Tidarfelagi.com

የዛኔውና የዛሬው ጷግሜ 5 አንድ ናቸዉን?

ጷግሜ 5 በኢትዬጽያ ታሪክ ዉስጥ የራስዋ ድርሻ ኢንዲኖራት ካደረጉ ክስተቶች መሃል የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት አንዱ ነበር። ምንም እንኳን ንጉሱም የካቲት 19/1966 ለተነሳባቸው ህዝባዊ አመፅ መፍትሄ ይሆናል በሚል ስልት የጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሀብተወልድን ካብኔ አፍርሰው በእንዳልካቸው መኮንን የሚመራ አዲስ ካቢኔ በተማሪዎችና በወታደሩ ግፊት ቢያቋቋሙም የአብዮቱ ድል የማይቀር መሆኑን የሚያሳዮ ክስተቶች ይከናወኑ ይዘዋል፤ በየፊናው የተለኮሰው እሳትና የተዳፈነው ፍም መሄጃ መቀመጫ አሳጥቶ ሲያበቃ የዘውድ አገዛዙን ልሶ ላይመለስ የቀበረዉን መስከረም 2/ 1967ን አስከተለ።

ምንም እንኳን ከየካቲት 66 እስከ መስከረም 2 በነበረው የለዉጥ ማእበል ጊዜ ዉስጥ ብዙ ሰው ለውጥ መምጣቱን የተቀበለ ቢሆንም የንጉሱ ከስልጣን መውረድ ሀገሪቱን የማያልቅ ፈተና ውስጥ ይከታታል ብሎ ማመኑ አልቀረም።

ከዚህም አልፎ እንዲያውም በብዙ የዋህ የሀገሬ ሰው አስተሳሰብ መሰረት የንጉሱ መውረድ መሬት መንቀጥቀጥ እና ሲብስም ፀሃይን ከኢትዮጵያ ምድር የሚያጠፋ ክስተት እንደሚሆን ያምን ነበር ማለት ይቻላል።

ታድያ ደርግ ይህንን የህዝቡን አምልኮ የሚመስል ፍራቻ ለማስወገድና ንጉሱን ማስወገድ ፀሃይ የሚያጠልቅ ሳይሆን ይልቁንም ለኢትዮጵያ ፀሃያማ ቀንን የሚያመጣ መሆኑን በማሳየት የህዝቡን አመለካከት ለመለወጥ ይረዳ ዘንድ(ያው ስራቸው አሻጥር የተሞላበት ቢሆንም) የተሳካ ስራ ተሰራ። በዚህም እንደተፈራው ፀሀይ ከኢትዮጵያ ምድር ሳይሆን ከንጉሱ ጎጆ ላትመለስ እንድትጠልቅ ተደረገ። ይህንንም ካስከተሉት ዋንና ጉዳዮች መካከል በጻግሜ 5 1966 የተከናወነው ድርጊት ይጠቀሳል።

የደርጉ ጊዜያዊ አስተዳደር በጷግሜ 5 ላይ የወሎን ድርቅ በተመለከተ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደሚያቀርብ ማስታወቂያ ሰርቶ የህዝቡን ጉጉት አነሳሳ
፤የሰዉም መነጋገርያ ይህ ብቻ ሆነ። እቤቱ ራድዮና ቴሌቭዥን ያለው በጊዜ ተመቻቸ፣ የሌለው ደግሞ በየጎረቤቱና ሊሰማ በሚችልባቸው ቦታዎች በተጠንቀቅ ተሰየመ።

የተባለው ሰአት ደርሶ የንጉሱና የህዝቡ ኢትዮጵያ የተለያዩና ፈጽሞም የማይተዋወቁ መሆናቸዉን በሚያሳይ መልኩ የወሎውን ድርቅ ከንጉሱ ልደት አከባበር ጋር እያነፃፀረ ሰዎችን ስሜታዊ በሚያደርግ መልኩ በማቅረብ የዘውዱን አገዛዝ አረመኒያዊነት ህዝቡ እንዲቀበል አደረገ። (ምንም እንኳን ብዙም ሳይቆይ እራሱ ደርግ አረመኒያወዊነቱን በጅምላ ግድያ፣ በቀይ ሽብርና በሌሎች ግድያዎችና አፈናዎች ቢያሳይም።)

ይህ ሲጀምር እዉነታ ላይ የተመሰረተ የደርግ የፕሮፓጋንዳ እስትራቴጂ በትክክል ተሳክቶ አብዛኛው ህዝብ «ንጉሱ ለምኔ?» ያለበት ደረጃ ላይ ያደረሰ ሲሆን የዘውዳዊው አገዛዝ መውደቁ ያስፈልጋል ብሎ የማያምነው ክፍል እንኳን አገዛዙ መጥፎ መሆኑን፣ ሊሞቱለትና ሊከላከሉለት የሚገባ እንዳልሆነ ሳያስገነዝብ አልቀረም፤ ለዚህም ማሳያው የ1967ቱ የአዲስ አመት አከባበር ከሌላው ግዜ እጅግ የቀዘቀዘ መሆኑ ነበር። ህዝቡ «ወገን እያለቀ የኛ አመትባል ማክበር ምን ደስታን ይሰጣል?!!!» እንዲል የተገደደበት ወቅት ነበርና።

የደርጉም ጊዜያዊ አስተዳደር ይሄን አጋጣሚ ተጠቅሞ «ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ!!!» የሚለውን የዘመናት ብሂል ወደጎን በመተው በወረሀ መስከረም 2/ 1967 ንጉሱን አውርዶ ለክብራቸው በማይመጥን ቮልስዋገን ጭኖ ከቤተመንግስት አውጥቶ ላይመለሱ አስወገዳቸው።

ታድያ ያ ንጉሱንና የዘመናት ጭቆናን ያስወገደው ለውጥ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ስርዓትና ዲሞክራሲያዊነት ለማሸጋገር ጥሩ አጋጣሚ የነበረ ቢሆንም እዚህ መዘርዘር በማያስፈልጉ ምክንያቶች የተነሳ እድሉን አጥተነዋል። ቢሆንም ጨለማውን የንጉሳዊ አገዛዝን ከሀገራችን አሽቀንጥረው ለጣሉ የህዝብ ልጆች የማያልቅ ክብር ይገባቸዋል ባይ ነኝ።

ዛሬስ?! እነሆ ዛሬ ጷጉሜ 5/2011 ነው። ዛሬም ያለፈውን ክፉት ማጋለጥ ላይ ችግር ያለብን አይመስለኝም። ነገር ግን አሁን ያለብንና ከታሪክም ተምረን በአግባቡ ልንመልሰው የሚገባው ጥያቄ – «ክፉ ስርዓትን ለማስወገድ የምንጠቀመውን ብልሀት መልካም ስርዓትን ለመፍጠር በስራ ላይ እናውለው ይሆን?» የሚለው ነው!!!

የጊዜ ቀመር ስለሆነ ያኔም ጷግሜ 5 ነበር ዛሬም ጷግሜ 5 ነው ፤ ነገም ሌላ መከሰቱ አይቀሬ ነው። ቀጣዩ ቀን ግን የባሰ አልያም ተመሳሳይ ከቻልን ወይም አዲስ እንዲሆን ማድረጉ የኛ ፈንታ ነው!

ቸር ያሰማን!

መልካም አዲስ አመት!

ይህ ፅሁፍ የዛሬ አመት ተፅፎ ለዛሬ እንዲሆን በትንሹ የተቀየረ ነው!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...