Tidarfelagi.com

ገነት ይቅርብኝ

“እንለያይ?” ስላት አስቀድማ ውብ ከንፈሮቿን ገለጥ አድርጋ የሲኦል መቀመቅ ውስጥ ሰምጬ እንኳን ቢሆን ንዳዱን የሚያዘነጋኝን ጥርሶቿን አሳየችኝ። ቀጥሎ ግን የእውነቴን መሆኑን ስታውቅ ሳሳዝናት ደፍሬ ማየት የሚከብደኝ ውብ ዓይኗ ደፈራረሰ።

“ማለት?” አለችኝ በተሰበረ እና የአፏን በር ለቆ ለመውጣት በሚቅለሰለስ ድምፅ

“እንድንለያይ እፈልጋለሁ። ከዚህ በላይ አብሬሽ መሆን አልችልም።” ብዬ መለስኩላት። የምትጠይቀኝ ወይም ማለት ያለባት ነገር የጠፋባት መሰለች። በተቀመጥኩበት መጥታ እግሬ ስር በዛለ ጉልበት ተቀመጠች።

“አልገባኝም። ምንድነው የተፈጠረው? ለምንድነው የምንለያየው? ሌላ ሴት…?” ስላሰበችው እንኳን የዘገነናት ነው የሚመስለው። እጇን አፏ ላይ ጭና አፈጠጠችብኝ።

“አይደለም። በፍፁም አይደለም ውዴ! በፍፁም!” ያልኳት የእውነቴን ነው።

“እሺ ምንድነው? እና ምን ተፈጠረ? በመሃከላችን አንዳች ቅራኔ ሳይፈጠር የምንለያየው ለምንድነው? ያልነገርከኝ ያጎደልኩብህ ነገር አለ?” አቀማመጧ፣ አጠያየቋ እናም የፊቷ የልመና ገፅ አንጀት ያላውሳል።

“አየሽ እሱ ነው ችግሩ። ምንም ነገር አጉድለሽብኝ አታውቂም። ምንም ነገር!! በሁሉም ነገር ሙሉ እና ልክ ነሽ።” ስላት ፊቷ በግራ መጋባት ተመሳቀለ።

“እና? እና ችግሩ ምንድነው? ምንም ያለማጉደሌ ጥሩ ነገር አይደል እንዴ?” አለችኝ

“ጥሩ ሊሆን ይችላል። ልክ ግን አይመስለኝም።” እያልኳት እንዴት ባስረዳት እንደሚገባት ማስላት ጀመርኩ።

ለእርሷ ማስረዳቱ ቢጨንቀኝም በትክክል ምክኒያቴ ይሄ ነው። የእርሷ ሰውኛ የማይመስል ፍፁምና!!!ባወቅኳት በመጀመሪያዎቹ ወራት በሚያፈዝ ውበቷ ፣ በማይሰለች ጨዋታዋ፣ በሚደንቅ ታታሪነቷ፣ በበዛ እንክብካቤዋ እና ፍቅሯ ስለሰጠምኩ አብራኝ እንድትኖር ከመስገብገቤ ሌላ የታየኝ ነገር አልነበረም። አብረን መኖር ከጀመርን በኋላ እያንዳንዱ ነገሯ በጥንቃቄ የተሞላ እና ልክ ብቻ መሆኑ የሚጨንቅ ነገር እንዳለው እየገባኝ መጣ። ሁሌም ልክ ናት! ሁሌም ጥንቅቅ ያለች እንከን አልባ ናት!

የሰው ልጅ ጆሮው ያምራል? የእግሯ ትንሽዬ ጣት ጥፍር ሳይቀር የእጅ ጣት የመሰለ ነው። ‘ይሄ ነገሯ ትንሽዬ ይቀረዋል’ የሚባል ምንም ቦታ የላትም። በቃ ከጎኔ ይዣት ስወጣ ታዋቂ የሆንኩ የምታስመስለኝ እንከን አልባ ውብ ናት። አንድም ቀን በእርሷ ምክንያት ሳንግባባ ቀርተን አናውቅም። ሁሌም የማጠፋው እኔ ነኝ። ከማጥፋቴ በላይ ደግሞ ምንም እንዳላደረግኩኝ ማስመሰሏ ያሳብደኛል። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ የምለብሰውን ልብስ ተኩሳ፣ ቁርስ አብስላ፣ የምይዛቸውን ነገሮች እንዳልረሳ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጣ፣ ተጣጥባና ተውባ ትቀሰቅሰኛለች። እንዴት እንደምታሳብደኝ ታውቅበታለች። ሁሌም እርግጠኛ መሆን የምትፈልገው እኔ መደሰቴን ብቻ ነው። ባላስደስታት እንኳን አትበሳጭብኝም። በደስተኛ ገፅታ ከጎኔ ትነሳለች። ወደስራ ልንሄድ ተሰናድተን ስንጨርስ እርሷም ቤቱም ጥንቅቅ ብለው ፀድተው አልቀዋል። ሁሌም እንዴት እንደሚሳካላት አይገባኝም። አንዲትም ቀን ግን ዝንፍ ያለ ነገር አይኖርም። ስራ በዝቶብኝ ምሳ ሰዓት መደወሌን ብረሳው እርሷ ከኔ በባሰ የሚወጥራት ስራ እያላት ሰዓቷን ሳታሳልፍ ትደውላለች።

እራት ልጋብዛት ቀጥሪያት በምክንያት ብሰርዘው አታኮርፍም። እቤት በጊዜ እገባለሁ ብያት እራት አሰናድታ እና ሻማዎች አብርታ ስትጠብቀኝ ደውዬ ከጓደኞቼ ጋር አመሻለሁ ስላት ‘እየጠበቅኩህ ነው።’ አትለኝም። ግን ሻማው በርቶ ቢያልቅ እንኳ ሶፋው ላይ ኩርምት ብላ ትጠብቀኛለች። ሞቅ ብሎኝ ስገባ የፊቷ ፀዳል አይቀንስም። ምንም እንዳላደረግኩ በፍቅር ትስመኛለች። አውልቄ የማዝረከርካቸውን ልብሶቼንና ጫማዬን በቦታቸው ታስቀምጣለች። በጊዜ ገብቼ ያበሰለችልኝን እራት እያጎረስኳት እንዳሳለፍናቸው ምሽቶች ሁሉ ጣፋጭ ፍቅር እንሰራለን። እሷ ከስራዋ ፣ ከእኔና ከቤቷ ሌላ ደስታን የምትፈልግበት ቦታ አትሻም። እኔ በስራ ሰበብ ወይ ከጓደኞቼ ጋር አልያም መጠጣት ፈልጌ ባመሽ ግን ለምን? አትልም። የተለየ ፊትም አታሳየኝም። እርሷ የወር ደመወዟን እቤቷ የሚያስፈልገንን ነገር አሟልታ የተረፋትን ስትቆጥብ እኔ ጓደኞቼን በመጋበዝ ወይ በሌላ ሰበብ ብሬን አጋምሼ ስገባ ምክንያቱን እንኳን መስማት አትፈልግም። ‘ፍቅርዬ በቂ ገንዘብ አለን አትጨናነቅ!’ ትለኛለች። አንዴ ወይ ሁለቴ ወይ ጥቂት ጊዜ አይደለም። ሁሌም እንደዚህ ናት። እናም ይጨንቃል።

ሰው እንዴት አንድ ቀን ስህተት አይገኝበትም? እሺ ቢያንስ እንዴት አይቆጣም? ከሰው ጋር ሳይሆን ከሆነ መለኮታዊ ፍጡር ጋር እየኖርኩ ይመስለኛል። እያስመሰለች እንደሆነ አስቤ ሆነ ብዬ ስህተት ላገኝባት ፈልጌ አውቃለሁ። በፍፁም አላገኘሁም። እናም የእርሷ ፍፅምና የእኔን ነጥብ ስህተት እንኳን ታደምቅብኛለች። በየእለቱ ራሴን መኮነን ሊያፈነዳኝ ነው። የእርሷ ንፅህና ከሚታየኝ በላይ የእኔ ቆሻሻ ይገዝፋል። እንደርሷ ለመሆን ሞክሬ አውቃለሁ። ግን አልቻልኩም። ሰው ላለመሆን እየተፍጨረጨርኩ እንደሆነ ይሰማኝና እተወዋለሁ። በአፏ ቃል ባትናገርም በድርጊቷ ታፀፅተኛለች። በፅድቋ ሀጢያቴን ትከምረዋለች። እሷ ስትገዝፍ እኔ አንሳለሁ። ሳስበው የሰማዩ ገነት ፍቅረኛዬን ይመስለኛል። ፅድቅ ብቻ!! በእርግጥ ለነፍስ ፍፅምና ላይጨንቃት ይችላል። ለስጋዬ ግን ኡኡኡኡኡ

“የሰው ልጅ ልክ ለመሆን ይማራል እንጂ እንዴት ለመሳሳት ይማራል? እሺ አንተን ከመለሰልኝ ዝርክርክ መሆን ካለብኝ እሆናለሁ። አንድ በአንድ ንገረኝ ምን ልተው?” አለችኝ ለምን መለያየት እንደፈለግኩ ስነግራት።

እዩዋት በናታችሁ? እዩዋት ስታሳንሰኝ!

★★★ ጨርሰናል !! ★★★

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...