ከታናሽ ወንድሜ ጋር በዲግሪ ፕሮግራም ተምሮ የተመረቀውን ዳንኤል የኮብልስቶን ስራን ሲያስተባብር አግኘሁት።
ሻይ ይዘን ስለ የተማሩ ኮብልስቶን ጠራቢ እና ደርዳሪዎች ተብሎ ተብሎ የተተወውን ክርክር እንደ አዲስ አደረግን።
ዳንኤል ‹‹ ስራ አጥተን ቤት ቁጭ ከምንል ገንዘብ እስካገኘን ብንሰራ ምናለ?›› ብሎ ነገሩን ስራ ከመናቅ እና ካለመናቅ ጋር አጣብቆት ብዙ ሞገተኝ።
“ስራ ገንዘብ ማግኛ ነው። ይሄ ደግሞ ገንዘብ ይከፍላል ። ሃጥያቱ ምንድነው?” ብሎ ተከራከረኝ።
ዳንኤል ልክ ነው።
ድህነት መለዮ ልብሳችን በሆነበት ሀገር ገንዘብ የሚያስገኝ ነገር ሁሉ እንደ ስኬት እንደሚቆጠር ግልፅ ነው።
ምክንያቱም ገንዘብ እህል ይሆናል።
ምክንያቱም ገንዘብ ቤት ኪራይ ይከፍላል።
ምክንያቱም ገንዘብ የታክሲ ይሆናል።
ያን ያህል ቀላል ነው።
ይገባኛል።
የኔ ችግር ከአጠቃላይ ክስረቱ ጋር ነው።
የኔ ችግር እነዚህ ልጆች ለአመታት‹‹ ሲማሩ እና ሲመራመሩ‹‹ ከርመው ያለተማረ እና ያልተመራመረ ሰው ሊሰራው በሚችለው ከዚያም በላይ ሊሰራው በሚገባው ስራ ላይ መሰማራታቸው…የእነዚያን ሰዎች የስራ እድል ከማጣበባቸው ነው።
ለኔ ይሄ ክስረት ነው።
ሰለዚህ የመንግስት ሚዲያዎቻችን እነዚህ ልጆች የምርቃት ሱፋቸውን አውልቀው በስራ ቱታ ድንጋይ ሲፈልጡ መዋላቸው እንደታላቅ ስኬት ሲያቀርቡት አይባኝም።
“በስራ ክቡር ነው” መልካም አባባል ልሽቀታችንን ሲደብቁት ደስ አይለኝም።
ችግሬ ከልጆቹ መስራት አይደለም።
ከነገሩ አቀራረብ እና አረዳድ ነው።
ስራቸው ልጆቹን ሊያሳፍር ባይገባም እንደ ሀገር ግን ሊያኮራን የሚገባ ነገር አይደለም።
ምክንያቱም ልጆቹ ዲግሪ ለማግኘት ብዙ ከፍለዋል።
ሀገሪቷም ካላት ትንሽ ብዙ ከፍላለች ።
…እና በረጅሙ ስናስበው ፣ ዛሬን በልተው ቢያድሩም የትምህርት ስርአታችን ክስረት ባንዲራዎች ናቸው።
ዛሬ ትምህርት ላይ ላሉ ማበረታቻ ሳይሆኑ ማስጠንቀቂያ ናቸው።
ያልተማረ ሰው ሊሰራ የሚችለውን ስራ ተምረው ስለሚሰሩ በልተው ቢያድሩም ለሃገር ውድቀቶች ናቸው።
ግን የነሱ ጥፋት አይደለም።
መብላት አለባቸው።
መኖር አለባቸው።
ሰለዚህ ወደ ገንዘብ የሚለወጥ እውቀት ልንሰጣቸው ስላልቻልን ወደ ገንዘብ የሚለወጥ ጉልበታቸውን ተጠቀሙ።
በዚህ ደግሞ ልናፍር እንጂ ልንኩራራ የሚገባ አይመስለኝም።