ቤተሰብ ውስጥ ምስቅልቅል የሚፈጠረው ወላጆች በተፈጥሮ ሞት ኑረትን ሲሰናበቱ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ልጆች በእናት አባት ሕላዌ ወቅት ያልታያቸው የሃብት ክፍፍል ትዝ የሚላቸው ያን ጊዜ በመሆኑ ነው። ብዙ ጊዜ የሃብት ቅርምት ቤተሰብን ባላንጣ ያደርጋል። ከአንድ አብራክ ተከፍለው ከአንድ ማሕጸን በቅለው ክፉ ደግ ያዩ ልጆች በወላጆች ህልፈት ማግስት በውርስ ሰበብ ጦር ይማዘዛሉ።
___
በቀደመ ክብራቸው የዘለቁ ቢዝነሶችን ታውቃላችሁ?። የወላጅን Brand ልጆች ሲያስቀጥሉት ገጥሟችሁ ያውቃል?ሃብታም የምትሉት የሰፈራችሁ ሰው ሲሞት ሃብቱ በልጆቹ ስም ቀጥሏል?
___
ብዙዎቹ ስማቸው ሳይቀር ተረስቷል። አሻራቸውም ደብዝዟል። የቢዝነሱ ምሰሶ ተናግቷላ። ዕድገቱ የሚመሰረትበት ዋና ሃብት ድንቡሎ ሳይጨምር ተበትኗል። ለመከፋፈል የተጉ ልጆች እንደ ክፍፍሉ ዕድሜ ማስቀጠሉ አይሳካላቸውምና አንዳንዶቹ በአዲስ ቢዝነስ ምስረታ፣ ሌሎቹ በተራ ተርታ፣ ቀሪዎቹም በጊዜያዊ ፌሽታ ገንዘቡን በትነው አጨብጭበው ይቀራሉ።
___
ወትሮስ የደረጀን ነገር ማፍረስ ምን ይጠቅማል? መሰረት የያዘን ነገር መናድ ምን ይረባል? እያደጉ መሄድ ሳለ፤ እያከሉ መንጎድ ሳለ።
___
አሁን አሁን የኛን ሃገር ነገር አበክሬ ሳየው ወላጆች በሞቱበት ቤት ውስጥ የተገኘ ቢዝነስ ይመስለኝ ይዟል። ‘ድርሻዬ’ እና ‘ፋንታዬ’ የሚሉ በዙ። አስገራሚው በአያት ድካም የተቋጠረን ጥሪት በራስ ጥረት ሳያደረጁ ‘የኔ ነው’ የማለት ድፍረታቸው ሲሆን መራሩ ሃቅ ግን ለነግ ልጆቻቸው ያለማሰብ ግለኝነታቸው ነው። ይሄ ደግሞ ዛሬን ካለማመን የሚመነጭ ህመም ነው። ክፉ በሽታ!!
•••
ጎበዝ… ከግዙፍ ኪሳራ በኋላ በወይኔ ለመጸጸትም ሆነ ‘በአበራሽ ጠባሳ’ ቀድሞ ለመንቃት ዕድሉ ከእጃችን ነው።
•••
“We must live together as brothers or perish together as fools. ” ~ Martin Luther King
___
ጥሪት – የቆየልህ እውነት፣ ጥረት – የራስ አበርክቶት፣ ጥምረት – የጉድለትህ ሙላት፣ ጥበቃ – ለልጆችህ ጥሪት። ሃገር!!!
___
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!
One Comment
ጠፍተህ ነበር እንኳን በደህና መጣህ