የመሲሁ ስቅየት
ግርፊያ ስቅላቱ
አምላክ ነኝ ስላለ
በድምቀት ተሳለ
የኛንስ ስቅላት ማነው ያስተዋለ?
ተመልካች ጠፍቶ እንጂ ዐይን የሚለግሰን
መውረድ እንደናፈቅን እኛም መስቀል ላይ ነን::
ዘውትር ዱላ እና አሳር
ዘውትር ችንካር ሚስማር
የሚገዘግዘን የሚጠዘጥዘን
እኛም ክርስቶስ ነን
እኔም ታዝቤያለሁ…
ሺ ዱላ ሺ ግርፊያ
ጀርባችን ላይ ያርፋል
“ስቀለው” የሚል ድምፅ በጆሮዬ ያልፋል
ባደባባይ መሀል ልብሳችን ተገፎ
ሲያዙት በሚታዘዝ ጀርባችን ተገርፎ
ስንቶች ተሳለቁ; ስንቶቹ ተፉብን
ዕርቃን ገላችን ፊት ዕጣ ተጣለብን
ዕዩት ይህን ሀገር ይህን ጎለጎታ
ስንት ዓይነት ሰሪ እጅ በምስማር ተመታ
ዕዩት ይህን ሀገር አጉል ተቸንክሯል
“ለምን ተውከኝ” ብሎ ጌታውን ይጣራል
ወዲያ ቄሳር አለ
ሰቃይ እየላከ ስንቱን የሰቀለ
ከወዲህ ሰቆቃ
ዘመነ-ቄሳሩ ጨርሶ እስኪያበቃ!
እዩን መስቀሉ ላይ
ተሸክመን ስቃይ
አታምኑ እንደሁ ዳሱ
ከእጃችሁ አይርቅም; ሚስማር ሰራሽ ብሱ!
ቄሳራዊ መስቀል እየቀያየርን
ኤሎሄ ያላዳነን
የተቸነከርን
እኛም ክርስቶስ ነን!
የዳግም ትንሳኤ ተስፋ ስናበቅል
ሌላኛው ይመጣል ተክቶ ሚሰቅል
ጩኸት ስቃያችን ሰማይ አልተሰማም
በተስፋ እጦት ጦር ግን;
ልባችን አልደማም::
መሰቀያችንን መስቀል ተሸክመን
ተራራውን መውጣት አጣምኖ ያደከመን
እኛም ክርስቶስ ነን!
ከሸክማችን ላይ ያገዘን ሰው የለም
በታሪክ ክፍላችን ይህ እንግዳ አይደለም
“ተጠማን” ብንልም ውሀ አላጠጡንም
የቄሳር ወዳጆች; ቢያውቁም አያውቁንም!
ይሄ ጊዜ እስኪያልፍ
ታሪካችን ይፃፍ
መስቀል የለመዱ በሰልፍ የሚነዱን
እኛም ክርስቶስ ነን
አዝነው እስኪያወርዱን!