የዚች ጨዋታ መነሻ የሆነኝ የዛሬ ምናምን አመት ያነብኩት “ያረብ ሌሊቶች ” ተረት ነው።
ጋሹ ታታሪና አይናፋር ባላገር ነው። ሲኖር ሲኖር; በስንት መከራ አንዲት ቆንጆ አጭቶ አገባ።
የሰርጉ ቀን ተበልቶ ተጠጥቶ ጭፈራው ደራ። ሚዜዎችና አጃቢዎች ሙሽሮች እንዲጨፍሩ ጋበዙዋቸው። ጋሹ ግብዣውን በስንት መግደርደር ተቀብሎ ይሄን እንቅጥቅጥ ያቀልጠው ጀመር። ሰርገኛው ክብ ሰርቶ የሙሽራውን እስክስታ ባድናቆት ፈዝዞ መመልከት ጀመረ።
እንክሽ እነካ
እንክሽ እነካ
ይህንን ችሎታ- ደብቆት ነው ለካ!
እንክሽ እነካ
አብዮት ካሳነሽ- በጋሹ ተተካ😁
ህዝባዊ አድናቆቱ ብዙ አልቆየም። ድንገት ከሙሽራው ሱሪ ግድም ቀለል ያለ ፍንዳታ ተሰማ። የፍንዳታው መንስኤ በሙሽራው ሆድ ውስጥ ሲብላላ የቆየው 59 በመቶ ናይትሮጂን -21 በመቶ ሃይድሮጅን -9 በመቶ ካርቦን ዳይወክሳይድ -7 በመቶ ሜታን -የእስክስታውን ጫና መቁዋቁዋም አቅቶት አፈትልኮ መውጣቱ ነው።
ሙሽራው ክው አለ። የሙሽሪትም ቆሌ ተገፈፈ
ሰርገኛው ሁላ ሳቁን ከጥቂት ሰከንዶች በላይ ማፈን አልቻለም።
በነጋታው: ጋሹ የፈሱን ሌጋሲ መሸከም ስላልቻለ ሙሽሪቱን ትቶ ከቀየው ተሰደደ። አምስት አመት ሱዳን በስደት ማቀቀ።
ጊዜው እየጨመረ ሲሄድ ያገሩን ናፍቆት አሸነፈው። እናም ለመመለስ ቆረጠ።
ድንበሩን ተሻግሮ ያገሩን ምድር ሲረግጥ እንዲት ሴትዮ የበቆሎ ጥብስ ስትሸጥ አገኛት። ከሴትዮዋ አጠገብ ትንሽ ልጅ ቁጭ ብላ ጠጠር ትጫወታለች።
ጋሹ በቆሎ ገዝቶ ዝምብሎ እንዳይሄድ
“ይቺ ልጅ ስንት አመት ሆናት?” ብሎ ጠየቀ።
ሴትዮይቱ ትንሽ አሰቡና መለሱ-
” አመተምረቱ ትዝ አይለኝም! ብቻ ! ብቻ ሙሽራው ጋሹ በሰርጉ ቀን በፈሳ በሳምንቱ እንደተወለደች ትዝ ይለኛል”
ጋሹ እንደገና ተሰደደ።
እና እኔ እምላችሁ!
የድሜልክ ገድላችሁን -ባንድ ጀንበር ከሚረሳ
ያንዲት ቅፅበት ነውራችሁን -ለዘላለም ከሚያወሳ
ይሰውራችሁ!
3 Comments
አሜን
hi bewketu i am your admirer…i always appreciate the way of seeing things… please keep it up few people are in this world they are living by paying high price for their people….you are one of them but please your thinking about ALMIGHTY GOD should be corrected coz here i am your brother so i have concern for you.
በዕውቀቱ! እንደው በጣም ስለምውደህ አንድ ያረጀች ቪትስ(ሞዴል 0001) ልሸልምህ ይቃጣኛል!፡፡