Tidarfelagi.com

‹‹ግን…. ባይሆንስ?››

 

ቴድ ቶክ ማየት በጣም ደስ ይለኝ የለ? ከምሳ ሰአቴ ቀንሼ ነው የማየው…አፌን በምግብ፣ አእምሮዬን ደግሞ በጥሩ የቴድ ቶክ ተናጋሪዎች ታሪክ ስሞላ ፍስሃ ይሰመኛል። በሁለት በኩል መመገብ ነዋ!

ዛሬ ያየሁት የዳያንን ነው። ዳያን ቮን ፈርነስተንበርግ (ስሟ መርዘሙ፣ ደግሞ ማስቸገሩ).. ዳያን እጅግ ስመጥር የፋሽን ዲዛይነር ናት። አለም ላይ አሉ ከሚባሉት አንዷ።

ዳያን ንግግሯ መጀመሪያ አካባቢ ናዚ ጀርመን አይሁዶችን እያደነ በሚገድልበት ጊዜ ወጣት ስለነበረችው አይሁዳዊ እናቷ ታወጋናለች። እንደሌሎቹ አይሁዳዊያን በጀርመኖች ለሞት የታጨችው እናቷ መልካም ነገር ገጥሟት ጀርመንኛ ትንሽ ትንሽ የምትናገር ጠና ያለች ሴት መዋወቋ ሕይወቷን ሊያርፍላት እንደሚችል ተስፋ አደረገችና ተጣበቀችባት። ከእሷ አልለይ አለች። በሄደችበት ሁሉ ትከተላት ጀመር።

በመጨረሻም ለማይቀረው ፍርድ እስረኞቹ ሁሉ ተሰበሰቡና አንድ የጀርመን ወታደር በተራ እየተቀበለ ‹‹አንቺ በግራ፣ አንቺ በቀኝ›› እያለ እንዲሰለፉ ሲደረግ፣ ተስፋ ያደረገችባት ሴት ‹‹አንቺ በቀኝ ተሰለፊ›› ተባለች።

ያቺ ጀመርንኛ ታተርፈኛለች ብላ ያመነችው የዳያን እናትም የወታደሩን ትእዛዝ ሳትጠብቅ ከሴቲቱ ላለመለየት ቶሎ ብላ በቀኝ ተሰለፈች። ወታደሩ ምንም አላላትም። ተዋት። ምን ያደርጋል! እስካሁን ድረስ ብዙ እስረኛ በተባለው መስመር ሲሰለፍና ይሄ ሁሉ ሲከናወን ከፍ ባለ ቦታ ላይ ቁጭ ብሎ በዝምታ የሚቃኘው የወታደሮቹ ሃላፊ ግን ወዲያውኑ የዳያን እናት ጋር መጥቶ በያዘው ጅራፍ ገረፋትና በግራ በኩል እንድትሰለፍ ገፈተራት።

እያንገሸገሻት በስተግራ ተሰለፈች።

ውስጧ በከፍተኛ ጥላቻ ተሞልቶ ቀና ብላ አየችው። ‹‹ለምን እንዲህ ያደርጋል? ቢተወኝ ምናለ….?››ብላ እጅግ ተማርራ ቀና ብላ አየችው። እስከዚያች ቅፅበት በብዙ ስቃይ ብታልፍም ከፈለገችው ሰልፍ አውጥቶ ወደፈራችው ሰልፍ የገፈተራትን ሰው ግን ከማንም በላይ አጥብቃ ጠልታው ቀና ብላ አየችው።

ከዚያ የሆነው ግን ይሄ ነው። እንዲህ እስክትንገሸገሽ የጠላችው ሰው ነው ሕይወቷን ያተረፈው። ለምን? በቀኝ በኩል የተሰለፉት ሰዎች በጋዝ ታፍነው ሊገደሉ የተመረጡና በኋላም ያለቁ ነበሩ።

ዳያን ይሄን ታሪክ ለምን ነገረችን?

አልፍ አልፎ ሁላችንም እንደ ዳያን እናት ባይከፋም የመረጥነው መንገድ ስለተዘጋብን ዓለም ክንብል ብላ የተደፋችብን፣ እጅግ ከባድ ነገር የደረሰብን ይመስለናል።…ግን…ባይሆንስ? ተገፍትረን የያዝነው መንገድ መርጠነው ካጣነው መንገድ የተሻለ ቢሆንስ?

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...