Tidarfelagi.com

የገደለ አባትሽ የሞተው ባልሽ (ክፍል ሶስት)

አማላይ ከሬሳ ሳጥኑ አጠገብ አልነሳም ብላ ለያዥ ለገናዥ አስቸገረች… ጋሼ የልጄ ገዳይ እሷ ናት ካልገደልኳት ብሎ ሁከት አስነሳ። እማዬም ለዓይኔ አልያት አለች። እኔስ? … እኔ ዞረብኝ።

«አስወጡልኝ ይህቺን ልጅ… ለልጄ በቅጡ ላልቅስለት አስወጡልኝ! » እማዬ እሪሪሪ አለች።

«ይግደሉኝ!… ይግደሉኝ እንጂ የትም አልሄድም! ይግደሉኝ ከፈለጉ… » አማላይ በሲቃ በተሰባበረ ቃላት ጋሼ ላይ አፈጠጠች። በጣም ጮክ ብላ ስለነበር ለተወሰኑ ሰኮንዶች ሁሉም ፀጥ አለ። ጋሼን ጨምሮ።…… ጎረቤቶች እንደመደገፍ እንደመግፋትም እያደረጉዋት “ከአይናቸው ትንሽ ገለል በይላቸው እስኪ።…. ጎሽ ልጄ!….. ልጃቸውንም አይደል ያጡት ። ጎሽ ሰው የሚልሽን ስሚማ…” እያሉ ያባብሏታል። ለእርሷ ያዘኑ ነገር ያስመስሉታል። ልክ ነገር እያደረጉ ያሉ ያስመስሉታል። በለቅሶ ብዛት አብጦ ግንባርና አይኗ አለመለየቱ ሀዘኗን አልነገራቸውም። የተዘጋ ድምፅዋ እና ፍቅሯ ከሞተ ደቂቃ አንስቶ እህል ያልቀመሰ የዛለ አካሏ የስብራቷን መጠን አልገለፀላቸውም። ምክንያቱም የገዳይ ልጅ ናታ!
“ልቀቋት የትም አትሄድም። …አይታያችሁም የሷስ ሀዘን? እሷም ፍቅሯን ነው ያጣችው ታልቅስለት ልቀቋት።” አስቤው አልነበረም ያልኩት።

ጋሼንና እማዬን ለብቻቸውከድንኳኑ አስወጥቼ አወራኋቸው።
“እርጉዝ ናት። የአብርሽን ልጅ አርግዛለች።” አልኳቸው
“እና ምን ይሁን ነው የምትለው? ከልጅህ ገዳይ ጋር በአንድ ድንኳን አልቅስ ነው የምትለኝ?” አለ ጋሼ እየጮኧ
“ጋሽዬ እሷ ምን አደረገች? እኔ ወንድሜን፣ እናንተ ልጃችሁን እንዳጣችሁት እሷም ፍቅረኛዋን የልጇን አባት ነው ያጣችው። አብርሽ በሷ ምክንያት በመለወጡ ስታወድሳት የነበረችው አማላይ እኮ ናት። ይወዳት ነበር ታውቃላችሁ። ትወደዋለች። ለመጨረሻ ጊዜ እጄን ይዞ አማላይ እና ልጄ ነው ያለኝ።”

እማዬ እርጉዝ መሆኗን ስታውቅ ለዘበች። ጋሼን ማሳመን ግን ቀላል አልነበረም።
“እሷ ከዚህ ድንኳን ትውጣ ካላችሁ እኔም ወንድሜን እንደቀበርኩ እወጣላችኋለሁ። እማዬ ሙች!” የመጨረሻ መሃላዬ እንደሆነ ያውቃሉ። ባይዋጥለትም
“እሺ እስከቀብር ድረስ ትቆይ” አለ።
ወደ ድንኳኑ ስንመለስ አማላይ በእርሷ ምክንያት እየተነታረክን እንደነበርም የረሳችው ትመስላለች። ወይም እንዳለችው ካልገደሏት ላለመውጣት ወስናለች ። ሳጥኑን በዛሉ እጆችዋ አቅፋ ትንሰቀሰቃለች።
የቀብሩ ቦታ ራሷን ስታ ወደቀች እና ሆስፒታል ወሰዷት። አመሻሽ ላይ ላያት ሆስፒታል ሄድኩ።
“እንዴት ነሽ?” አልኳት ስለሚባል እንጂ እንዴት እንደሆነች መገመት ከባድ አልነበረም።
“ደህና ነኝ። ይሄን ጉሉኮስ ከጨረሽ ትወጫለሽ ብለውኛል።”
ምን ብዬ ጋሼ ከቀብር በኋላ አይኗን እንዳላይ ብሏል ልበላት? ምን እያሰበችስ እንደሆነ ምን ብዬ ልጠይቃት?
“ሰምቻለሁ። አባትህ ያሉትን ሰምቻለሁ። አልፈርድባቸውም።” አለችኝ ራሷ። ተነፈስኩ።
“ምንም ነገር ሲያስፈልግሽ ግን እኔ እንዳለሁ እወቂ። ደውዪልኝ። በምችለው ሁሉ እረዳሻለሁ።” ካልኳት በኋላ ፊቷ ላይ የነበረው መቀዛቀዝና ተስፋ መቁረጥ የተናገርኩት ነገር እርባና ቢስ እንደሆነ አሳበቀልኝ።
“ምነው?”
“አይ ምንም። አመሰግናለሁ። በጣም ነው የማመሰግነው።” አለችኝ በቃ ጨርሰናል ሂድልኝ ባለበት ድምፅ
“ጉሉኮሱ ብዙ አልቀረሽም። ሰፈር ላደርስሽ ችላለሁ።”
“አብርሽን የገደለብኝ ሰው ቤት ተመልሼ የምገባ ነው የሚመስልህ?” አለችኝ ስለአባቷ የምታወራ አትመስልም።
“ታዲያ የት ነው የምትሄጂው? ”
“እኔ እንጃ አላውቅም። ብቻ እዛ ሰፈር አለመሆኑን አውቃለሁ።”
“እሺ ዘመድ ምናምን እዚህ አለሽ?”
“የአባቴ እህት ናት። ታብድብኛለች እሷጋ መሄድ አልችልም። በቃ አንተ አትቸገር እኔ ራሴን የምጥልበት ቦታ ፈልጋለሁ።” አለችኝ የጨነቃት ባለመምሰል። ተቀመጥኩ። ጠበቅኳት። ለተወሰነ ቀን ሆቴል እንድታርፍ አደረግኩ። እኔ የመጨረሻ አመት ዩንርስቲ ተማሪ ነበርኩ። ላስተዳድራት የሚያስችለኝ አቅም የለኝም። እሷ ደግሞ ገና የአስራሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። ድንኳን ከፈረሰ በኋላ የሆነውን ለነጋሼ ነገርኳቸው። እማዬ ትምጣና አብራን ትሁን አለች። ጋሼ ከማመኑ በፊት ከአብርሽም ከጋሼም ቀፍዬ ያጠራቀምኩትን ገንዘብ መጨረስ ግድ ነበር።
አብራን መኖር ጀመረች። አባቷ አስራ ሁለት አመት ተፈርዶባቸው ወህኒ ወረዱ። እናቷም “አባቷን ለዚህ ሁሉ ጣጣ ከዳረገችው በኋላ ጭራሽ አብራቸው ኖረች” በሚል አልቀብርሽም አትቅበሪኝ ብለው መልእክት ላኩባት። እየሰነበተ የሷ አብራን መኖር ትክክለኛ ነገር መሰለ። ሰፈሩም እስኪታክተው አውርቶ ረገበ። ወለደች። ባቢ የተወለደ ቀን ሁሉም ሀዘኑን ዘነጋ። ባቢ ሲያድግ አማላይ ባዳችን መሆኗን ረሳን። አብርሽ በእርሷ ምክንያት ከመሞቱ በላይ የአብርሽን ልጅ ያስታቀፈችን ገነነ። እማዬ ደስታዋ ቅጥ አጣ። እኔ ተመርቄ ስራ ያዝኩ። ባቢ አምስት አመት ሲሆነው እሷም ትምህርቷን ቀጠለች።
ዛሬ ላይ ሁሉም ቦታ ቦታውን ይዟል። ባቢ ዘጠኝ አመቱ ነው። አማላይ የአራተኛ አመት ሜድሲን ተማሪ ናት። እኔ? ከሁለት አመት በፊት የራሴን ቤት ተከራይቼ ብወጣም ሲናፍቁኝና ስሰክር ወደቤት ጎራ ማለቴን አልተውኩም።
*** *** *** *** *** ***

ከሰርኬ ጋር ሆኜ ስልኬ ጠራ። ሰርኬ ናታ!….. በፖለቲካ ንዝነዛዋ ሲኦል የምትሰደኝ ……… በሲጋራዋ ጭስ ሙቀት ገነት የምትልከኝ ……. እሷ! ……ከሶስት ወር ጅንጀና በኋላ “አልፈታሁትም እንጂ ባል አለኝ” ያለችኝ? አዎ እሷ!
ስልኬ ደግሞ ጠራ። አማላይ ናት። አንዴ ነው የምትደውለው። ካላነሳሁላት ደግማ አትደውልም። ራሴ ጉዳዬን ስጨርስ ደውልላታለሁ። ደግማ ከደወለች ነገር ነው። ልትጮህብኝ እንደሆነ እያወቅኩ አነሳሁት። አውቃለች ማለት ነው።
“ሄለው”
“የት ነህ?”
“ፓርላማ መሰስ ብዬ ገብቼ …….” አልሳቀችልኝም።
“አንተ መቼ ነው የምታድገው? እኔ እኮ ህፃን አይደለሁም። የራሴን ችግር በራሴ መፍታት እችላለሁ። ያስቀየመኝን ሁሉ ተደባድበህ እስከመቼ ነው የምትዘልቀው? ወይስ ምንም ነገር አላውራህ?”
ሁሌ ቃል እገባላታለሁ። ግን ጠብቄላት አላውቅም። ለእሷ አንዲት ዘለላ እንባ ምክንያት የሆነ ማንም ቢሆን በቃል ልግባባው አልችልም። ከፍቷት ነበር የነገረችኝ። ከወራት በፊት ወደድኩሽ ብሎ ሲፈርጥ ሲነሳ የነበረ አብሯት የሚማር ልጅ በቂ ምክንያት እንኳን ሳይነግራት ሲለያት አለቀሰች።
“ቆይ ምንድነው ችግሬ? ለምንድነው የቀረበኝ ሁሉ አብሮኝ የማይቆየው?” አለችኝ። እንዲህ ያሳመማትን ሰው መታገስ አልችልም ነበር። ፈልጌ አገኘሁት። ምን ያህል እንደጎዳሁት አላውቅም። ሰዎች ሲጯጯሁ ነው ከቦታው የጠፋሁት።

“አሁኑኑ እቤት ና! አሁኑኑ! አሮን አሁኑኑ ብዬሃለሁ።”…….. በሙሉ ስሜ ከጠራችኝ በብዙ ተናዳብኛለች ማለት ነው።
” እሺ” ብቻ አልኳት

የገደለ አባትሽ የሞተው ባልሽ (ክፍል አራት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...