Tidarfelagi.com

የኢትዮጲያውያን ገና በአል

የገና (ልደት) በዓል በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቀኖና መሰረት ከዘጠኙ ዐብይ በአላት ውስጥ አንዱ በአል ነው። እለቱ በትንቢተ ነቢያት የተነገረለት የሰውን ልጆች በጥንተ ተፈጥሮ የፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ አሁን ደግሞ በሐዳስ ተፈጥሮ ለመፍጠር ማለት ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ የተወለደበት እለት ነው።

የልደት በዐል የሚከበረው በየአመቱ ታህሣሥ ፳፱ (29) ቀን ሲሆን በዘመነ ዮሐንሥ ግን (የዘመነ ጳጉሜን ስድስድት ስለሆነች) በዐሉ ታህሣሥ ፳፰ (28) ቀን ይከበራል። ይህም የተጀመረው በአፄ ዐምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት ነው ይባላል። የልደት በዓልከጾም ዘመን ጋር የተያያዘ ስለሆነ ገሃድ የለውም፤ የማይፆሙ ሰዎች ግን ዋዜማውን ብቻ ገሃድ ብለው ይፆሙታል።

በገና በዓል በተለያዩ አካባቢዎች ወንዶች የገና ጨዋታ የተሰኘውን ባህላዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ይስተዋላሉ።

የገና ጨዋታ

የገና ጨዋታ

የተለያዩ መንፈሳዊና ባህላዊ አከባበር ከሚከበርባቸው ስፍራዎች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ጃንሜዳ ተብሎ የሚታወቀው ገናን ነው፡፡

የገናን ባህላዊ ጨዋታን ስንመለከት አስቀድሞ የቡድን አባላት የሚሆኑ ሁለት ሰዎች ይመረጣሉ፡፡ ሁለት ሁለት ተጫዋቾች ወደ አባቶች ይቀርቡና በምርጫው ወደ ቡድን ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሚያስፈልገው የተጫዋች ቁጥር ሲሞላ ወገን ወገናቸውን ይዘው በዱላ ቀልጣፋ የሆኑ ተጫዋቾች ጥንጓን( መጫወቻ ኳሱ) ወደፊት እንድትቀጥል ይመቷታል ወይም ይመልሷታል፡፡ ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ በጨዋታው ስለሚሰጡ ጥንጓን ከእግር መካከል በገባች ጊዜ ከሰው እግር ጋር ደርበው ስለሚመቱ የእግር መሰበር በዚህም ሳቢያ ወገን ለይተው እስከመፈናከት ይደርሳሉ፡፡ በንጉሳውያን ዘመን የመኳንንቱም አሽከሮች፣ የንጉሡና የንግሥቲቷ አሽከሮች የጌቶቻቸውን ስም በጉብዝና የሚያስጠሩት በባህላዊው የገና ጨዋታ ነው፡፡

ጨዋታው በመንደር ልዩነት ከሆነ የታች አምባ ቡድን ሀምሳ ተጫዋቾች ቢሆኑ የላይ አምባ ቡድን ሰባ ሆነው ቢጫወቱ የሚከለክል ደንብ አልነበረም፡፡ ጨዋታው በመጨረሻ ፀብ ስለሚያነሳ ብዙ ጊዜ ጉዳት ያጋጥማል፡፡ ጥንጓም ኃይለኛ ለጊ በመታት ጊዜ ዐይን እስከ ማጥፋት ትደርሳለች፡፡ ተጫዋቾች “በሚና” ብለው በሚጫወቱበት በቆልማማ ዱላ ቢደባደቡም የሚገላግል ዳኛ አልነበረም፤ ጨዋታውን በሚመለከቱ አባቶችም በድብድብ ከመሳቅ በስተቀር ሽምግልናቸው ለገና ጨዋታ አልተለመደም፡፡ “እግር ይብሳል፣ ያንከላውሳል፡፡” እያለ ማስፈራራት፣ ራስን መቀወር ወይም እንቆራቆስ ብሎ እጅና እግርን በዱላው መምታት በገና ጨዋታ የተለመደ ነበር፡፡

የገና ጨዋታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች የታወቀውና በኦሊምፒክ የስፖርት በዓል ከሚደረጉ ውድድሮች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ጨዋታ ሆኪ በሚል ስም ይጠራል፡፡ ፈረንጆች የፊት አደጋን መከላከያ ዘዴ ይጠቀማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያገር ባህል ገና ጨዋታ በሚደርስ አደጋ ማንም ተጫዋች አይጠይቅም፡፡

በገና ጨዋታ አሸናፊ ለሆኑት ቡድኖች ፊሪዳና ጠጅ ተሰጥቷቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየዘፈኑ ሲሸልሉና ሲያቅራሩ ሜዳውን የጦርነት ድል ያገኙበት ያስመስሉት ነበር፡፡ ከሚዘፍኑትና ግጥሞች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

“ማታ ነው ድሌ፣
ይሄ ነው አመሌ፡፡
አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡
ኦ! ጉ! አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡
ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው፣
የአንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው፡፡
የብብቱ ሽታ፣ የመንፈቅ በሽታ፡፡
የጀርባው መርሬ፣ ያውላል ጥድ በሬ፡፡
ካስር ጋን አተላ፣
አይተርፈው በአንኮላ፡፡
እግርህ የሸረሪት ሆድህ የእንቁራሪት፣
ቀን እንደጠላሁ ና እንዳትመጣ ሌሊት፡፡”

ስድብ ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመኳንንቱና በነገሥታቱም ላይ ሊሰነዘር ይችላል፡፡ በሚደርስባቸው ስድብ ግን ምንም ዓይነት ቁጣና ቅጣት አያደርጉም፡፡

“በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፡፡” የሚለው የዘፈን ግጥም ይህን ባህል ይገልፃል፡፡
የገና ጨዋታ ከክርስትና ሃይማኖት በፊት ይዘወተር እንደነበርና በኢትዮጵያ ከታኅሣሥ የመኸር ወቅት ጋር የተያያዘ ባህል ነበረ፡፡ ከበዓሉ ጋር የተያያዘ ብዙ የስነቃል ግጥሞችን ይገኛሉ፡፡

“ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣
እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡
ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና፣
ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና፡፡
ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣
ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታኅሣሥ፡፡
በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣
እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ፡፡”

ምንጭ፡-

www.sewasew.com
bisrat-views.blogspot.com

4 Comments

  • zerugebremichael7@gmail.com'
    Zeru commented on January 6, 2016 Reply

    ቃለ ሂዎት ያሰማልን ፡ በዓሉ የሰላም ፡ የጤናና የፍቅር ያርግልን !!

  • Anonymous commented on January 6, 2016 Reply

    እንኳን በሰላም አብሮ አደረሰን መልካም በአል ለሁላችን !!!

  • solomong0924@gmail.com'
    ሰለሞን commented on January 6, 2020 Reply

    አመሰግናለው!

  • wwwliuelsisaylula@gmail.com'
    ልዑል ሲሳይ commented on January 7, 2022 Reply

    Thanks for learning us!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...