Tidarfelagi.com

ድንኩዋን ሰባሪው

 

አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው። የቸሬ ድህነት ግን ወለል እንኩዋ የለውም። ከቸሬ ጋር ስትወዳደር ድህነት ራሷ ሀብታም ናት። እኔ ግን ምናለ መፈላሰፉን ትቼ ወደ ታሪኩ ብገባ !

በቀደምለት ቸሬ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን በጉልበትና በፀሎት ለማገዝ ወደ ስፍራው ሄዶ ነበር። በስፍራው : ከፊቱ እንደ ባለሙያ ሴት ልቃቂት የተበተኑን ድንኳኖች ሲቆጥር : አንዲት የርዳታ አስተባባሪ ሴትዮ አይታው” አይዞህ ሁሉም ጥሩ ይሆናል” እያለች ወደ አንድ ድንኳን ውስጥ አስገባችው። ምን የመሰለ ፍራሽና ብርድልብስ አስታቀፈችው። ቸሬ እንዲህ አይነት ነገር በህይወቱ ዘመኑ አይቶ ስለማያውቅ ብርድልብሱን እንደታቀፈ የርዳታ አስተባባሪዋን ሴትዮ ትከሻ ተደግፎ ላምስት ደቂቃ እንቅልፍ ወሰደው። ጥቂት ቆያይታ ሴትዮዋ ላንድ ወር የሚበቃ ሩዝ እና ማኮሮኒ ሰፈረችለት።

” ይሄ ላንድ ወር የሚሆንህ የኪስ ገንዘብ ነው ” ብላ አምስት ሺህ ብር በእጁ ላይ ስታስቀምጥለትማ በቁሙ ሊወድቅ ምንም አልቀረው። የድንኳኑን ተራዳ ተደግፎ ለትንሽ
ከመውደቅ ተረፈ። ቸሬ “የኪስ ገንዘብ ” ማለት ምን እንደነበር ለማስታወስ አስር ደቂቃ ማሰብ አስፈልጎታል: :

የሚያስቅምጠው ገንዘብ ኖሮት ስለማያውቅ ኪስ ያለው ሱሪ መልብስ ካቆመ ራሱ ብዙ ጊዜ ሆኖታል።

በማግስቱ ቁርሱን በልቶ ጋደም ባለበት ዶክተር አብይ እና ለማ መገርሳ መጥተው ጎበኙት። ጥቂት ቆይቶ ፍልፍሉ ገብቶ ቀልድ አውርቶለት ራሱ ስቆ ሄደ። ጎሳየ ተስፋየም ብቅ ብሎ ትንሽ አንጎራጉሮለት በርታ ብሎት ተመለሰ። ቸሬ ይሄ ነገርማ በህልሜ ሳይሆን አይቀርም ብሎ የገዛ ፊትን በጥፊ እየመታ ለመንቃት ሞከረ።

ቸሬ : በህልሜ ነው በውኔ በሚያሰኝ ምቾት ውስጥ አንድ ወር ያክል እንደቆየ ተፈናቃዮችን ወደ መጡበት የመመለስ ስራ ተጀመረ።

አንድ ቀን የቲቪ ጋዜጠኛ ወደ ቸሬ ድንኩዋኑ ገብቶ:-

“መፈናቀልን እንዴት ትገልፀዋለህ?”

“ለኔ መፈናቀል ማለት ” አለ ቸሬ በትካዜ” ለኔ መፈናቀል ማለት ከዚህ ድንኩዋን ወጥቶ ወደ ቤት መመለስ ነው”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...