ጊዜ አሰላስል አሰላስልና ሌላ ቃል ባጣ፣ ሌላ አቀራረብ ቢነጥፍብኝ ፈርጠም ብዬ….
– አልወደውም…ለባሌ ፍቅር የለኝም ስል አራቱም ሽማግሌዎች የእናቱን ጡት ጠግቦ እንደሚቦርቅ መንፈቅ ያልሞላው ህፃን በሳቅ ሲንፈቀፈቁ፣ ጦሽ ብለው ሲፈነዱ ይታየኛል…
– በይ በይ በይ…እኔንም ልጆቼንም በረሃብ እየቀጣን ነው…በገባ በወጣ ቁጥር አለእረፍት ይደበድበኛል….ብለው የሚያለቅሱ ስንት ሴቶች ጉዳይ አለብን…አልወደውም አልሽ?..ቀውስ! ሃሃሃሃሃ እያሉ ቤቴን ጥለው ሲሄዱ ይታየኛል…
እውነታቸውን ነው…ቀውስ ነኝ…
በዚህ ህዝብ ስሌት፣ ‹ሞት እስኪለየን ድረስ› ያልኩት በደም ፍላት ገድሎኝ ወይ ገድዬው፣ ወይ አቃጥሎ እስኪደፋኝ ወይ አቃጥዬ እስክደፋው አንደማለት ነውና ቀውስ ነኝ….
አራተኛ—እኔስ? አርባዎቹን የጀመረች ፈት እና የሁለት ልጆች እናት ኑሮዋ ምን ይሆናል? ቤቷን ቀጥ አድርጋ ብትይዝ፣ ልጆቿን ውልፍ ዝንፍ ሳትል ብታሳድግ፣ ስራዋ ላይ አለእሷ የለም ብትባል …አለ አይደል…የቤት ሕይወቷ ምን ይመስላል? ከዚህ ወዲህ ወንድ ይፈልጋታል? ፍቅር ይይዛታል? ፈት ሴት እራት ትጋበዛለች? ወይን እንጠጣ ምናምን ትባላለች? ካዲስ ሰው የአልጋ ጨዋታ ትጀምራለች?…..ደስታን ማግኘት ትችላለች? ….በሰላሳዎቹ ያገኘሁትን ደህና ባል በአርባዎቹ ጥዬ ወጥቼ የሚወደኝ ሰው ባጣስ? ሕይወቴ ልጅ ከማሳደግ እና ቤት ከማስተካከል ያለፈ ደስታን ባያውቅስ? አርፌ ብቀመጥ አይሻልም? ደሞ በግልባጩ ሄኒ አንዷን ጡቷ እንደ ቀስት የሾለ፣ መቀመጫዋ በወሊድ ያልረገበ፣ ጭንቅላቷ በሂውማን ሄር ያበደ የሃያ ምናምን አመት ወጣት ሴት ቢያገባስ? እኔ ብቻዬን ስባዝን፣ እኔ ብቻዬን ስቀር፣ ካሁን ባልተሻለ በረዶ ቤት ብቻዬን ሳድር እሱ የሃያ ሁለት አመት ትኩስ ገላን አቅፎ ቢውል-ቢያድርስ?
ውል አልባ የሆነው ሃሳቤ አሁንም ሳይቋጭ፣ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ሳልቆርጥ ነጋ።
እግሬን በማታው አኳሃን እየጎተትኩ መታጠቢያ ቤት ስገባ ሄኖክ ጥርሱን ይፍቃል።
እስኪጨርስ ብዬ መኝታ ቤት ልመለስ ስል ስሜን ሰማሁ። ደነገጥኩ። ጠራኝ? ሄኖክ ከሳምንታት በኋላ ስሜን ከአፉ አወጣ?
-ጠራኸኝ እንዴ? አልኩት በፍፁም ጥርጣሬ ወደ እሱ ዞሬ
– አዎ…. አለ አፉን ያለቀለቀበትን ውሃ ከተፋ በኋላ…
ቀስ ብዬ ተጠጋሁት። ሁሌም እንደሚያደረገው እርጥብ ፊቱን በትንሽዋ ፎጣ ካደረቀ በኋላ ጠጋ አለኝና፤
– ቤት መከራየቴን ልነግርሽ ነው ሄለን…ከእንግዲህ እንዲህ መኖር አልችልም…ልጆቼን አሳድጋለሁ…ዝርዝሩን ማታ በደንብ እናወራለን….ደህና ዋይ…
እንኳን መልስ ለመስጠት ለሚለኝ ነገር አግባብ ያለው የስሜት ምላሽ ለመስጠት ፋታ ሳይሰጠኝ ወደ ክፍሉ በጥድፊያ ሄደ። አነጋገሩም ሆነ አካሄዱ ፍፁም ቁርጠኝነት፣ ፍፁም እርግጠኝነት ነበረበት።
ይሄኔ ነው እሱም እንደኔ ሲብሰለሰል መክረሙን፣ እሱም ለመቁረጥ ሲለካ መሰንበቱን ያወቅኩት።
ልዩነቱ እኔ በዝግታ ዘጠኝ ጊዜ ስለካ እሱ ግን አንድ ጊዜ ቆርጧል።
ጨዋታውን አፍርሷል። ዳቦውን ቆርሷል።
One Comment
found you by chance……….but am getting addicted to your blog.