እንኳን ለአለም መሃኖች ቀን አደረሰን
እንዲህ የሚባል ቀን እንደሌለ አውቃለሁ።
ግን እስከመቸ ሌሎች የደነገጉትን ቀን ብቻ ሳከብር እኖራለሁ ?!
እኔም ቀን ልደንግግ እንጂ
በድሮ ጊዜ ልጅ መውለድ የሴት ዋና ተግባር ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ያኔ ዘጠና ሚሊዮን ገና አልሞላንም ። የተወለደው ሁሉ አይበረክትም። ከፈንጣጣ መቅሰፍት ቢያመልጥ ርሃብ ይገለዋል። ወይ እበላ ሲል ሰይፍ ይበላዋል። ያኔ ልጅ ማለት የርስት ወራሽ ነው። ቦዲጋርድ ነው። ከብልት በስተቀር ሌላ ቋሚ ንብረት ለሌለው ምስኪን ወንድ ተስፋ ነው። ባገራችን፣ ተስፋየ የሚለው ስም መብዛቱ ይህን ያሳያል።
ወላድ የዚህ ሁሉ በረከት አምጭ ሆና ስለምትቆጠር ትወደሳለች። “ወላድ በድባብ ትሂድ “የሚባለው ምርቃት ጥልቅ ትርጉም ነበረው። ድባብ ግዙፍ ቀይ ጃንጥላ ሲሆን ትልልቅ ማእረግ ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚይዙት ነበር።
ባንፃሩ ፤ መካን ሴት ወዮላት ! ልጅ ማምረት አለመቻልዋ በስንፍና ያመጣችው ይመስል ፣ንቀትን ትጠግባለች። “በቅሎ” ተብላ ባሽሙር ትሰደባለች። ባሉዋ ይፈታታል። ባይፈታት እንኳ ሽለ-ሙቅ ሴት ፈልጎ ይደርብባታል።
የድሜዋን ብዙ ክፍል ፣ ፈውስ ፍለጋ ትባዝናለች። በየጠበሉ በየአዋቂው ቤት እየተንከራተተች ጉልበቷንና ጥሪቷን ትበትናለች። አንድ ንፍጣም የመንደር ሀኪም የስርና የቅጠል መሞከርያ ያደርጋታል።
“ለእናትነት የምናዘንበው ቅጥ ያጣ ውዳሴ ከላይ ከላይ ሲታይ ፣ሴትን ማክበር ይመስላል። ግን በደንብ ስትፈትሸው እልም ያለ መድልኦ ነው። ሴቶች በማህፀናቸው ሀሳብ ብቻ ተጠምደው ፣የአእምሮ ፍሬ እንዳያበረክቱ ማዘናጊያ ነው። “ይላል ወዳጄ ምኡዝ። እውነቱን ነው? ወይስ እብደቱን ነው?
ሮዛ ፓርክስ ፣ አዝማሪት ጣዲቄ ፣ እቴጌ ጣይቱ የተለየ ሀሳብ ያፈለቁት ለዚህ ይሆን? ምናልባት፤ የለመድነው በር እስኪዘጋ ድረስ ሌላ በር መኖሩን አናጤንም።
የጎጃሙ ጌታ ራስ ሃይሉ፣ ባንድ ወቅት የመካን ሴቶችን ንብረት መውረስ የሚያስችለው ግፈኛ አዋጅ አውጥቶ ነበር ይባላል። ወላዶች ፣”እንኳን ከዚህ ሰወርከን “አሉ። መካኖችም የመጣውን አሜን ብለው ተቀበሉ።
አንዲት ሴት ግን አልተበገረችም። ራስን እየተከተለች ግፈኛውን አዋጅ እንዲያፈርስ መወትወት ጀመረች።
አንድ ቀን ራስ በበቅሎው ሴትዮዋ በግር ሲሄዱ አንድ ምስኪን ገበሬ ሲያርስ አዩ። ገበሬው፣ አንዲት መሲና ላምና አንድ በሬ ጠምዶ ያርሳል።
ሴትዮዋ ይህንን ስታይ፣ ቀልጠፍ ብላ እንዲህ ገጠመች፤
” እዩ ተመልከቱ የመካንን ጉድ
ጠምደው አረሱባት፤ እንደኔ ባትወልድ”
ራስ ሃይሉ ፣ ግፈኛ ጌታ ቢሆንም ግጥም የማይዘልቀው (ግጥም -ከላ) ሰውነት አልነበረውም። በሴትዮዋ ሀሳብ ልቡ ተነክቶ ላሚቱን ከቀንበሩ አስፈታት። በማግስቱም ግፈኛውን አዋጅ ሻረው።
አሪፍ ሀሳብ ድንጋይ ልብ ያቀልጣል። እናም፣ ዘጠኝ ወር የሚያረግዙ ሴቶችን ስናወድስ፣ በዘጠኝ ሰከንድ የለውጥ ሞተር የሚሆን ሀሳብ የሚያፈልቁ ሴቶችንም አንርሳ።
One Comment
ደስ ይላል እናም፣ ዘጠኝ ወር የሚያረግዙ ሴቶችን ስናወድስ፣ በዘጠኝ ሰከንድ የለውጥ ሞተር የሚሆን ሀሳብ የሚያፈልቁ ሴቶችንም አንርሳ።