Tidarfelagi.com

የየመኒዎች ጨዋታ

በዚህ ወቅት የቅርብ ጓደኛዬ የመኒው ኮሎኔል ሙሐመድ አል ሐይደሪ ነው። ረመዳንን በአብዛኛው አንድ ቤት ነበር ያሳለፍነው። አሁንም አብረን ነው የምንውለው። በተለይ ከሰዓት አብረን ስንጫወት ነው የምናሳልፈው። በርካታ ቁም ነገሮችንም ከእርሱ እየተማርኩ ነው። 
—-
ጦርነትን ሸሽቶ ከሀገሩ የወጣው ሙሐመድ አል ሐይደሪ ወደዚህች ከተማ የመጣው ባለቤቱ የገለምሶ ተወላጅ ስለሆነች ነው። የእርሷ አባት በልጅነታችን ቢስኪሌት እንከራየው የነበረው ጋሽ ፉአድ ናስር ነው።

እንደሚታወቀው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የመኒዎች በሀገራችን ይኖሩ ነበር። ታዲያ እነዚያ የመኒዎች በንግድ ከባድ የመሆናቸውን ያህል በጨዋታ አደገኛ ናቸው። እስቲ አንዳንድ ታዋቂ ጨዋታዎቻቸውን እናስታውሳችሁ።
—-
በ1967 በተካሄደው የዐረብ እስራኤል ጦርነት ወቅት ዐረቦች በደረሰባቸው ሽንፈት ተከፍተዋል። በኢትዮጵያ የሚኖሩ የመኒዎችም በጣም ተበሳጭተው ነበር። እናም የተለያዩ የሀገራችን ዜጎች ወደ የመኒዎች መደብር እየሄዱ ይለክፏቸዋል።

ኢትዮጵያዊው: “አንተ ባለ ሱቅ፣ የእስራኤል ሸሚዝ አለ?”

የመኒው: “አባትና እናትህን ረግጦ የገዛው ጣሊያን ሸሚዝ አለ”

(ጣሊያን ኢትዮጵያን አልገዛችም። የመኒው ለለከፋው መልስ ለመስጠት ሲል ነው “ረግጦ የገዛው” የሚል የንዴት መልስ የሰጠው)።
—–
የመኒው ተከሰሰ። ፍርድ ቤት ቀረበ። ዳኛው ክሱን አነበቡለት።

ዳኛ: “መደብርህ ፅዳት የለውም፣ ሸረሪት ተገኝቶበታል”
የመኒው: “ያ ዳኛ! ይሄ ዓይነት ሸረሪት ነው ወይስ ሌላ ዓይነት ሸረሪት?
(በፍርድ ቤቱ ግድግዳ ላይም ሸረሪት ነበረበት! ሃሃሃሃሃ)።
—-
ረፋድ ላይ ነው። ወቅተል ሐራራ ነበር። የመኒው ኢጀበና ስላላደረገ መናገር አስጠልቶታል። አንድ እቃ ገዥ ወደ መደብሩ ገባ።

“የፋኖስ ብርጭቆ ፈልጌ ነበር”
“የለኝም”
“ይሄው አለ እኮ”
“የለኝም አልኩህ”
“ኧረ እያየሁት? ለምን አትሸጥልኝም?”

የመኒው ተናደደ። እናም የፋኖሱን ብርጭቆ ካለበት አንስቶት ባፍጢሙ መሬት ላይ ወርወረውና ሰባበረው። ከዚያም ገዥውን እንዲህ ብሎት ጠየቀው።
“አሁንስ ብርጭቆው አለ?”
(ይህኛው በጣም ነበር የሚያስቀኝ። ክርስቲያኗ ፍቅረኛዬ ለምላት ልጅ በነገርኩበት እለት ሳቋን ማቆም አቅቷት ነበር)።
—–
በሀገራችን ነጋዴዎችና ከተሜዎች ዘንድ ተዘውታሪ የሆኑ የየመን አባባሎችን ልጨምርላችሁ!!

ሹፍ ኡመሃ ወዘዊጅ ቢንተሃ (እናቷን አይተህ ልጅቷን አግባ)
የውም ዐሰል፣ የውም በሰል (አንድ ቀን ማር፣ አንድ ቀን ሽንኩርት)
ኢዛ ከሠረ ጠባኽ ፈሰደል መረኽ (አብሳይ ሲበዛ ወጥ ይበላሻል)
ከማ ተዲኑ ቱዳን (አትፍረድ ይፈረድብሃል)
ሓሪብ ሚነል መውት ደኸለ ሐድረመውት (ሞትን ሽሽት ወደ ሞት ማዕከል ገባ)
ኢተቂ መረን ሚን ዐደዊከ፣ ወ አልፍ መራ ሚን ሰዲቂከ (ከጠላትህ አንድ ጊዜ ተጠንቀቅ፣ ከወዳጅህ ግን ሺህ ጊዜ ተጠንቀቅ)
አል ወቅት ሰይፉን፣ ኢንለም ቱቅጠዕ ቢህ የቅጠዐክ (ጊዜ ሰይፍ ነው፣ ካልቆረጥክበት ይቆርጥሃል)።
—–
ተማም
አፈንዲ ሙተቂ
ገለምሶ ምዕራብ ሀረርጌ
June 11/2019

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...