Tidarfelagi.com

ገበያ

እኔ እምቆይበት ከተማ ውስጥ Walmart የሚባል ገበያ አለ፤ ፋሲካ አንድ ሳምንት ሲቀረው ባለንጀራየ በየነ የፈረንጅ ደገኞች ፥ በግ ወደ ሚሸጡበት መአዘን ጎራ አለ።
በየነ የአንዱን በግ ጥርስ ገልጦ አየው፤ የበጉ ጥርስ ከዳር እስከዳር በሽቦ(ብራስ)ታስሩዋል፤
“የየት አገር በግ ነው”?
ባለበጉ ፈረንጅ በበጉ ላት ላይ የተለጠፈውን ስቲከር ካነበበ በሁዋላ ‘የቦስተን በግ ነው” ሲል መለሰ።

‘Grass-fed ነው? ፤ ሳር እየበላ ያደገ ነው?”
ፈረንጁ በቀኝ እጁ በያዘው የታጠፈ አለንጋ የግራ መዳፉን እየጠበጠበ፥ በየነን ትንሽ ከገላመጠው በሁዋላ፤
“ሰውየ ፤ ጤነኛ ነህ ግን? ሳር እዚህ አገር መናፈሻ እንጂ መኖ ሆኖ አያውቅም ፤ ይሄ በግ ቦቆሎ፥ ካሮት ፥ እና ጥቅል ጎመን እየተመገበ ያደገ ነው፤ በሶስት ቀን አንዴ ቫይታሚን ይውጣል፤ ገላውን በሻምፑ ይታጠባል፤ አራቱን ብብቶቹን ዶዶራንት ይቀባል! በዚያ ላይ ” እስከ ፋሲካ የሚቆይ ‘ላይፍ ኢንሹራንስ’ አለው ፤ ጄሎ የምትለብሰውን ጠጉራም ካቦርት አይተኸዋል? ከዚህ በግ ላይ የተሸለተ ነው”

በየነ ፤በጉን ገዝቶ፤” ኩሊ ኩሊ” ብሎ ተጣርቶ ፤ ባንድ የስፓኒሽ ኩሊ አስጭኖ ሲወጣ እግረመንገዱን፤ በበሬው ገበያ በኩል አለፈ፤ ድንገት የአንዱን ሰንጋ ቀልቡን ስቦት ርምጃውን ገታ አደረገ፤
“ አሪፍ ሰንጋ ይመስላል፤ ግን ሻኛው አይታየኝም ፤ ሻኛው ከኔ ነው?’
ባለስንጋው ማብራሪያ መስጠት ጀመረ፤
“የኢዶኒዥያ ሰንጋ ፤ በትርፍ ጊዜው የጭነት አለገልግሎት ስለሚሰጥ ሻኛው ይሙዋሙዋል ፤ ለዚያ ነው “
“ያለ ሻኛማ ይሆንም” በዩ ተቃወመ፤
“ይሄን ያህል ሻኛ ካማረህ ግመል ለምን አትገዛም፤ ?፤ የፊትና የሁዋላ ሻኛ እያማረጥህ ትበላለህ”
“እኔ የበሬ ነዋ እምፈልገው?”
“ችግር የለውም!” አለ ሻጩ” አንድ ሳምንት ከሰጠኸን ከፍሪምባው ላይ ስጋ ወስደን፤ የሻኛ ንቅለ- ተከላ ልናደርግበት እንችላለን”

በዐሉ ፤የሰላም የፍቅርና የተድላ እንዲሆንላችሁ ተመኘሁ

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...