የሆነ ጊዜ ላይ አንዲት ቆንጅየ ልጅ ፍሬንድ ሪኩየስት ላከችልኝ! በእህትነት ተቀበልኳት ! ትንሽ ቆይቼ እህትነቱን ባንድ እርምጃ ላሳድገው ብየ በማሰብ በኢንቦክስ “ ሰፈርሽ የት ነው? አላማስ አለሽ? ” ምናምን ማለት ጀመርሁ ፤ ጥቂት እንዳወጋሁት ግን በሴት ፎቶ የተጠለለ ወንድ መሆኑን ባነንኩበት፤ ከዚያ በቃ ተውኩትና ተውኩት።
ነገሩ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር ፤ ጥቂት ቆይቶ ሌላ ሰው ( ታናሽ ወንድምየው ይመስለኛል) ተመሳሳይ ፎቶ ገጭ አድርጎ ርኩሰት ማለቴ ሪኩየስት ላከልኝ ! ለጊዜው ብልጭ አለብኝ ! ድርግም እስኪልብኝ ጠበኩና የሚከተለውን መልክት ሰደድሁለት “ ፎቶውን እንኳ ቀይሩልኝ እንጂ ቤተሰብ! ፤ የቁም የተነሳችው ፎቶ የላትም?’
ድምፃዊ ኬኔዲ መንገሻ የሆነ ጊዜ ኢቲቪ የሙዚቃ ቪድዮ ሊቀረፅ መጥቶ ጥሩ ላስተናገደው ዘበኛ ሌዘር ኮቱን አውልቆ ሸለመው ፤ ከሁለት ካሴት በሁላ ወደ ጣቢያው ሲመለስ ተሸላሚው ዘበኛ አሁንም በዘበኛነት እንደ ፀና አገኘው ፤ ጭራሽ ሌዘሩን ዛሬም ገድግዶታል ፤ ኬኔዲ ጠጋ ብሎ ሌዘሩን ባይኑ አጠናው! ክርኑ አካባቢ ትንሽ ከመንተቡ በስተቀር የድሮው ነው፤ ኬኔዲ ፈገግ ብሎ ዘቡሌውን እንዲህ አለው “ ፍሬንድ ! ሌላም ነገር ቀላቅልበት እንጂ”
እናምን ለማለት ነው፤ የስልጡን አገር ሚድያዎች መለያ የተለያዩ ባለሙያዎችን እና ተወዳዳሪ ሀሳቦችን መጋበዝ ነው፤ አንድ ሚድያ ለወቅታዊ ፖለቲካ ተንታኝነት አንድ ሊቅ ይኖረዋል ፤ ለኢኮኖሚ ትንታኔ ሌላ ሰው አለ፤ መረጃ የሚያጣራ ባለሙያ ደግሞ ለየቅል ነው ፤ ባገራችን አንዱ ሰውየ በሁሉም ዘርፍ እንደ ድሮ ካሴት እየተገላበጠ ሲዘፍንብን ይውላል! ‘ ፖለቲካውን ይበትነዋል ! ሃይማኖቱን ይተነትነዋል፤ ኢኮኖሚውንም አይምረው! አንዳንዴ አፈር ፈጭተው ያደጉ ሶስት አብሮ አደጎች አንዱ አወያይ ሁለቱ ተወያይ ሆነው ሚድያ ላይ ይቀርባሉ ፤ሙግት ያቀርቡናል ብለህ ስታስብ ዱላ ቅብብል ይጫወቱልሀል፤ አሁን ፍንትው አድርገህ እንዳስቀመጥከው ! አሁን አንተ እንዳልከው “ እያሉ ይሞጋገሳሉ፤ ትንሽ ለየት ያለ ሀሳብ እሚኖረው አወያዩ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም “ ይሄን ጉዳይ እንዴት ታየዋለህ?” ብሎ ይጠይቅና መልሱን የሚያዳምጥ መስሎ ሌላ ቦታ ይመርሻል ፤ “ ቅድም ከቤት ስወጣ ስቶቩን አጥፍቼው ነበር? “ በሚል ሀሳብ ተጠምዷል።
እኔ በመንፈስ አላምንም የምል ሰው ነበርኩ ፤በቀደምለት አንድ የሙሉ ጊዜ ተንታኝ የሆነ ሰውየ በሁለት ቻናሎች ላይ በተመሳሳይ ሰአት ላይቭ ሲገባ አይቼ መንፈስ መኖሩን አረጋገጥሁ ! የመንግስት ሚድያዎች የመንግስትን ፖሊሲ የሚሞግት ሰው ጋብዙ ! እኛ ፌስቡክ ላይ እምንጭር ሰዎች እኮ ባቅማችን የሚነቁረንንም ኮመንት እናስተናግዳለን! ተቃዋሚዎችም ትንሽ ለየት ያለ ሀሳብ ያለው ሰው ቀላቅሉ፤ እኛም እጃችንን ከፈንድሻው አይናችንን ከቲቪው ስክሪን ላይ ሳንነቅል “ ሸቀሸቀላቸው በገዛ ጦራቸው “ እያልን እናሟሙቅ፤ ዝም ብሎ አንድ ሀሳብ ብቻ እሚቀዳበት ከሆነ ማደያ እንጂ ሚድያ ነው ለማለት ይከብዳል ፤ እየቀላቀልን !