እዚህ ጓዳዬ ውስጥ የከሸፈ አብዮት አለ!
የጓዳዬን አብዮት ለማክሸፍ፣
አድማ በታኝ አልተላከም! አስለቃሽ ጭስ አልተጣለም! ጥይት አልተተኮሰም! ከክሽፈቱ ጀርባ አንድ ነገር ብቻ ነበር፤ ሚስቴ!!
አብዮት እባላለሁ። ወጣት ነኝ፤ አብዮት ውስጤ የሚፈላ ወጣት! “ተነሳ፣ ተራመድ ” በምልበት እድሜ፣
“ተኛ፣ ተቀመጥ ” የተባልኩ የአብዮት አቀንቃኝ።
“ከሀገር የሚበልጥ ዓላማ የለም” እላለሁ።
“ከትዳር የገዘፈ ምኞት ከንቱ ነው” ትለኛለች።
“ልጄ የሚያድገበትን ሀገር የተሻለ ለማድረግ ራሴን እሰጣለሁ ” ስል፣
“ለልጃችን አስብ እንጂ፣ ያለ አባት ልታስቀረው ነው? ለኔም እዘንልኝ፣ አባት የሌለው ልጅ ላሳድግ? ” እንባዋን ታፈሰዋለች! ደሜን ላፈስላት የነበረችው ሀገር፣ በሚስቴ እንባ ማፍሰስ ምክንያት ሃሳቧ ይመክናል።
***
ከያንዳንዱ የከሸፈ አብዮት ጀርባ ሚስት አለች ብዬ ማመን ጀምሬያለሁ። የከሸፈ አብዮት ሌላ ስሙ፣ “ሚስት ” ይመስለኛል።
ብዙ አደባባይ እንዳይወጣ፣ በትዳር ገመድ የታሰረ ወንድ ይታየኛል።
:
የሴት ልጅ የህይወት አላማ፣ በትዳር አይነ እርግብ የተከለለ ነው። ያለነፃነት ካለፈው እድሜዋ በላይ፣ ትዳር ሳትይዝ ሊያልፍ ያለው እድሜዋ ያሳስባታል። የመጀመሪያው አላማዋ ትዳር፣ የመጨረሻ አላማዋ ልጅ ይሰኛል! ይሄ ሴቴ ርዕዮት ነው። ወንዴ አይደለም!
:
ወንድ ልጅ፣ ከእናቱ የተለማመደውን “ሴቴ” የህይወት ምልከታ፣ ተሸክሞ ወደ ሚስቱ ይሄዳል። ሚስቱ ያንን ታስቀጥላለች። ይሄንን ሳስብ፣ “ወንድ ልጅ ሴቶች የሚጫወቱት ኳስ ነው ” እላለሁ።
“ሴቶች ወደተለሙት ግብ የሚሄድ ኳስ! ከዛ ሴቴ ግብ ይቆጠራል፤ ትዳር!! ” ይህንን እሱም ማወቁን እጠራጠራለሁ።
ሀገር በትዳር ፊት ትንሽ ናት?
ነገ፣ነፃነት በሌለበት ሀገር ውስጥ የወለድኩት ልጄ፣
“ምን ብለህ እንዲህ አይነት ስርዓት ወስጥ ወለድከኝ ” ቢለኝ መልሴ ምንድነው?
ነፃ ባልሆኑ ሰዎች የሚመሰረት ትዳር አላማው ምንድነው? ነፃ ያልሆኑ ልጆች መፈልፈል??!
:
የ Zorba ጥያቄ በሃሳቤ ይመጣል፣
“Only people who want to be free are are human being. Women don’t want to be free. Well, is a women a human being? ”
.
.
ልቤ ላይ ገሞራ አለ! “ያዝ “ብሎ መነሳት ያምረኛል
ወዲህ፣ የሚስቴ “ትዳራችን “ይይዘኛል።
የሚስቴ “ልጃችን” ያደናቅፈኛል።
እንባዋ ይስበኛል!
“የዜጎች ደም በከንቱ እየፈሰሰ እንዴት ዝም ብለህ ቁጭ በል ትይኛለሽ? ” ስላት፣
“እና ሌላው ጠግቦ ሞተና አንተም ደም ልታዋጣ ያምርሃል? ለውጥ ለማይመጣው ቤተሰብህን በትነህ መቅረት አምሮህ ነው? ቆይ ለምንድነው እማታስበው?! ቤተሰብህን… ” ለቅሶዋን ትጀምራለች። ላባብላት እጠጋለሁ።
ገሞራዬ በእንባዋ ይሸረሸራል። በጣቶቿ መዳሰስ፣ ሃሳቤ ከአገር ወደ አልጋ ይወርዳል!
:
እዛ፣ አብዮቱ የሚያነሳው አጥቶ ተኝቷል!!
***
መንግስትን መጣል የፈለጉ ፓርቲዎች፣ ለሴቶች የሚሆን የቅስቀሳ ፕሮግራም መቅረፅ እንዳለባቸው አምናለሁ። ሴቶች ህይወትን ከትዳር አሻግረው ካላዩ፣ አብዮቱ የየትኛውንም አባወራ ደጅ አይሻገርም።
“ምንድነው ሞባይልህ ላይ አቀርቅረህ የምትፅፈው? “… ሚስቴ ናት።
“ምንም ”
“በል እሱን ተውና፣ ልጁን አንዴ ተቀበለኝ! ”
:
:
ሀገር ከትዳር ሲያንስ፣ አይደለም አብዮት ማንሳት፣ ስለ አብዮቱ መፃፍ ይከብዳል
One Comment
ቆንጃ አስትማር ስለሆን ቀጥሉበት