እመሃል ላይ ተገምሰው ማዶ ለማዶ የሚያተያዩን ሰባራ ድልድዮች እየበዙ ነው… አንዳንዶቹን ሆን ብለን ሰብረናቸዋል… አንዳንዶቹ በሌሎች ሰንኮፎቻችን ዳፋ ተሰብረዋል… ሌሎቹን ግን መሰበራቸውን እንኳ አልተረዳንም…
~
አንዳንዶች የሚሰብሩትን ድልድይ ፋይዳ በወቅት ስሜታቸው ትኩሳት ውስጥ ብቻ ስለሚመዝኑ የሰባሪነት ወኔ እንጂ የአስተዋይነት ስክነት ከቶም አይታይባቸውም… ሰብረው መሄዳቸውን እንጂ መመለሻ ማጣታቸውን አያስተውሉም…
~
ጎበዝ… ጊዜው የተሰበሩ ግንኙነቶችን የምንጠግንበት እንጂ ሌሎች የአብሮ መኖር ምልክት የሆኑ ድልድዮችን የምንሰብርበት አይደለም… አዲስ ድልድይ ባትሰራ እንኳ ነባር ድልድይ አለማፍረስ ደግ ነገር ነው…
~
ድልድዮቻችንን እንያቸው እስኪ… ተጎምደው የቆዩንም ሆነ በእኛው የተገመደሉት ቅን ልቦቻችንን ይናፍቃሉ… እስኪ መሰረታቸው ጠንካራ የሆኑትን ባሉበት እንጠግናቸው… የስብራታቸው ዳፋ ለሕልውናቸው ስጋት ከመሰለን ደግሞ በአዲስ መልክ እንስራቸው… ደግመው የማይሰሩትን ማፍረስ ግን መመለሻ ያሳጣል… የሰበሩትን ዳና ማጥፋት የልጆችን ወኔ ይሰልባል…
~
ግንባታ ላይ እንጠመድ ጎበዝ… የቤተሰብን ሰባራ እንጠግን፣ የሕብረተሰብን ሰባራ እንጠግን፣ የጓደኝነትን ሰባራ እንጠግን… የትውልድን ሰባራ እንጠግን፣ የግለሰብን ሰባራ እንጠግን፣ የተቋምን ሰባራ እንጠግን፣ የጉርብትና ሰባራ እንጠግን፣ የአስተሳሰብን ሰባራ እንጠግን፣ የልጅነትን ሰባራ እንጠግን፣ የወጣትነትን ሰባራ እንጠግን፣ የአዛውንትነትን ሰባራ እንጠግን…
~
አዎን ግንባታ ላይ እንጠመድ… የምድሪቱ ሰባራ መጠገን ይሻል፣ የሰላም ሰባራ መጠገን ይሻል፣ የአንድነት ሰባራ መጠገን ይሻል፣ የእውነት ሰባራ መጠገን ይሻል፣ የፍቅር ሰባራ መጠገን ይሻል…
~
ግንባታችን የትናንት ሰንኮፎቻችንን ለማሻገር አይሁን… ውድቀቶቻችንን ለማሻገር አይሁን… እንክርዳዱን ለማሻገር አይሁን… ቂምና ቁርሾ ለማሻገር አይሁን… ያልኖርንበትን ዘመን እንከን ለተለገስነው ዛሬም ሆነ ለምናወርሰው ነገ ለማሻገር አይሁን…
~
ሰባራ ድልድይን ክፉ አሳቢ አልፎ እንዳይገፋን ስንሻ አፈረስነው… ለመልካም መስተጋብር ስንል ዳግም መልሰን ባለበት ገነባነው… የዚህ ዓይነት መልካም ነገራችን ላይ የተጨመረልንን የማጽናት ምስል ያስፈልገናል… የሰባራችንን መሰረት ፈትሸን የጥንካሬ ሃውልታችንን የመገንባት መንፈስ ያሻናል…
~
ክፋትን ለማስረጽ የቀየስነውን አፍርሰን የመልካምነት መሸጋገሪያ የሆነውን እንገንባ… ነባር ማፍረሱን ትተን ለሕልውናው እንትጋ… “Problems cannot be solved at the same level of awareness that created them” _ Albert Einstein
~
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!