Tidarfelagi.com

የኬዱክ እጆች

( ማሳጅ በባሊ፣ ኢንዶኖዢያ)

-የቱሪስት ሃገር ስለሆነ ኑሮ እሳት ነው…እኔ ደግሞ ደሞዜ በጣም ትንሽ ነው። በወር ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ይከፍሉኛል ግን አይበቃኝም…የቤት ኪራይ ዘጠኝ መቶ ሺህ እከፍላለሁ…

ኬዱክ ናት እንዲህ የምትለኝ። ኬዱክ በስመጥሩ ሆቴል ውስጥ ያለ ዝነኛ የስፓ አገልግሎት መስጫ ሰዎችን በማሸት ትተዳደራለች። 2.3 ሚሊዮን? የብር ምንዛሬው ነገር አሁንም ናላዬን ስለሚያዞረው በቅጡ ላዝንላት አልቻልኩም።

ጥቂት ካሰብኩ በኋላ ግን ከሁለት መቶ ዶላር እንደማይበልጥ ተረድቼ በተአምረኛ እጆቿ እያፍታታች ያለችው ሰውነቴ ተኮማተረ።

-ቢሆንም መስራት ነው…ደግሞ በጣም ጎበዝ ነሽ አልኳት።
ከአንጀቴ ነው። እጆቿ እያሹኝ ነው። እጆቿ እየፈወሱኝ ነው። ማሳጅ ወዳጅ ስለሆንሁ አዲስአባ አለ የተባለ ቦታ፣ ጥሩ ነው ያሉት ሰው ጋር ምንም ከፍዬ እታሻለሁ። እንዲህ እድል ገጥሞኝ ወጣ ስልም አሳድጄ ከምፈልጋቸው ቦታዎች ዋናው የማሳጅ ቦታ ነው። እንዲህ ያለ ችሎታ ግን አይቼ አላውቅም፡

ኬዱክ ልዩ ናት።

ዝም ብላ በእጆቿ አስማት መስራት ጀመረች። እኔም አመም ሲለኝ ኣ…ደስ ሲለኝ እሰይ…ስል ቆየሁና ከመፍታታቴ ብዛት እንቅልፍ ሸለብ ያደረገኝም መሰለኝ።
– እንቅልፍ ሊወስደኝ ነው ኬዱክ አልኳት። ሳቅ አለችና ቅድም እግሮችሽን በባህር ጨው ሳጥብሽ ጀምሮ መተኛት እንደፈለግሽ ገብቶኛል። ጥሩ እየሰራሁ ነው ማለት ነው…እባክሽ አሁንም ዘና በይ ሚስ አለማየሁ አለችኝ።
አለማየሁ የአያቴ ስም ነው። እንደማንኛውም ሀበሻ ከሀገር ስወጣ ፓስፖርት ላይ በሰፈረው የአያት ስሜ ስለምጠራ ዛሬም ሚስ አለማየሁ ነኝ።
እንዳለችኝ ዘ….ና አልኩ። ሸለብም ሳያደርገኝ አልቀረም።

ምን ያህል እንደቆየሁ ሳላውቅ ወደ አቅሌ ስመለስ ኬዱክዬ ጀርባዬ ላይ ዱቅ ብላለች።

ማለቴ ቆማለች። ቆማለች ስል ከጀርባዬ አይደለም። እኔ ተኝቼ እሷ ጀርባዬ ላይ ቆማለች።

ደንገጥ አልኩና …በሕይወቴ ከአንደበቴ ይወጣሉ ብዬ አስቤ የማላውቃቸውን ቃላት አረፍተነገር አድርጌ ተናገርኩ።

– እንዴ…ለምን ጀርባዬ ላይ ቆምሽ? አልኳት ሳቄ እየቀደመ። አትከብድም ግን ነገሩ ግራ ሆነብኝ። በእጆቿ ፈንታ እግሮቿ ላፕቶፕ ላይ ተጎንብሶ በመሰንበት የጓጎለ ሰውነቴን ሲያፍታቱ እየተሰማኝም ቢሆን ነገሩ ግራ ሆነብኝ።
– የማሳጁ አካል ነው ሚስ አለማየሁ…

ከተመቸኝ ምንተዳዬ ብዬ እላዬ ላይ አክሮባት ስትሰራ ዝም አልኳት።

ትንሽ ቆይታ ወረደችና በእጆችዋ ቀጠለች። እየሰራች በሷ ጀማሪነት ወሬ ቀጠልን

– እናንተ ሃገር ማሳጅ አለ?
– እ?
– ሃገራችሁ አፍሪካ ?
( ከየት ነሽ ስትለኝ ኢትዮጵያን ስጠራ እንደ አብዛኛው የዓለም ህዝብ ዓለም ካርታ ላይ ስላላገኘችን አፍሪካ ብዬ ተገላግዬ ነበር)
– አፍሪካ ሀገር አይደለም…አህጉር ነው…
– እሺ አህጉራችሁ ማሳጅ አለ?

በጥልቅ ተነፈስኩና ይሄን ሁሉ ብር ከስክሼማ ትምህርታዊ ውይይት አላደረግም አልኩና
– አዎ አለ …
– ውድ ነው?

ኦፋ ኬዱክ ደሞ!

– ደህና ነው ( ትእግስቴ እያለቀ)
ነገሬ ገባት መሰለኝ ዝም ብላ ማሳጁን ቀጠለች። (አዎ የኔ እናት…አንቺ የሚያምርብሽ በእጆችሽና በእግሮችሽ ስታወሪ ነው)

ደቂቃዎች ሲያልፉ ይሉኝታ ያዘኝና፣
– ሌላ ሀገር ኖረሽ ታውቂያለሽ? አልኳት
– አዎ..ዱባይ እና ቱርክ ሰርቻለሁ
– ኦ…ከዛ ሀገርሽ ለመኖር ተመለስሽ?
– ኮንትራቴ አልቆ ነው። መመለስ አልፈለግኩም ነበር..
– አሃ…ገባኝ…
ፀጥታ እና ግሩም ማሳጅ ብቻ። ብዙ ሳትቆይ እንደገና ጀመረች
– ደቡብ አፍሪካ ስራ አግኝቼ ነበር ሚስ አለማየሁ..
– ተይ እንጂ..! በጣም አሪፍ…ለምን አልሄድሽም ታዲያ…?
– የስራ ፈቃድ እምቢ አሉኝ
– ውይ..እንግዲህ ደጋግሞ መሞከር ነው
( ለካ አፍሪካም አውሮፓና አሜሪካን ቢያቅታት ሌላ ሌላውን ታንቆራጥጣለችና!…ታንኪው ሳውዝ አፍሪካ!)

– ልትረጂኝ ትችያለሽ ሚስ አለማየሁ..?
– እ?
– ፈቃዱ ላይ…ምናልባት ብትረጂኝ ብዬ ነው…
– እ…እኔ እኮ ሃገሬ እዛ አይደለም…ኢትዮጵያ ነው ኬዱክ (ሳቄ በጣም መጣ)
– አፍሪካ…አይደል?
– አዎ አፍሪካ ነው ግን አፍሪካ እንዳልኩሽ ሃገር አይደለም..አህጉር ነው
– ግን አንቺ ሀገርሽ እዛ ነው አይደል…?
– ብዙ ሃገር ነው ያለው…ልክ እንደ እስያ…እስያ ውስጥ ጃፓን አለ…ቻይና አለ አይደለም?
– አዎ
– ስለዚህ እኔ አንዱ ጋር ነኝ…አፍሪካ ትልቅ አህጉር ነው (ደከመኝ)
– ግን ላንቺ ሃገርሽ አፍሪካ ነው አይደል?

(ይህች ልጅ እግዜር እንዲህ ያለ እግር እና እጅ ላይ ያለነገር ሰጥቶ አላጎበዛትም። በዚህ ካልበላች በምን ትበላለች ብሎ ነው…እንዴት ያለ ነገር ነው ወገን!)
– አዎ… አዎ ነው
– ስለዚህ ትረጂኛለሽ?
– አዎ…ከቻልኩ እረዳሻለሁ… (ምናባቴ ላድርግ…ሌላ ማምለጫ ቀዳዳ አሳጣችኝ)
– ውይ…ታንኪው ሚስ አለማየሁ…አሁን ተገልበጪ…

ተገለበጥኩ።

ተገለባብጬ ማሳጁ በፍስሃ ሲያበቃ አመስግኛት ልብሴን መለባበስ ጀመርኩ።
ከተፈጠርኩ እንዲህ ተዝናንቼ አላውቅም። መላው ሰውነቴ በሽብሸባ እና በዝማሬ እያመሰገነኝ መሰለኝ።
አዲስ አበባ የገጠሙኝ ማሳጆች አሰብኩ። ባለ 450 ብሩ በጣት ጠንቆል ጠንቆል፣ ባለ 300 ቤቱ ሴቶችን በ‹ሼም› ብቻ ለማስመሰል የሚያሸው ‹ሃፒ ኢንዲንግ› ማሳጅ ቤት፣ ደህናውን ሰውነት አጣሞ አጣሞ ለውጋት የሚዳርገው ባለ 600 ብሩ ‹‹ቲሹ ማሳጅ››፣ ለሳምንት ስብርብር አድርጎ የሚያስረው ባለ ስትራፖው የ200 ማሳጅ፣ ድንጋዩ ጠባሳ የሚስቀረው ባለ 700 ብሩ ‹ሆት ስቶን ማሳጅ›…

ልዩነቱን እያጣጣምኩ አንዲት ቀልድ ትዝ አለችኝ።

ሁለት ሴቶች በመንገድ እየሄዱ አንድ አህያ የአንዷን ሴት አህያ ‹‹ልብ ልቡን እያለ ››የልቧን ሲያደርስላት ደረሱ። አህዩት በፍስሃ ታናፋለች። ሴቶቹ ትንሽ ቆመው የሚሆነውና ካዩ በኋላ አንዷ ምን ትላለች? ‹‹አቤት…አቤት….! መደረጉንስ ይህች ብስብስ ተደረግኩ ትበል። የእኛስ ጨዋታ ነው››

እኔም ከኬዱክ ማሳጅ በኋላ ‹‹መታሸቱንስ የኢንዶኔዥያ ህዝብ ታሸሁ ይበል። የእኛስ ጨዋታ ነው›› ብያለሁ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...