“የኢትዮጵያ ምድር አንቺ የደም ጎዳና
መስክሪ አፍ አውጪና”
(ምኒልክ ወስናቸው)
“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ”፤ አዳም ረታ በአብዮቱ ዘመን የነበሩ የአንድ ሰፈር ልጆችን ሕይወትና ዕጣ ፈንታ የሚያሳይበት ትረካ ነው። አዳም፤ የእነዚህን ልጆች እድገትና ጉርምስና፣ የፖለቲካ ንቃትና አሳዛኝ ፍፃሜ በሰባት መንገዶች ወግ ከፋፍሎ ያስነብበናል።
በዚህ ታሪክ ውስጥ አዳም ስለመንገዱ፣ መንገዱን ስለሰሩት የእግር ዳናዎች፣ በመንገዱ ላይ ስለሚጓዙ እግሮች ልዩ አትኩሮት ሰጥቶ ይተርካል። ምናልባትም መንገድ የታሪኩ ዋነኛ አፅም ነው። መንገዶች ግዑዝ መመላለሻዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የገፀባህሪያቱ ሕይወት የተተለመባቸው፣ የልጅነት፣ የፍቅር፣ የአብዮት፣ የሞትና የፀፀት ታሪክ የተመዘገበባቸው ድርሳናት ናቸው።
‘As people, in the course of their everyday lives, make their way by foot around familiar terrain, so its paths, textures and contours, variable through the seasons, are incorporated into their own embodied capacities of movement, awareness and response – or what into Gaston Bachelard calls their ‘muscular consciousness’. But conversely, the pedestrian movements thread a tangled network of personalised trails through the landscape itself. Through walking, in short, landscapes are woven into life, and lives are woven into the landscape in a process that is continuous and never ending.
የመንገደኞች የእግር ጉዞ፤ በምድሪቱ ላይ የተጠላለፈ የዱካ መረብ ያኖራል። በመራመድ ጉዞ ውስጥ ምድርና ሕይወት አብረው ይሸመናሉ።
‘ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ ውስጥ ገፀ ባህሪያቱ በመራመድ፣ ወዲያ ወዲህ በማግደም፣ በዕለት ተዕለት መግባት-መውጣት ሂደት ውስጥ መንገዶችን ያበጃሉ። እነዚህ መንገዶች ከሕይወታቸው ጋር የተሳሰሩ ናቸው። የሕይወት ታሪካቸው መንገዶቹ ላይ ታትሟል። መንገዶቹም ከወጣቶቹ ሕይወት ጋር ተሸምነዋል። ሕልው ሆነውም ያዩትና የሰሙትን አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ።
“በዚህች መንገድ አቧራ፣ በዚህች መንገድ አፈር ላይ፣ ሁሉ ያቅሙን የራሱን ሐላፊ፣ የራሱን ዛሬ፣ የራሱን ትንቢት ጭሯል . . . መንጎል መዘን፣ እዚያ ዋልካ ውስጥ ነክረን፣ ብራና ላይ ብንቸከችክ ድጓችን አይሆንም?”
እነዚህ መንገዶች ርዝማኔአቸው ከገፀባህሪያቱ ግቢ እስከ ከተማዋ እምብርት፣ እስከ ዳር ድንበር፣ ከዚያም እስከ ባህር ማዶ ይዘረጋል።
1/
“#ጥቢኛ_እግር”
አዳም፤ የመንገዶቹን ሕይወት የሚያሳየው በገፀ ባህሪያቱ መነፅር ነው። የድርሰቱ መጀመርያ ላይ ዋናው ገፀ ባህሪ አለሙ ገና ከመወለዱ፣ ከእናቱ ጡት በፊት፣ አዋላጆች በደስታ ሲጨፍሩ ከመሬት ያስነሱትን አቧራ ይቀምሳል። ከፍ ሲልም የተወለደበት ቤት ውስጥ ይድሃል። የቤቱ ወለል አቧራ አይኑ ውስጥ ይገባል፣ ሽንቱን መሬት ላይ ሸንቶ፣ በሽንቱ የተለወሰውን አፈር በልጅነት ጉጉት ይቀምሳል። በልጅነት መገለጥ የቤቱንና የግቢውን መንገድ ይመረምራል፣ የሀገሩን አፈር ይቀምሳል፣ የሀገሩን አቧራ ይተነፍሳል። ገና በሞሳነት እድሜው ሁለንተናው ከሀገሩ አፈር ጋር ይዛመዳል።
“አቧራው ቤተሰቤ ነበር
አቧራው ምግቤ ነበር”
“ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ክፍል፣ ከላይ ወደታች ተዟዙሬ አጥንቼአለሁ። ነገሮችን በዐይን፣ በዳሰሳ በጣዕማቸው መድቤአለሁ።
ይሄ ጎዳናዬ ነበር።
ይሄ አገሬም ነበር”
ደሃ እናቱ እንዝርቷን እያሾረች “#እግሮችህ_የቡሄ_ጥቢኛ ይመስላሉ” ትለዋለች። ድህነት ይዟት ለእግሩ ጫማ መግዛት ስለማትችል፣ አድጎ በእግሩ መሄድ ሲጀምር ለእግሮቹ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይጀምራል። የጣቶቹ ቁጥር ጎድሎ እንደሆነ ይቆጥራል፣ ጣቶቹ መሃል ያለውን አቧራ እየፈተለ ይጠርጋል።
“በእናቴ የእግሮቼ ጥቢኛ ተብሎ መሰየም መንገዶችን አተኩሬ እንዳይ አደረገኝ” እያለ መንገዶቹን በልዩ አትኩሮት ይመዘግባል። መንገዶችን ሲያይ፣ መንገዶቹ ላይ የታተሙትን ዱካዎች፣ የጫማ ማህተሞች ይመረምራል። የራሱን ትርጉም እየሰጠም ከባቢውን ይረዳል።
2/
“እግር_እንይ”
“አርቀን ማስተዋል ማለት፥ የኛን ሥልጣኔ ድልድይ
እግር ማየት ነው ብለዋል፥ እስቲ እንግዲህ እግር እንይ!”
(ፀገመ)
ፀጋዬ ገ/መድህን ፒያሳ ላይ ሆኖ በስላቅ እንደታዘበው የአዳም ገፀ ባህሪ አለሙ መንገድና እግር ተመልካች ነው። ይህ ልምድ ግን እንደፀጋዬ ስላቅ ከንቱ ፆታዊ መሻት ሳይሆን ከመንገድና ከእግር ላይ የማንነት፣ የሀገር፣ የታሪክ ትርጉም ፍለጋ ነው። አለሙ ለመንገዶችና መንገዶች ላይ ለታተሙ ዳናዎች ልዩ አትኩሮት ይሰጣል። ለዚህም ነው በዚህ አጭር ልብ ወለድ ውስጥ በርካታ ዳናዎች፣ እግሮችና የመንገዶችን ጉዳይ የምናነበው። (ምናልባት ለመንገዶች ልዩ ቦታ መያዝ የአዳም የጂኦግራፊ ትምህርት ቅመም ይኖርበት ይሆን?)
የገፀ ባህሪው ንፅረተ ዓለም የሚቃኘው በመንገዶችና በተጓዦቹ ዳና ነው። እነዚህን ምሳሌዎች እንይ፤
“እናቴ በጓዳ በር ገብታ ማድቤት ቁርስ መስራት ስትጀምር፣ ከመስፈሪያቸው የተለቀቁት ዶሮዎች ላባቸውን እያርገፈገፉ፣ የአቧራው መንገድ ላይ #የእግሮቻቸውን_ሰንበሮች_ያትማሉ”
***
“ጤዛ ተኖ ሠፈር ሞቅ ሲል የመጀመርያዋ ነጠላ/ቀሚስ/ጋቢ ገዢ ሴት በር ሲያንኳኩ #በሳር_በሳሩ_እሄድና እከፍትላቸዋለሁ። በጧሚ (ቁርስ ባልበላ) አፋቸው እያዛጉ ጊዜ_በቀደደውና #ተረከዙን_ባሳጠረው_ጎማ_ጫማቸው_እዚያች_ደቃቃ_መንገድ_ላይ_ዱካዎች ይጥላሉ። ብዙ ያልተራራቁ፣ በመጠኑ የግራው ወደ ግራ፣ የቀኙ ወደ ቀኝ በሚጠቁሙ ሸፋፋዎች #ድንግል_አቧራዬ_ላይ_ሕላዌአቸውን_እየፃፉ”
***
የአለሙ ጎረቤት የሆኑትን አቶ ሸገኔ አባታቸው ሊጠይቋቸው ከቡታጅራ ሲመጡ አለሙ ከእግራቸውና ከኮቴያቸው ስር የማያውቀውን አዲስ ሀገር ምስጢር ይመረምራል። ከሰፈሩ ንፍቀ ክበብ ሳይወጣ ሰፊውን ሀገሩን ማወቅ ይጀምራል
“ሁልጊዜ ሲመጡ የማያቸው #በቦት_ጫማ_ነው…ከቦት ጫማቸው ላይ የተራገፈውን ጭቃ አንስቼ #የተረከዝ_ማሕተሙን አያለሁ። እሱን በእጄ ስይዝ ለአፍታ ‘ቡታጅራ’ የተባለ ሀገር የሄድኩ ይመስለኛል”
***
“ቤዛዊት ግቢ የዝንጀሮ ቆለጥ ነበር። በፀሐያማ የበጋ ቀናት በምቾቱ ተስቦ ከአጥር ውጪ የተንዠረገገውን ወይናማ ፍሬውን እየዘለልኩ በጥሼ፣ የለበሰውን አቧራ ሳላፀዳ በልቻለሁ። አበባዎቹን ካማሩበት አውልቄ ወለላቸውን መጥምጫለሁ። አባቷ ‘ችግኙ ከአንኮበር የመጣ ነው’ ሲሉ ሰምቻለሁ። አንኮበር የት ነው? #እግር_አለው_ቦታው? #እግር_አለው_ችግኙ?
አለሙ ከመንገድና ከእግር ጋር ያለው ቁርኝት አዲስ መገለጥን ብቻ ሳይሆን የነገሮች መመልከቻ አንፃርም ሆኖ እናነባለን:: ለምሳሌ ውበትን ሲገልፅና ሲረዳ የሰፈሩን መንገድ አጣቅሶ ነው። በቁንጅናዋ ማልሎ ሱቋ እየተመላለሰ ከረሜላ የሚገዛትን መሪማን ለማድነቅ የትረካ አትኩሮቱን እሷ ላይ ሳይሆን መንገዱ ላይ ያነጣጥራል፤
“ሲነጋ ጀምሮ መሪማ ስታየው የምትውለው #የታደለው_መንገድ ይኼ ነው።”
መንገዱ ነፍስ ዘርቶ፣ ሕያው አካል የሆነ ይመስል መሪማ ሱቅ ስለተዘረጋና ስታየው ስለምትውል ከመንገዱ ጋር ቅናት ይጋባል።
መንገዶቹ እየረዘሙ፣ ከሰፈር ወደ ከተማ፣ ከዛም ወደ ሀገር ሲለጠጡ፣ የገፀ ባህሪያቱም ህይወት በዚያው አብሮ ሲለወጥ የምናየው በእግራቸው ዳና እና ጫማቸው ላይ በተከመረው ጭቃ ነው።
“በአውቶቡሶች ውስጥ –አረንጓዴያቸው የተረሳ የብረት ባንዲራዎች፣ በታክሲዎችም– ባሕርና ደመና የመሳሰሉትን፣ #የጫማችንን_አቧራ_ልንጥልባቸው_እንሳፈራለን። የማያውቀን ያራገፍነውን ተሸክሞ ይሄዳል። ወደ ካዛንቺስ፣ ወደ ኡራኤል፣ ወደ ልደታ፣ ወደ መሿለኪያ፣ ወደ መሣለሚያ፣ ወደ ኮቶኒ፣ ወደ ፖፖላሬ፣ ወደ ቄራ፣ ወደ ወሎ በር፣ ወደ ጅማ በር፣ ወደ ሽሮ ሜዳ፣ ወደ መርካቶ፣ ወደሆነ ቦታ… ጠረንና አፈር እንደኳስ እየተቀባበልን #በዚች_ከተማ_አንጀቶች_እንደ_ጉርሻ_ስንመላለስ”
“የሠፈራችንን አቧራ #በጫማዎቻችንና_በእግሮቻችን_ይዘን አስፋልት ውስጥ እንገባለን። ክረምት ክረምት በጋምቤላ ላይ፣ በመቱ ላይ፣ በጅማ ላይ፣ በደሴ ላይ፣ በደጀን ላይ፣ በሶዶ ላይ፣ በጨርጨር ላይ እየጎረረ የመጣ ደመና በጣለው ዝናብ የቦካ ነው። ረጠበም ዶቀተም አውቶቡሶች፣ የጭነት መኪናዎች ጭቃችንን እንደ ነፋሱ ሲካፈሉን… በጎማዎቻቸው አጣብቀው ወዳላየናቸው ቦታዎች ሊያደርሱት….”
3/
የ’ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ ዋና ገፀ ባህሪ በጉርምስና እድሜው የወቅቱ አብዮት መንፈስ ይቀርበውና አንዲት ካፌ ውስጥ ቁጭ ብሎ መንግስት ገልባጭ ለመሆን ይመለመላል። ታዲያ የዚህችን ካፌ መግቢያ በር እንደሚከለው ይገልፀዋል፤
“ገብረወልድን የተዋወቅኩት እዚህ ነው። ቅዱስ ከተባለ አራዳ ጋር የተዋወቅኩት እዚህ ነው። መንግስት ገልባጭ ለመሆን የተመለመልኩት እንትና ካፌ ቤት ገብረወልድ የገዛልኝን ቺዝ በርገር በቡና እያማግሁ ነው። የኬክ ቤቱ መግቢያ ወደ ውስጥ እስከ ሁለት ሜትር ጥልቀት #በደንበኞች_ጫማ_ታዝሎ_የመጣ_ጭቃና አቧራ ሸፍኖት ነበር። ሊከላከሉትም ሰጋቱራ እየነሰነሱ…..”
አለሙ ስሟን እንኳን ከማያስታውሳትና ‘እንትና’ ብሎ እንደዋዛ ከጠራት ካፌ ውስጥ ልብ ያለው አንድ ነገር የደንበኞች የእግር አሻራና የመጡባቸውን ቦታዎች ማህተም የሆነውን ጭቃ ለመከላከል የተነሰነሰውን ሰጋቱራ ነበር።
በልጅነቱ፤ እነዚህ የእግር ዳናዎች የቤቱ አንድ አካል እንደነበሩ ቀደም ብሎ ይተርካል፤
“#ጭቃ_የለበሱ_እግሮች ወደ ቤት ሲገቡ ከቤትም ሲወጡ አይቻለሁ። እነሱ የተዉት ከወለሉ ተጣብቆ የቀረው ጭቃ ሲደርቅ በላዩ ላይ ተንከባልያለሁ”
ቺዝ በርገር የሚበላባት ዘመናዊ ካፌ ግን ጭቃውን ለመከላከል መግቢያዋ ላይ ሰጋቱራ ተነስንሶባታል። የሰው ልጅ ዘመናዊነትና ስልጣኔ ሲቀምስ ከመሬት ጋር ያለው ንክኪ እየራቀ ይመጣል ይላሉ ፀሀፍት። ለምሳሌ ጫማ፣ መኪና እና ወንበር የዚህ ውጤቶች ናቸው። ጫማ የተጓዡን እግር ከመሬቱ በመነጠል በእግርና በመሬት መነካካት የሚፈጠረውን አካላዊ ቅርበትና ረቂቅ አስተውሎ ይገድባል። ወንበር ጭራሹኑ እግርን ከማሰብ ወጪ ያደርገዋል። በዚህም፤ ድርጊት፣ አካልና አእምሮ ይነጣጠላሉ። አየር ላይ የቀረ፣ መሬት ያልያዘ ኑባሬም የዘመናዊ ሕይወት መገለጫ ይሆናል፤
“Nothing however better illustrates the value placed upon a sedentary perception of the world, mediated by the allegedly superior senses of vision and hearing, and unimpeded by any haptic or kinaesthetic sensation through the feet. Where the boot, in reducing the activity of walking to the activity of a stepping-machine, deprives wearers of the possibility of thinking with their feet, The chair enables sitters to think without involving the feet at all. Between them, the boot and the chair establish a technological foundation for the separation of thought from action and of mind from body – that is the fundamental groundlessness so characteristic of modern metropolitan dwelling”
ሰው ከተፈጥሮና ከከባቢው ጋር ያለው ግንኙነት ከመንካት ወደ ማየትና ወደ ማሰብ የተሸጋገረው ዘመናዊነት ሲመጣ ነውና፤ አለሙም ሰፈርና ሀገሩን ከመንካትና ዱካውን ከመመርመር ርዕዮተ አለም ወደ መስማት ይሸጋገራል። ምናልባትም እንደ ቅዱስ ያሉ ‘አራዶች’ አብዮተኛ የሚመለምሉባት ካፌ ውስጥ የሀገሩን አፈር፣ ተንከባሎ ያደገበትን ጭቃ ላለማስገባት የተበተነችው ሰጋቱራ የዚህ ሽግግር/መነጠል ትዕምርት ነች። ከካፌው ሁሉ ለይቶ ልብ ያላትም ለዚሁ ይመስላል።
የፖለቲካ ንቃቱን ተከትሎ የአብዮቱ የፖለቲካ ሽኩቻ ሲጀመር ሂደቱንና ውጤቱን የሚነግረን አሁንም እግርና የሰፈሩን መንገድ እያጣቀሰ ነው። እዚህ ላይ በልጅነቱ የሕይወትን መንገድ የገለጡለት መንገዶች በወጣትነቱ አስከፊ ዘመን የሱንና የአብሮ አደጎቹን የሞት፣ የስቃይና የፀፀት ድርሳን ያሳዩታል።
“አብዮቱን ከአጥቂነት ወደ ተከላካይነት ሲያሸጋግሩት ተተኩሶበት #እግሩን_የተመታው፣ እያነከሰም የተያዘው እዚህ ነው”
***
ያለስሙ ስም ሰጥተው “ባንዳ” ብለው ያገለሉትና ሰላምታ የነፈጉት ጓደኛቸው፤ ብቸኝነትና መገለሉ ከብዶት ራሱን ሰቅሎ ሲያገኘው የተመለከተው እግሩን ነው፤
“#ለስላሳ_እግሮቹ የገላውን ፍስ ለብሰው፣ በአደገበት፣ አቧራ በተጫወተበት አፈር ተለስነው”
***
የልጅነት ጓደኛውን ቤዛዊትን፤ ገብሬ የተባለው የወንድ ጓደኛው (ለትግል የመለመለው) አታሎና ከእሱ ደብቆት፣ በሀሰት ፍቅር አስረግዞአት በፀፀት ማስወረዷን ያያል። ያደጉበትና የተጫወቱበት መንገድ ላይ ሲያገኛት የጨለመ ሕልሟን እግሮቿ ላይ ይመለከታል
“#በግራ_እግሯ ላይ ከቀሚሷ ስር ደም ሸረር ብሎ ሲወርድ አየሁ።”
በመጨረሻም፣ በፖለቲካ ምክኒያት የታሰረበት እስር ቤት ውስጥ እግሩ ተገልብጦ ይገረፋል
“ሳራ የሲሚንቶ ቤት አስገብታ ስላስገደልኳት በበቀል #ውስጥ_እግሮቼን በሽቦ መታቻቸው። የምኒልክ ወስናቸውን ‘እሸት እሸት’ እያፏጨሁ በተንጎራደድኩበት ጎዳና፤ በወፌ ላላ አለቀስኩ”
“#ውስጥ_እግሬም በሽቦ እሳት ነዶ ነበር። ወፌ ላላዬን እንደ ለምለም እንጀራ ደጋግሜ በላሁ”
በዚህ ስቃይ ውስጥ ሆኖ ራሱን ይጠይቃል። እዚህ የደረሰበትን የህይወት ጎዳናም ይፈትሻል።
“ማነው እንዲህ አንተን በደም መራኮት ያስተማረህ?” ሲል ራሱን ይጠይቃል።
ለዚህ ጥያቄ መልሱንም የሚፈልገው ታዲያ ያው አፈሩ ውስጥ ነው።
“ያስተማረኝን ፍለጋ አፈር እየጎተትኩ ከተከተትኩበት ስወጣ ያጋጠመኝ መልስ መሐረቦሽ፣ ቴዘር ቦል፣ ሶከር፣ ጢብጢብ . . . የመሳሰሉ ነበሩ”
የኖረበትና ያደገበት አፈር የልጅነት ሕይወቱንና ፍቅሩን እንጂ የተገዳደለበትን ምክኒያት አላሳየውም።
4/
“አንተ ጎዳና፤ አንተ መንገድ”
“ካላሰብኩት መንገድ እያመራ እግሬ
የት ቦታ አደረሰኝ ደግሞ ኧረ ዛሬ!
ባልደከምኩ ነበር በጉዞ አበሳ
ባውቀው መድረሻዬን ጥንቱን ሳልነሳ”
(ሚካኤል በላይነህ)
አለሙና በሕይወት የተረፉት አብሮ አደግ ጓደኞቹ የሕይወታቸው መጨረሻ ያላሰቡትና ያላለሙት ስደት ይሆናል። እሱ በእግሩ ተጉዞ፣ ሱዳንን አቋርጦ አውሮፓ ይገባል። እንግሊዝ ሀገር፣ ለንደን ከተማ ቆሞም በሀገሩ እንደለመደው የለንደንን ጎዳናዋች ይመረምራል። ነገር ግን የምዕራባውያን ስልጣኔ ካዘመናቸው ጥርጊያ መንገዶችና አስፋልቶች ላይ ትርጉምና ሕይወት ማግኘት ቀላል አይሆንም፤
ፀሀፍቱ እንደሚሉትም፤
“It is simply that boots impress no tracks on a paved surface. People, as they walk the streets, leave no trace of their movements, no record of their having passed by. It is as if they had never been. There is, then, the same detachment, of persons from the ground, that runs as I have shown like a leitmotif through the recent history of western societies. It appears that people, in their daily lives, merely skim the surface of a world that has been previously mapped out and constructed for them to occupy, rather than contributing through their movements to its ongoing formation”
በማያውቀው መንገድ፣ ዱካዎችን መከተልና ማንበብ በማይችልበት የለንደን ኮንክሪት ጎዳና ላይ፤ ከሀገሩ ተነጥሎ፣ መሬት ያልያዘ፣ አየር ላይ የሚንሳፈፍ ምስኪን ስደተኛ ይሆናል
“የለንደን መንገዶች አስፋልትና ሲሚንቶ ናቸው። አላውቃቸውም አያውቁኝም። የትኛውንም ቦርቡሬ ገበጣ መጫወት አልችልም . . .
ከተቀመጥኩበት እውጭ የመንገድ ስም የተፃፈበት የብረት ሰሌዳ ይታየኛል። ላነበው ባልችልም ይታየኛል። አቧራ አይሸተኝም። አይታየኝም”
ቤቱ ገብቶ የሕይወቱ ታሪክ የተፃፈበትን እግሮቹን ሲመለከትም ልጅ ሆኖ እናቱ #ጥቢኛ የምትለው እግሩ ተለውጧል። የተገረፈበት፣ በእግሩ የተሰሰደበትና የቆሰለበት ታሪኩ ማህተም እግሩ ላይ ይታያል
“ፊት ለፊቴ የተዘረጉትን እግሮቼን አየኋቸው። ጥፍሮቼ ጠቁረዋል። መረገጫቸውን የኦምደርማን መሬት አምሶአቸው ገርጅፈዋል። ቁርጭምጭሚቶቼ አመድ ይመስላሉ። (ከካርቱም ሰብስበው ያመጡት) ጠዋት ማታ አመድ እንደሚመስሉ ልብ አልኩ። ግራ አውራ ጣቴ ተሰብሮ ወደ ቀኝ ተጣሟል። (መተማ አካባቢ ከገደል ወድቄ የሆንኩት ነው)
እግሮቼ እናቴ ትላቸው እንደነበረ #ጥቢኛ አይመስሉም . . . ይህቺን እግሬን ፎቶ ተነስቼ ለእናቴ ብልክላት ታውቀኛለች?”
አለሙ ያለፈ በደሉን በኑዛዜ ንስሃ አጥቦ አዲስ ህይወት ለመጀመር የሚዘጋጀው፣ አውሮፓ ተኝቶ በሚያየው ህልም ጠቋሚነት ነው።
5/
“በመዋደድ ጉዞ
በፍቅር መንገድ ላይ
እየተሳሳቁ ዳግም
እያዩ መናፈቅ
በትዝታ”
(ጥላሁን ገሰሰ)
በታሪኩ መጨረሻ ላይ አለሙ የልጅነት ጓደኛውን ቤዛዊትን አውሮፓ ያገኛታል። የወጣትነት ዘመን በደላቸውን ተቃቅፈው ይቅር ይባባላሉ። ኋላም ላይ እየተሳሳቁ የጋራ ቁስላቸውን አብረው ያክማሉ። የሰባተኛውን መንገድ መጀመርያ በፍቅራቸው ይጀምሩታል።
አንድ ቀን ቤቱ ተቀምጦ ሕልም ያልማል። በሕልሙ ልጅነቱን፣ እናቱን፣ ሰፈሩን እና ሀገሩን ያያል።
“እዚህ ነጭ የብርሃን ሰሌዳ ውስጥ ቢራቢሮዎቹ እየበረሩ ይገባሉ። ‘ሂድ!” አለችኝ እማማ። ወለል ላይ አስቀመጠችኝ። የምንቧች መስሎኝ ነበር። ግን ቆሜአለሁ። ደጋግማ “ሂድ!” አለችኝ። በር ላይ የተገተረ የመሰለው ብርሃን በላዬ ከነትኩሳቱ ፈሰሰ። አይኖቼን በድፍረት ስገልጥ በስተቀኜ አረንጓዴ መስክ ላይ ቤዛዊት ገመድ ስትዘል አየኋት። እማማ ለሶስተኛ ጊዜ “ሂድ!” አለችኝ (በልቤ እቆጥራለሁ)። ቃሏ ውስጥ ቁጣ ነበር። እንደዚህ ተቆጥታኝ ስለማታውቅ በድንጋጤ ባነንኩ።”
በፀፀትና በትርጉም የለሽ የአውሮፓ ኑሮ ታስሮ የነበረው አለሙ በሕልም አለም የእናቱ ምርቃት “ሂድ!” ተብሎ ለአዲስ ጎዳና ይታጫል። በሕልሙ አይኑን ሲገልጥ ያያት ቤዛዊትን ነው። ከሕልሙ ሲነቃም ቤዛዊት አብራው አንድ ክፍል ውስጥ ነበረች። ባሻገር ቆማ ስልክ ስታወራ ያያታል፣
“ገላዋ የአገሯ ታሪክ ያለፈበት ስጋና አጥንት አይመስልም”
በመጨረሻም፤ በጥፋተኝነት ስሜት የታሰረውን እግሩን ነፃ አውጥቶ “እንደሰው ልጅ ተሳሳትኩ” ብሎ በኑዛዜው ማግስት አዲስ የሕይወት መንገድ ይጀምራል።
—//—
ⓒ ጌታሁን መ.
***
*ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ (አዳም ረታ: 2003)
*CULTURE ON THE GROUND The World Perceived Through the Feet (Tim Ingold:2004)