Tidarfelagi.com

ጎባጣው ትዳሬ

በየሳምንቱ ቅዳሜ አንድ መርህ አለኝ ፤ ያገርቤትም ሆነ የውጭ አገር ፖለቲካ ዜና እጦማለሁ፤ ኪነጥበብና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ እጣድና ነፍሴን አለመልማታለሁ፤ በዚህ መሰረት ፥ ቅድም ዩቲዩብ ላይ ስርመሰመስ ቆየሁ።

በቀደም አንድ የሞሮኮ ዜጋ የሆነ ዘፋኝ “ ሊጋባው በየነ” የሚለውን ዘፈን በራሱ ቃና ዘፍኖ አስደምሞኝ ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ ሸገር ውስጥ በስደተኝነት የሚኖር ሶርያዊ ዘፋኝ “ ለዚህ ለዚህማ ምናለኝ አገሬ “ የሚለውን የጌቴ አንላይን ዘፈን ዘፍኖ አስለቀሰኝ።

ወደ ፌስቡክ ተመለስኩ፤ ባለፈው አንዱ “ ላጤ” የሚለውን ግሩፕ እንድቀላቀል መጥርያ ልኮልኝ ነበር ፤ ያለሁበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለመሰለል ፈልጎ ይመስለኛል፤ እኔም ግሩፑን ቀስ ብየ በለሆሳስ እየተራመድኩ ሰለልኩት፤ ፍቅር የተራቡ ” ሆርኒ” ወጣቶች የተደራጁበት ቡድን መሆኑን ደረስኩበት፤ ብዙም ሳይቆይ አንዲት ወይዘሮ ‘ በትዳራችን ጉዳይ እንመካከር “ የሚል ግሩፕ ላይ እንድሳተፍ መጥርያ ሰደደችልኝ ፤ ይሄ ግሩፕ የመጨረሻ ተመቸኝ፤የመጀመርያም ተመቸኝ ። አብዛኞቹ የግሩፑ አባላት ፥ የፍቅር ታሪካቸውን ተርከው ፤ በትዳራቸው ላይ የገጠማቸውን ችግር ዘርዝረው፥ ካንባቢ ምክርና መፍትሄ ያማትራሉ፤ እንሆ እኔም ተሞክሮየን ለማካፈል ወሰንኩ ፥

በውቄ እባላለሁ፤ ከባለቤቴ ጋራ የተገናኘነው ባጋጣሚ ነው፤ በጊዜው እሷ ሚስ ኢትዯጵያ ተብላ በቁንጅና ስትመረጥ እኔ አወዳደሪው ነበርኩ። የመጀመርያዎቹ ሀያ አመታት የትዳር ቆይታችን ጎረቤት የሚያስቀና ነበር ። ከቢሮ ስመጣ በደስታ በፈገግታና በውዝዋዜ ትቀበለኛለች፤ ኮቴን አውልቃ ወደላውንደሪው አፍ እየጨመረች “ ምሳ እስኪደርስ ፤ ክትፎ በቆጮ እየቀማመስክ ቆይ “ ትለኛለች። ከምሳ በሁዋላ ሶፋው ሳፋ እሲከመስል ድረስ ፍቅር እንሰራለን፤

በዙም ሳይቆይ ጸነሰች ፤ ከዘጠኝ ወራት ላልበለጠ ጊዜ በርግዝና ቆየች ። ያለ ብዙ ምጥ ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ ልጃችንም ያለ ብዙ ለቅሶ ተገረዘ ! ልጃቸን በተወለደ በአንድ አመቱ ዶንኪቲዩብ ላይ እየቀረበ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ ምክር መለገስ እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ጀመረ። ሰባት አመት ሲሞላው ካሮጌ ቅጥቅጥ ሚኒባስ ሂሊኮፍተር ሰራ ። አሁን ካዲስ አበባ ብሾፍቱ ራይድ እየሰራበት ይገኛል።

ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለቤቱ ጸባይ መቀየር ጀመረ። የገቢ ምንጯና ለኔ ያላት ፍቅር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤ ለልደቴ ፍልውሃ ያለውን ፓርክ ገዝታ በስጦታ አበረከተችልኝ ።

በዚህ አይነት ሁሉን የሚያስቀና ትዳር ውስጥ እየኖርን እጅግ የሚያሳዝን ነገር ተከሰተ፤ ሄቲ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ ! ታሊባን አፍጋኒስታን መልሶ ተቆጣጠረ፤ ይህ ግን በፍቅራችን ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽኖ አልነበረውም ።
አንባቢ ሆይ !! ትዳራችን ፈረሰ የሚለውን ለመስማት፥ ምክርና ከንፈር መጠጣ ለማዋጣት ሰፍ ብለህ እየጠበቅህ ነውን ? በቃ ሼም የለህም? ለምን የሟርተኞችና የክፉ ታሪክ ናፋቂዎች ግሩፕ አታቋቁምም ?

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...