የፍቅረኞች ቀንን የማልወደው ፍቅርን ስለማልወድ አይደለም፡፡ ፍቅርን የሚዘክር ቀንን ስለምጠላም አይደለም፡፡
የፍቅረኞች ቀንን የማልወደው ከፍቅረኞች ቀን ይልቅ የጥቅመኞች ቀን እየሆነ ስለመጣ ነው፡፡
‹‹ከወደድከኝ የፍቅረኞች ቀን እለት ግሎባል ሆቴል ውሰደኝ›› የሚል ማስታወቂያ በየቦታው ተለጥፎ ሳይ፣
‹‹እኔ ዘንድሮ እንደአምናው በቸኮሌት አልሸወድልህም…ዘንድሮ የምፈልገው የኢቴልኮን ፓያስትራ ከነፀጉር ማድረቂያው ነው›› የሚል መስታወቂያን በሬዲዮ ተደጋግሞ ስሰማ፣
እውነትም የዚህ ቀን ፋይዳ መጠቃቀም እንጂ መዋደድ ስለማይመስለኝ ነው፡፡
ቀኑ ከፍቅር ይልቅ አራተኛ ክፍል እያለሁ በተደጋጋሚ ይደረግ የነበረውን ‹‹ፍቅር ይበልጣል ገንዘብ›› ክርክር ስለሚያስታውሰኝ ነው፡፡
ፍቅር ለውድ ስጦታ ራሱን የሚያንበረክክበት ቀን ስለሚመስለኝ ነው፡፡
ቅድመ ሁኔታ ያለው መፋቀር ስለሚያስጠላኝ ነው፡፡
እንደው ባጠቃላይ ፤ በሁሉም ቀን የሚዋደዱ ሰዎች ‹‹አንድ…ሁለት…ሶስት…›› ተብለው ወይም ደግሞ ፊሽካ ተነፍቶላቸው መዋደዳቸውን ለመግለፅ ከሱቅ ሱቅ ሲሯሯጡ ማየት ስለሚቀፈኝ ነው፡፡
እኔ ምንም ይሰማኝ ምንም፤ ባለፈው አመት ግን በአንዳንድ ምግብ ቤቶች ለቀኑ ተብሎ ተብሎ ቀይ እንጀራ እና ቀይ ዳቦ መጋገሩን ስመለከት ‹‹ቫለንታይንስ ደይ›› እንኳን የሴቶቻችን ልብ ውስጥ ቡሃቃችን ውስጥ መግባቱን ተረዳሁና ተስፋዬን ቆረጥኩ፡፡
እናም የዚህ ቀን ተሳታፊ ለመሆን መርጠን…
አበባ ለመግዛት ወዲህ ወዲያ የምንራወጥ ከሆነ፣
የተጠየቅነውን ስጦታ በጊዜ ለመሸመት የምንዋከብ ከሆነ፣
ቢያንስ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ፋይዳ በሚኖረው ሁኔታ ብናሳልፈው መልካም ነው ብዬ አሰብኩ፡፡
ቢያንስ እምቡጡኑም ፍርፋሪውንም ሳንበላ ልናከብረው ብንችል ጥሩ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡
ይህን ሳስብ ሳለሁ….
ይሄንን ቀን ምክንያት አድረገው የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ያለማንም ድጋፍ ለመጨረስና ሰው ለመሆን የሚጥሩ ጎበዝ ተማሪዎችን ለመርዳት የሚለፉ መልካም ሰዎችን መኖራቸውን ሰማሁ፡፡
ሃሳባቸው እንዲህ ነው፡፡
ቀኑን የሚያከብሩ ሰዎች ለፍቅረኞቻቸው አበባ ወይም ሌሎች ስጦታዎችን ከእነሱ ቢገዙ ገንዘቡን ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የአመት ወጪ ማዋል ነው፡፡
የማወራችሁ፤ የወር አበባቸው ሲመጣ ‹‹ሞዴስ›› መግዣ ስለሌላቸው ለቀናት ከክፍል ስለሚቀሩ ሴት ተማሪዎች ነው፡፡
የምነግራችሁ፤ ሳሙና መግዣ አጥተው ሌሎች ተማሪዎች ጥለውት የሄዱትን የሳሙና ስብርባሪ ለመጠቀም በየሽንት ቤቱ ስለሚንከራተሩ ተማሪዎች ነው፡፡
የማነሳላችሁ፤ ደብተር መግዣ በማጣት፣ ጠቃሚ ‹‹ሃንድ አውት›› ማባዣ በማጣት የትምህርት ውጤታቸው ስለሚጎዳ ጎበዝ ተማሪዎች ነው፡፡
…የነዚህ መልካም ሰዎች አላማ ባለፈው አመት ተሳክቷል፡፡
ከረዳናቸው ዘንድሮ ደግሞ ይበልጥ ይሳካል፡፡
ሽያጩ መቼ ነው?
ሀገር ውስጥ ላሉ፤ ቅዳሜ እና እሁድ
ከሀገር ውጭ ያላችሁ ደግሞ፧ ይህን ሊንክ በመከተል መግዛት ትችላላችሁ
ቦታዎቹ፤
ማለዳ ካፌ – አራት ኪሎ
ቦሌ – ኤድና ሞል፧ሞናርክ ሆቴል እና ሴቨር ሬስቱራንት
ፍቅር ካለ 2000 ሺህ ብር አንድን ተማሪ ለአንድ አመት ድብን አድርጎ ይደገፋል፡፡
…እንግዲህ ያለ ቅድመ ሁኔታ ከተዋደዱ አይቀር እንዲህ ነው!
One Comment
Thanks alot….