Tidarfelagi.com

የዝምድና ታሪክ

በታሪካችን የብሔረሰብ ማንነት በተዋልዶ ብቻ ሳይሆን በተለምዶም የሚገኝ ነበር።
በቅርብ ርቀት ከማውቀው ከጎጃምና ከወለጋ ታሪክ ምሳሌ ላምጣ።
አንድ ኦሮሞ ከወለጋ በዘመቻ በንግድ ወይም በምርኮ አባይን ተሻግሮ ወደ ጎጃም ይዘልቅና በዛው ቀልጦ ይቀራል እንበል። ክርስትና ተነሥቶ የጥምቀት ስም ይዞ ዳዊት እየደገመ ፤ እንደ ዓለሙ አጋ በገና እየደረደረ እስክስታ እየጨፈረ ተቀባዩን ሕዝብ መስሎ ይኖራል። በጀግነነት ወይም ባስተዳደር መላ ብልጫ ካሳየ ደግሞ ጭፍራ ይመራል። ከቀናውም ሰፊ ግዛት ያስተዳድራል።

የዘመነ መሳፍንቱ የጎጃም ዳሞት አገውና ሜጫ ጌታ የነበረው ደጃዝማች ጎሹ ወደ አማራ ከተቀየሩ ዘመዶች የተገኘ ነው። የሱ ቤተሰቦች እስከራስ ኃይሉ ድረስ ገዝተዋል።የጎሹን ኦሮሞ ትውልድ ቻርለስ ቤኪ በሰፊው ጽፎታል ። ያገራችን የዜና መዋእሎችም ባለፍ ገደም ጠቆም አድርገውታል ። ለምሳሌ አንዱ የዜና መዋእል ጸሐፊ የጎሹን አባት የዘውዴን ጀግንነት ሲያወሳ“ እንዘ ኢይፈርህ ምንትኒ ለዝንቱ መስፍን ። እስመ አልቦ ዘይትማሰሎ እንበለ አቡሁ ደጃዝማች ቱሉ ቀዳሚ ዘተብሃለ በዘመነ ንጉሥ አድያም ሰገድ ይሉ አይሉ የታለ ቱሉ ዘሞተ ቀቢሮ ወዘተረግዘ ጸዊሮ ግእዘ መንገለ ግሽ ርእሰ ግዮን ” ይላል(ይህ መስፍን ምንም አይፈራም። ይሉ አይሉ፤ የታለ ቱሉ፤ የሞተ ቀብሮ የተወጋውን ተሸክሞ ወደ ግሽ ግዮን ራስ ወጣ ከተባለለት ካባቱ ከደጃዝማች ቱሉ በቀር የሚመስለው የለም)

በተቃራኒው አንድ ክርስትያን ጎጃሜ ወይም አማራ በግድም ሆነ በውድ ወደ ወለጋ ከዘለቀ በጉዲፈቻ ወደ ኦሮሞነት የመለወጥ እድሉ ሰፊ ነበር ። በጉዲፈቻው ወደ ኦሮሞነት ከተለወጡ ጎጃሜዎች ዝነኛው ገመ ሞራስ ይባላል ።ገመ ሞራስን በጉዲፈቻ ያሳደገው አንድ የታወቀ የቦረና ቤተሰብ እንደሆነ ተገልጿል። አሳዳጊው ሲሞት ገመ ሞራስ ሀብቱን ወርሶ ፤ ደራ ከተባለ አገር ነፍጥ እና ነፍጥ ተኳሽ ቅጥረኞችን ሸምቶ ጉዱሩንና አካባቢውን ሰንጎ ገዝቷል።
ጥምቀትና ጉዲፈቻ ተመዛዛኝ የጥቅል ማንነት መለወጫ መሳርያዎች ናቸው።
አንደኛው መሣርያ ካንደኛው የከበረ እንደነበር ለማሳየት መሞከር ከንቱ ድካም ነው።
የማንነት ለውጥ ለመኖር የሚደረግ ትግል አንድ ገጽታ ነው። በጦርነት የተያዘ ምርኮኛ ወይም እግር የጣለው መንገደኛ በማያውቀው አገር ሲደርስ ሁለት ዋና ዋና እድሎች ነበሩት። ወይ ተመንጥሮ ይጠፋል፤ አለያም አሸናፊውም መስሎ ባሸናፊው ክንድ ሥር ተጠልሎ ኑሮውን ይገፋል።
እናማ ወዳጄ ! ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፉ ከምድረ ገጽ የተደመሰሱ ህዝቦችን ስታስብ ፤በየትም በኩል በየት ተርፈህ ይቺን የማለዳ ጸሐይ መሞቅ መታደልህን ስታስብ “ተመስጌን ይህንንስ ማን አየብኝ “ ለማለት አይቃጣህም?
ምስሉ የገመ ሞራስ ነው።

የዝምድና ታሪክ – ሁለት

 

Menilikበምስሉ ላይ ምኒልክና የሸዋ መኳንንት ይታያሉ ፤ በቀኝ በኩል ጫፍ ላይ ቆሞ የሚታየው ድቡልቡል ሰውየ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አያት ደጃዝማች ጉዲሣ ነው። የዚህን መስፍን ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ባጭሩ የዘገበው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር የነበረው ህሩይ ወልደሥላሴ ነው። የ”ህይወት ታሪክ“ በሚል ርእስ በ1914 ባሳመው መጽሐፉ፤ ”ወልደሚካኤል“ በሚል ርእስ ሥር እንዲህ ብሎ ይጀምራል፤ “ ደጃዝማች ወልደሚካኤል ፤አባ ጉራች፤ ጉዲሣ ወልደሚካኤል ፤ የንጉሥ ሳህለሥላሴ አማች። እሳቸውም የራስ መኮንን አባት ናቸው፤ ገጽ 86)ዝርዝሩ ይቀጥላል። ይህ መጽሀፍ ከተጻፈ ከአርባ አመት በኋላ የተጻፈው የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል“ ቼ በለው” የቀኃሥን አያት ስም ዞር አድርጎ ”ወልደሚካኤል ጉዲሣ እንደሆነ ጽፏል።

ስለሰውየው የተጻፉትን ነገሮች በግሌ መርምሬ ፤ ጉዲሣ ወልደሚካኤል የአንድ ሰው ስም መሆኑን ደርሸበታለሁ። ጉዲሣ የተወላጅነት ስም ሲሆን ወልደሚካኤል የጥምቀት ስም ነው።
የምኒልክ አያት ንጉሥ ሣህለሥላሴ ልጃቸው ተናኘ ወርቅን ለጉዲሣ ድረዋል። ከሁለቱ ግኑኝነት የተፈሪ አባት መኮንን ከነሉሉ ዱብ ብሏል ማለት ነው።
በሳህለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሸዋን ቤተመንግሥት ለመጎብኘት የታደሉ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ጸሐፊዎች ይህንን ጋብቻ በጉዞ ማስታወሻቸው መዝግበውት ይሆን ብየ ያቅሜን ገለጥ ገለጥ ማድረግ ጀምሬ ነበር።Maurice Tamisier እና Edmond Combes የተባሉ የፈረንሳይ መንገደኞች ይቺን ነገር ጣል አርገው አልፈዋል፤
Le Lendemain de notre arrv ée à Ankober ,SahleSellassi ,qui avait promis l’une de ses filles en marriage à un Galla converti ,l’envoya chez son futur époux ,qui gouvernait une province à plusieurs journées de la capitale.
ትርጉም በስለሺ፤
“አንኮበር በገባን ማግስት ሳህለሥላሴ ከሴት ልጆቹ አንዲቱን ላንድ የተጠመቀ ኦሮሞ ለመዳር ቃል ገብቶ ኖሮ ከመዲናይቱ ብዙ ቀን መንገድ የሚርቅ አገር ወደ ሚገዛው እጮኛዋ ሸኛት ፤ ” ይሉና የነበረውን አጀብ በሰፊው ይዘግባሉ።
የተጠመቀው ኦሮሞ የዶባው ገዥ ጉዲሳ ወልደሚካኤል ይሆን? ልጂቱስ ተናኘ ወርቅ ትሆን ?
ዋናው ጉዳይ ወዲህ ነው፤ በኢትዮጵያ የነበረው የባላባት ወግ ባውሮፓ ከነበረው ዘረኝነት ወግ በጣም የተለየ ነበር። በግለሰብነቱ ከተርታው የተለየ ብልጫ ያሳየ ሰው ለከፍተኛ ማእረግ ይመለመላል፤ የንጉሥ ልጅ ያገባል ፤ እድል ከቀናውም ንጉሥ ይወልዳል። ባህልን በጌቶች ባህል የማስገበር ዝንባሌ ቢኖርም“ ደምህ ከደሜ” እንዳይቀላቀል የሚያሰኝ የዘረኝነት ፖሊሲ አልነበረም።
በመጨረሻም ! ብሄርብሄረሰቦች ሆይ ተጣበሱ ! ተካለሱ ! በጥላሁን ጠመኔ የተሠመረውን ድንበር አፍርሱ!
(የግርጌ ማስታወሻ ፤ ጥላሁን የስብሐት ገብረእግዚኣብሄር ”ሌቱም ኣይነጋልኝ ገጸ- ባህርይ ነው። ለመደባደብ ሲፈልግ በሱና ባባላጋራዎቹ መካከል ወለል ላይ የጠመኔ ድንበር ያሰምራል

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...