Tidarfelagi.com

ድንቁርና ይጥፋ ዕውቀት ይስፋ

“~~~ድንቁርና ይጥፋ ዕውቀት ይስፋ
ይህ ነው የኢትዮጲያ ተስፋ~~~~ “

ማንኛውም ሰው እናት ሀገሩ ባስገኘችለት ፣ ሊቃውንት አባቶች አዘጋጅተው ባቆዩለት ፊደል ተምሮ ማንበብና መፃፍ ተቀዳሚ ተግባሩ ይሆናል። መምህራንም የፊደላትን ሥነ ባህርይ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። ይህም በየጊዜው ለሚነሳው ብሔራዊ ትውልድ እራሱን ክዶ ሌላውን ሆኖ እንዳይገኝ ወይም “መነሻውን አያውቅ መድረሻውን ይናፍቃል “ከመሰኘት ነፃ ያደርገዋል። ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ

በመሠረቱ ታሪክ ቀድሞ የመገኘት እድል በገጠመው ትውልድ ተዘጋጅቶ ለሀገር ባለቤትና ለዜግነት ማንነት የባህልና የቅርስ መታወቂያነት ማረጋገጫና ማስረጃ በመሆን በታማኝነት ዝክረ ነገርነቱ ለቀጣዩ ትውልድ ከዘመን ከታሪክ መነሻነቱና ደጀንነቱ ጋር ዘመን የሚሸጋገር ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የሀገርና የወገን ታላቅ ቅርስ ነው ።
በመሆኑም ቀደምት አባቶቻችን ያላቸውን እውቀት በመጠቀም አንደኛ አናባቢ የማያስፈልገው ፊደል ቀርፀውና ዜሮ የሌለው ቁጥር ፈልስፈው በሥነ ጽሑፍ አስቀምጠውልናል ። ሁለተኛው በአለም ላይ የሌለ ልዩ የሆነ የቅኔ ጎዳናን ቀይሰው መስመር አስይዘውልናል። ሶስተኛው በግዕዝ በአራራይና በዕዝል(በሀገርኛ ኖታ) የዜማ ስልት አቁመው ኢትዮጲያን ለነዚህ ሁሉ ሀብታት ባለቤትነት አብቅተውልናል። በአለም ሀሳባቸውን በሥነ ጽሑፍ የሚገልዝፁበት ፊደል ካላቸው ጥቂት ሀገራት አንዷ ሆና እንድትቆጠር አብቅተዋል። በመሆኑም ልቡናቸው በሀገር ፍቅር በወገን የክብር መንፈስ እሳት እየተለኮሰ ለኛ ለኢትዮጲያውያን የሥነ ጽሑፍና የታሪክ ቅርስ ያበረከቱ አባቶቻችን ሊቃውንት እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል።

ኢትዮጲያ ምንም ከላይ የጠቀስናቸው ሁሉ ባለቤት ብትሆንም ለብዙ አመታት የፊደላት ቅርጽና የሥነ ጽሑፍ እውቅና የሚንፀባረቀው በቤተ መንግስት ግፋ ሲልም በአንድአንድ ከተሞች ነበር ተስፋፍቶ የሚገኘው ። ነገር ግን ይህን ችግር ተመልክተው ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ከእፅዋት ቀለም አንጥረው ፣ ከሸንበቆ ብዕር ቀርፀው የፍየል ቆዳ ፍቀው አለስልሰው በመፃፍ “…ሀ-ሁ…ዕውቀት ይስፋ ድንቁርና ይጥፋ ይህ ነው የኢትዮጲያ ተስፋ…” የሚለውን መፈክር ተጠቅመው ወደ ማህበረሰቡ ዘለቁ።

የታሪክ አደራቸውን ተቀብለው ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ በትክክል አደራቸውን ጠብቀው የዜግነት ግዴታቸውን ከተወጡ ባለሞያዋች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ “ድንቁርና ይጥፋ ዕውቀት ይስፋ ፣ ይህ ነው የኢትዮጲያ ተስፋ” ብለው በማወጅ ታላቁን ጠላታችንን ድንቁርናን ለማጥፋት በመላው ኢትዮጲያ የፊደል ሰራዊት ሲያዘምቱ ኖረዋል። ልዩ ልዩ የፀሎት መፃህፍትን በማዘጋጀት ከማቅረባቸውም በላይ የኢትዮጲያ ሥመ ጽሑፍ ባህል ለአለም ለማስተዋወቅ
የጣሩም ታላቅ ሰው ነበሩ።
ለሀገር ያገለገለ ለነፃነቱ የታገለ ሰው ስምና ዝናው ታሪኩ በዘመን ብዛት ተሸፍኖና ተዘንግቶ የሚቀር ሳይሆን ከዘመን እስከ ዘመን በጉልህ ድምፅ ሲያስገመግም ይኖራልና ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ስምና ስራ ምንግዜም በየትውልዱ ህሊና የሚጠፋ አይደለም።
“ሀ…ሁ ድንቁርና ይጥፋ ዕውቀት ይስፋ ፣ ይህ ነው የኢትዮጲያ ተስፋ ”

፨ ንባብ~~~ያልተዘመረላቸው ቅፅ ፩.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...