Tidarfelagi.com

የጥንቱ ፈጥኖ ደራሽ የአራዳ ዘበኛ

በዚህ አጋጣሚ የቀድሞውን ትውልድ አኩሪ ታሪክ ከአስታወስን አይቀር ከእነ ዘዬው እና ቋንቋው ማስታወሱ ደግሞ በበለጠ መንገድ ራሱን የቻለ እውቀት ስለሆነ ስለዚህ ፖሊስ ከማለት እንደ ትውልዱ የቋንቋ አጠቃቀም “የአራዳ ዘበኛ” እያሉ መጥራቱ ግድ ይላል ታዲያ ይህን አስገንዝቤ ወደ ታሪኩ ስቀለስ ከዚህ በፊት በተለያዩ አመታት በተለያዩ ስያሚወች ተመስርተው ህብረተሰቡን ያገለገሉ ጽኑ እና ታማኝ የአራዳ ዘበኛ አባላትን አስተዋጾ ያቀፈ አጫጭር ጦማሮች ማቅረቤ ይታወሳል።

ከአጼ ቴወድሮስ ዘመነ ስርዓት ጀምሮ ተቋቁመው የነበሩ የሰላም ጥበቃ አባላት ተባራሪ ዘበኛ ፣ጥሩብሌ ፣ ጠረ ወስላታ ፣ የደጋው ነብር እየተባሉ ለዘመናት በህብረተሰቡ ይታወቁ እንደነበር እና አመት ከአመት ጀንበር ፈንጥቃ እስክታቆለቁል በየመንገዱ በገበያው በመንደሩ ተሰማርተው ለህብረተሰቡ የጥበቃ አገልግሎት ሲሰጡ እርሻ የማረስ ጊዜ ስለአልነበራቸው የሚተዳደሩት መንግስት ከሚሰጣቸው የወር ተቆራጭ ደሞዝ ሲሆን የደሞዙም መጠን እንደዘመኑ ይለያያል።

ለዛሬ ደግሞ በምስሉ ላይ የሚታዩትን በምዕራባውያን አቆጣጠር በ1945 ዓም ላይ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በጎ ሀሳብ “ፈጥኖ ደራሽ ” በሚል መጠሪያ ተቋቁመው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በምንም አይነት ሁኔታ የተጣለባቸውን የመንግስት አደራ በጉቦ ሳይሸጡ ህብረተስቡን በሐቅ አገልግለው ከታሪክ ዕይታ የተሰወሩትን የጥንቱን የአራዳ ዘበኞችን እናስታውሳቸው።

የዛሬው ዘመን የአራዳ ዘበኞችስ ይህን ታሪክ ያውቁት ይሆን? ጉቦ ተቀብሎ ወንጀለኛን መልቀቅ ተጠቂውን ህብረተሰቡ በቁም ገድሎ መቅበር እንደሆነ እና በሙስና ተደልሎ ወንጀለኛን በነጻ የሚለቅ ፖሊስ ከወንጀለኛው የባሰ የህዝብ ጠላት መሆኑን ይረዱ ይሆን?

የታሪክ አስተዋሽ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...