Tidarfelagi.com

ያመት በአል ማግስት ትእይንቶች!!

– የተመጠጠ ቤት
የሞላ ሽንትቤት
ጭር ያለ ቤተሰብ
የተጠረገ ድስት -ድርቅ የመታው ሞሰብ!!

-ያደፈ ቄጤማ
በበግ በሰው እግር- የተደቀደቀ
ወዙ ባንድ ሌሊት -ተመጦ ያለቀ
መጥረጊያ ሚጠብቅ -ወድቆ ተበታትኖ
ትናንት ጌጥ የነበር- ዛሬ ጉድፍ ሆኖ!!

-የተወቀጠ ፊት -የነጋበት ድንገት
በዳንኪራ ብዛት-ወለም ያለው አንገት
የዞረበት ናላ -ጌሾ ያበከተው
እንኳንስ መገንዘብ -መጀዘብ ያቃተው
የወለቀ ወገብ -የዛለ ትከሻ
መኪና ይመስል -ብየዳ የሚሻ

-የጠጅና የጢስ- ድብልቅ እስትንፋስ
ከሆድ ሸለቆ ውስጥ -የታፈነ ነፋስ
ባንጀት የታሰረው
እንደተከበበ አመፀኛ ሽፍታ
መውጫ የቸገረው!

-የማይፈካ ሰማይ -የማይዘንብ ደመና
በላባና በፈርስ -ያደፈ ጎዳና
በበግ ራስ ምላስ -የተልከሰከሰ
የጠገበ ውሻ-
በመንፈቅ አንድ ጊዜ አጥንት የቀመሰ::

ሀንጎቨር ያዛገው-መሂና አሽከርካሪ
እግረኛ አስደንባሪ
በከፊል የነቃ -በከፊል የተኛ
ከሱ የማይሻል- የመኪና እረኛ
ካውራ ጎዳናው ዳር -ቁሞ ሚያንቀላፋ
ድብርትን ባናቱ -እንደ ቆብ የደፋ!!

The moral of the story :

የተድላ ማገዶ!!
ላጭር ጊዜ ነዶ
ላጭር ጊዜ ደምቆ
ላጭር ጊዜ ሙቆ
አመዱ ብዙ ነው: አያልቅም ተዝቆ!!

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • esemlalemserkadis@gmail.com'
    ሰርክአዲስ commented on November 26, 2021 Reply

    የምር በጣም የሚያዝናና ነው app ከጫንኩት ብዙ ጊዜ ነው ግን ለመክፈት ዘገየው አሁንም ግን ተመችቶኛል በዚሁ ቀጥሉበት በውቄ በጣምምምምም ነው የምወድህ እግዚአብሔር ይባርክህ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...