በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የተዛባ አስተሳሰብ አለ። ብዙ ሰው ዕውቀትንና ብቃትን ድግሪ ከመያዝና ካለመያዝ ጋር ይመዝናል። ድግሪ ሳይኖራቸው ዓለምን የለወጡ ተመራማሪዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ድግሪ ያለው ሁሉ ባለዕውቀት አይደለም። ይህ ማለት የድግሪን ዋጋ ማናናቅ አይደለም። መማር፣ መመራመር ተገቢ ነገር ነው። የዶክትርና ድግሪ ግን ብቻውን የብቃት ልኬት አይሆንም። ስንትና ስንት ዶክትርና በአፍንጫዬ ይውጣ የሚያሰኙ ድኩማን በሜዳው ላይ በፈሰሱበት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው።
በተለይ ወያኔ የድግሪን ዋጋ እጅግ ካረከሰው በኋላ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር የሚባል ማዕረግ ለኔ ትርጉም አልሰጥህ ብሎኛል። ከማዕረጉ ይልቅ ሰውየውን በተግባር ማየት እፈልጋለሁ።
አንድ ጊዜ የኢሳቱ አበበ ገላው አቶ ቆስጠንጢኖስ በርሄ የዶክተሬት ድግሪ እንደሌለው “የማጋለጥ ጀብዱ” በሠራ ጊዜ በቆስጢ ተግባር ባልደሰትም “ለቆስጢ ዶክትርና ምን ያደርግለታል?” ብዬ ራሴን ጠይቄአለሁ። ቆስጠንጢኖስ በርሄ ፒ ኤች ዲ ሊስራ ቢል አይደለም አንድ፣ አሥሩን እንደሚሠራ አውቃለሁ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ (undersecretary) ሆኖ የሠራ፣ ችሎታውን በአደባባይ ያስመሰከረ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በኩራትና ብቃት የሚያስተምር፣ ለአለምአቀፍ ድርጅቶች ብዙ የኮንሰልተንሲ ሥራ የሚሠራ ሰው እንደሆነ አውቃለሁ። ሌላ ቀርቶ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ የሚፅፋቸው መጣጥፎች ( በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በአለም አቀፍ አስተሳሰብ) የሚያመራምሩ ናቸው። ዶክተሬቱ ለጉራ ካልሆነ ለቆስጢ የሚጨምረው ነገር ያለ አይመስለኝም። የወያኔ ሥርዓት ስንቱን ገልቱ ዶክተር በሚባል ማዕረግ አምበሽብሾት አይተናልና ነው።
የዶክተሬት ነገር ከተነሳ በኢትዮጵያ አንቱ ከተባሉት ምሁራን ጥቂቶቹን እንጥቀስ።
ዕውቁ ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ የመጀመሪያ ድግሪ ብቻ ነበረው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተከበረ፣ አሻራውንም ጥሎ ያለፈ ሰው ነው። ማዕረጉ ረዳት ፕሮፌሰር (የዶክትርና እኩሌታ) ነበር።
በኢትዮጵያ አከራካሪው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የዶክትርና ድግሪ ያላቸውም። በሁለተኛ ድግሪ ነው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙት።
ደማሙ ብዕረኛ መንግሥቱ ለማ ድግሪ አልነበራቸውም። ከለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ሳይጨርሱ ነው ያቋረጡት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበበት ትምህርት ክፍል እስካሁን ድረስ አሻራውን እንደ መንግሥቱ ለማ ጥሎ ያለፈ ሰው ያለ አይመስለኝም።
ስመጥር የሥነ ልሳን ሊቅ ፕሮፌሰር ሀብተማርያም ማርቆስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ዘንድ የተከበሩ ነበሩ። ነገር ግን ዱክትርና አልነበራቸውም።
እውቁ ተመራማሪ ደሳለኝ ራህመቶ ዱክትርና የላቸውም። የኢትዮጵያን የግብርናና የመሬት ስሪት የሚያጠና ባለሙያ ደሳለኝን ሳይጠቅስ ማለፍ አይሆንለትም። በነገራችን ላይ ደሳለኝ የባለብዙ መስክ የዕውቀት ባለቤት ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመን የማያውቅ ያለ አይመስለኝም። ሰውየው የዶክትርና ወረቀት የላቸውም። ብቃታቸውና ዕውቀታቸው ላይ ማንም ጥያቄ አያነሳም።