Tidarfelagi.com

የኤርትራ ህልም (ክፍል ሁለት)

የኢትኖግራፊ ሽርሽራችን በኤርትራ ምድር ቀጥሏል። አሁን ወደ ምዕራብ ኤርትራ ተሻግረናል! ባርካና ጋሽ የሚባሉት ቆላማ አውራጃዎች እዚህ ነው ያሉት። አቆርዳት፣ ተሰነይ፣ አሊጊደር፣ ኡምሐጀር፣ ባሬንቱ የተሰኙት ከተሞች በቆላው ምድር ውስጥ ተዘርግተዋል። ኩናማ፣ ናራ እና ቤጃ የሚባሉት ብሄረሰቦች እዚህ ነው የሚኖሩት። የአካባቢው ዋነኛው ህዝብ ግን ለኛ በጣም ቅርብ የሆነውን ሳቂታውን የቤኒ አምር ወጣት ያስገኘው የትግረ ህዝብ ነው።

የትግረ ህዝብ በውስጡ በርካታ ጎሳዎች አሉት። ከሁሉም የሚበረክተው ግን የቤኒ አምር ጎሳ ነው። ህዝቡ የሚነጋገርበት የትግረ ቋንቋ ከሴማዊ ቤተሰብ ነው የሚመደበው። ለዚህ ቋንቋ በጣም የሚቀርበው በደጋው ኤርትራና በኛዋ የትግራይ ክልል የሚነገረው ትግርኛ ነው። እነዚህ ሁለት ቋንቋዎች ከጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋ ነው የተወለዱት። ይህንን ቋንቋ ከ35 በመቶ የማያንሰው የኤርትራ ህዝብ ይናገረዋል። የትግረ ቋንቋ ከኤርትራ ሌላ በሱዳንም (ከሰላ አካባቢ) በስፋት ይነገራል።

ትግረና ትግርኛ በጣም ከመመሳሰላቸው የተነሳ እንግዳ ለሆነ ሰው አንድ ዓይነት ቋንቋዎች ሊመስሉት ይችላሉ። በተጨማሪም ለትግርኛ ተናጋሪዎች የትግረ ቋንቋን መልመድ በጣም ቀላል ነው ይባላል። የትግረ ተናጋሪም ትግርኛን በቶሎ መልመድ ይቀለዋል። በመሆኑም ከጠቅላላው የኤርትራ ህዝብ 50% የሚሆነው ሁለቱንም ቋንቋዎች መናገር ይችላል (ይህ ቁጥር ትግርኛ ብቻ የሚናገሩትን፣ ወይንም “ትግረ” ብቻ የሚናገሩትን አይጨምሩም)።

ምዕራባዊው ቆላ ኤርትራዊያን በጣም የሚያደንቋቸውን እንደ ሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ፣ ሙሐመድ ኢድሪስ እና ኢድሪስ ገላውዴዎስን ያፈራ መሬት ነው። በዚህ ሰሞን ልቤን ያሸፈተው የትግረ ልጅ ግን “አሕመድ ሼክ” ነው። አሕመድ ሼክን አወቃችሁት አይደል? አዎን! “ባቡሬይ”፣ “ኢላ ሰርጎ” ወዘተ.. እያለ በማይጠገበው የትግረ ምት የሚያዜመው ተወዳጅ ድምጻዊ ነው። አንድ ኤርትራዊ ወዳጃችን “ኤላ ሰርጎ”ን ሲፈታልን `ከጀርባው ፌሎሶፊ አለው” ነው ያለኝ። ነገሩ እንዲህ ነው።

የትግረ ሴት ለምትወደው አንድ ሰው (ለባሏ) እንጂ ለማንም ጸጉሯን አትገልጠውም። ስለዚህ ጉብሊቷን ልጅ የወደደው አሕመድ ሼክ በተዋቡ ግጥሞች እያወደሳት ዘፈነላትና ፍቅሩ ልቧ ውስጥ ዘልቆ መግባቱን ለማረጋገጥ ጸጉሯን ማየት ጀመረ። እርሷም ግጥሞቹን ከሰማችለት በኋላ ጸጉሯን ገልጣ አሳየችው። ድል አድራጊው ወዲ ሼክም ይዟት በረረ። “ኤላ ሰርጎ! ኤላ ሰርጎ” እያለ ነጎደ!
——
ሰሜን ኤርትራ!
ተወዳጇ የከረን ከተማ እዚህ ነው ያለችው! የሀረርጌዋ የድሬ ዳዋ ከተማ መንትያ እህት የምትመስለው ውቢቷ የሰሜን ፈርጥ! በቪዲዮ አይቻት ውበቷን አደነቅኩላት! አበቦቹ! ቤቶቹ! መንገዶቹ ሁሉም ውብ ናቸው (ፎቶውን ተመልከቱት)። ከትግራይ የተገኘው ዝነኛው ብርሃነ ሃይለ አንድ ላይ በነበርነበት ዘመን ለከረኗ ጉብል እንዲህ ብሎላታል።

ሸው በሊ ብለነይ ብለነይ
ዝለሊ ብለነይ ብለነይ
አሊሊ ብለነይ ብለነይ
አቲ ጓል ከረነይ ብለነይ

አዎን! ቢለን ከከረን ከተማ ጋር ስሙ የሚጠቀስ ብሄረሰብ ነው። ቋንቋው ከኛው የአገው ቋንቋ ጋር አንድ ዐይነት ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው አንባቢ ሊመራመር የሚገባው። በወሎና በጎጃም የሚኖረው አገው ምን ሊያደርግ እዚያ ሄደ?… መቼ ነው እዚያ የሄደው?… መላምት ከመዘብዘብ በስተቀር ማንም ሰው ይህንን እንቆቅልሽ በሚያመረቃ ሁኔታ ሊፈታው አልቻለም። ኤርትራና እኛ አንድ ነን የሚያሰኘኝ እንዲህ ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ ስላለን ነው።

ቢለን ውብ ባህል ያለው ህዝብ ነው። በዚህ ህዝብ ባህል መሰረት ሴቶቹ ካገቡ በኋላ ጸጉራቸውን መሰተር ግድ ነው። ህዝቡ የቢለን ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆንም የትግረ ቋንቋንም ይጠቀማል። ትግርኛም በስፋት ይነገራል። በጣም ታዋቂ የሆነው የቢለን ተወላጅ “ዑመር እዛዝ” ነው። የጀብሃ ጦር ከመፍረክረኩ በፊት የሁለተኛው ዞን አዛዥ እንደነበረ ከዚህ በፊት ጽፌ ነበር።

ከከረን ሽቅብ ወደ ሰሜን ስናመራ ታሪካዊቷ አፋቤት አለች። ጄኔራል ታሪኩ አይኔ የሚመራው ናደው እዝ እዚህ ነበር የሰፈረው። የቀይ ኮከብ ዘመቻ ዋና አምባም ይህ ነበር። ከአፋቤት ወደ ሰሜን ስንበር ንዳዳማውና አስቸጋሪው የሳህል መሬት አለ። በሰህል እምብርት ላይ የኤርትራ ገንዘብ መጠሪያ ለመሆን የበቃችሁ “ናቅፋ” አለች። በዓሉ ግርማ እንደተረከልን ከሆነ ሳህል ማለት እሳት ነው። ነገር ግን ሰዎች ይኖሩበታል። ከብቶች ይሰማሩበታል። ተክልም ይበቅልበታል። እዚህ አካባቢ በብዛት የሚኖረው ህዝብ “ረሺዳ” ይባላል (አንዳንዶች “ራሻይዳ” ይሉታል፤ ስህተት ነው፤ ትክክለኛው አጠራር “ረሺዳ” ነው)።

የ“ረሺዳ” ህዝብ ከሌላው የኤርትራ ህዝብ የሚለይበት በርካታ ነገሮች አሉት። ለምሳሌ ይህ ህዝብ ከሳዑዲ ዐረቢያ ተነስቶ ወደ ኤርትራ የገባው በቅርብ ዘመን (በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ) ነው። በዚያ ወቅት የአሁኗ ሳዑዲ ዐረቢያ አልነበረችም። ሀገሩ ሁሉ በጎሳዎች የተከፋፈለ በረሃማ ምድር ነበር። ከነዚህ ጎሳዎች አንዱ አል-ረሺድ ይባላል። ይህ የአል-ረሺድ ህዝብ የአካባቢው የበላይ እንዲሆን በኦቶማን ቱርክ ተወሰነ። አብዛኛው ህዝብም ለነርሱ አደረ። “አል-ሱዑድ” የሚባለው ቤተሰብ ግን “አሻፈረኝ” አለ። “ራሴ በረሃውን ጠቅልዬ መግዛት ስችል ለምን በአል-ረሺድ ጎሳ የበላይነት አድራለሁ” በማለት አንገራገረ። በሁለቱ መካከል ጠብ ተነሳ። በመጀመሪያው ላይ የአል-ረሺድ ጎሳ አሸነፈ። አል-ሱዑዲዎች ወደ ኢራቅ ሸሹ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን የአል-ሱዑድ ቤተሰብ በእንግሊዞች ደጋፊነት ራሱን አጠናክሮ መጣ። በአል-ረሺድ ጎሳ ላይም ድልን ተቀዳጀ። በዚህም የተነሳ የዐረቢያ በረሃ ለአል-ረሺድ ጎሳ አባላት ሲኦል ሆነ። ረሺዳዎች እየተያዙ በጅምላ ታረዱ። ንብረታቸው ተዘረፈ። በፊት ይረዳቸው የነበረው የቱርኮች መንግሥት በራሱ ችግር በመወጠሩ ምንም ሊያደርግላቸው አልቻለም። በመሆኑም ከእልቂቱ ለመዳን ሲሉ ባህር እያቋረጡ ወደ አፍሪቃ ምድር ተሰደዱ። በሱዳንና በኤርትራ መኖሪያቸውን ቀለሱ።

እንግዲህ ረሺዳዎች ከዘር ማጥፋት ወንጀል ለመሸሽ ወደ ኤርትራ የመጡ ተፈናቃዮች ናቸው ማለት ነው። በኤርትራ ውስጥ ንጹህ የዐረብ ዝሪያ የሚባሉት እነርሱ ናቸው። የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውም ዐረብኛ ነው። በዚህ ህዝብ ባህል መሰረት ለአካለ መጠን የደረሰች ማንኛዋም ሴት ፊቷንም ሆነ ጸጉሯን መሸፈን ግዴታዋ ነው። በዓሉ ግርማ በኦሮማይ ውስጥ ሲተርክልን “ማንኛውም የረሺዳ ባል የሚስቱን ፊት ገልጦ የሚያይበትን ሰው አይፈልግም” በማለት የተናገረውም የባህላቸው አንድ አካል ነው።
——-
አሁን ወደ ምስራቅ ኤርትራ ተሻግረናል። ብርኽቲ የሆነችው ምጽዋ እዚህ ነው ያለችው። ብርሃነ ሃይለ “ሸው በሊ ብለነይ” የተሰኘውን ዘፈን ሲቀጥል ምጽዋን እንዲህ ይላታል።

“አብ ዋሊድ ማሳዋ
ኩለ ሊየን ሒልዋ”

ትርጉሙን በትክክል ባላውቀውም “የምጽዋ ልጆች ሁሉም ጣፋጭ ናቸው” የሚል መልዕክት እንዳዘለ ይገባኛል። የምጽዋ ልጆች ቆንጆ ናቸው ተብሎ እየተደጋገመ ተነግሮላቸዋል። ከወደብ ከተማ የተገኙ በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ስልጣኔና ልዩ ልዩ ባህሎች ነበርሱ ላይ ሲነፍስ ይታያል።

ምጽዋ በጣም ውብ ናት። በተለይም ኪነ-ህንጻዋ ብዙ ተብሎለታል። ከዑስማናዊያን ቱርኮች ዘመን ጀምሮ ብዙ ገዥዎች ሲፈራረቁባት የነበረች መሆኗ በከተማዋ የሚታየውን ኪነ-ህንጻ እንዳሳመረው ምሁራን ያስረዳሉ።

ኤርትራዊያን ምጽዋን ይወዷታል። እኛም እንወዳታለን። ነገር ግን ወደዚያ ለመድረስ የሚሻ ሰው እንደ እሳት የሚፋጀውን ሙቀቷን መቻል አለበት-ከተማዋ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሙቀት ካላቸው ስፍራቸው አንዷ ናትና። የዚህች ከተማ ህዝብ ኑሮውን ከአየር ጸባዩ ጋር እንዲጣጣም አድርጎ ቀይሶታል። በመሆኑም አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወነው ከምሽት እስከ እኩለ ሌሊት ባለው ጊዜ ነው። ታዲያ ከተማዋ ለዘወትር እንደጋለች አትቀርም። በዓመት ሁለት ጊዜ ሙቀቱ ጋብ ይልና ጤናማው አየር ይነፍስባታል። ይህም ከጥር-የካቲት ባለው ጊዜ እና በሀምሌ ወር ነው። በነዚህ ወራት ከተማዋን የሚጎበኘው ቱሪስት በጣም ይጨምራል። በቀድሞው ዘመን ቀዳማዊ ኃይለሥላሤም ከተማዋን ለመጎብኘት የሚመጡት በነዚህ ወራት ነው (እርሳቸው ያሰሩት ቤተ-መንግሥት እስከ አሁን ድረስ አለ)።

ምጽዋ በወደብነት አገልግሎት መስጠት የጀመረችበት ዘመን በትክክል አይታወቅም። የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው ከተማ ቀመስ ሰፈራ ነበር። ይሁንና እስከ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ እንደ ወደብ ሲያገለግሉ የነበሩት ከምጽዋ አጠገብ የነበሩት ጥንታዊያኑ “ዙላ” እና “አዱሊስ” ነበሩ። የምጽዋ ተፈላጊነት ጉልህ ሆኖ የተከሰተው የባህር መደቡ በ1508 በዑሥማናዊያን ቱርኮች (Ottoman Turks) በተያዘበት ወቅት ነው። ከቱርኮቹ በማስከተልም ግብጾችና የኢጣሊያ ወራሪዎች ተፈራርቀውባታል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን ከተዋሃዱ በኋላ ምጽዋ ከፍተኛ እመርታ ማሳየት ጀምራ ነበር። ከ1970ዎቹ መግቢያ ጀምሮ ግን የጦርነት ቀጣና ሆነች። የሻዕቢያ ሀይሎችና የኢትዮጵያ ሰራዊት ከፍተኛ እልቂት የተፈጸመባቸውን ጦርነቶች አካሂደውባታል። በተለይም በ1982 (እ.ኤ.አ. 1990) በተካሄደው ጦርነት ከሁለቱም ወገን በአስር ሺህ የሚቆጠር ሰራዊት መርገፉን ሁኔታውን በቅርበት የተከታተሉ ወገኖችና የዐይን ምስክሮች ገልጸዋል (የሀምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልባኖን “አይ ምጽዋ” አስታውሱት)። የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምም “ለከፍተኛ ሽንፈትና ኪሳራ የዳረገን ውድቀት ያጋጠመን በምጽዋ ነው” በማለት ተናግረዋል።

የድሮው ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) የአሁኑ “ህዝባዊ ግንባር ንዴሞክራሲን ንፍትሒን” (ህግዴፍ) ምጽዋን የተቆጣጠረበትን ዘመቻ “ኦፕሬሽን ፈንቅል” በማለት ይጠራዋል። ምጽዋ የተያዘችበት ዕለትም (የካቲት 20) በየዓመቱ ይከበራል። በርካታ ህዝብ ወደ ምጽዋ ከሚጎርፉባቸው ዕለታት መካከልም አንዱ ይህ “የኦፕሬሽን ፈንቅል” መታሰቢያ የሚከበርበት ቀን ነው።

ምጽዋ የብዙ ህዝቦች መኖሪያ ናት። ዋነኞቹ ነዋሪዎች ግን የአሳውርታ፣ ሳሆ፤ እና አፋር ብሄረሰቦች ተወላጆች ናቸው። በከተማዋ በዋናነት የሚነገረው ቋንቋ ዐረብኛ ነው። የሻዕቢያ መስራች ተብሎ የሚታወቀው ዑስማን ሳልህ ሳቤ የተወለደው በምጽዋ አጠገብ ካለችው ሂርጊጎ የተባለች አነስተኛ መንደር ነው። ኢብራሂም አፋ፣ ረመዳን መሐመድ ኑር እና ዓሊ ሰዒድ አብደላን የመሳሰሉት የህግሓኤ (ሻዕቢያ) እውቅ ኮማንደሮችም የምጽዋ ልጆች ናቸው።

ከምጽዋ ወደብ ዝቅ ብሎ ጥንታዊቷ የአዱሊስ ወደብ ትገኛለች። ይህች የወደብ ከተማ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የተጓዦች መግቢያና መውጪያ ነበረች። የጥንቱ ሮማዊያንና ግሪኮችም በደንብ ያውቋታል። አጼ ካሌብ ወደ ደቡብ ዐረቢያ ሲዘምት ወታደሮቹን በመርከብ ያስጫነው ከዚህች የወደብ ከተማ ነው። በሀገራቸው ከፍተኛ በደል ያጋጠማቸው የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮች ከጥቃቱ ለመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በአዱሊስ በኩል ነበር ያለፉት። ሌላም ብዙ ታሪክ ተስተናግዶአል-በአዱሊስ።
———
ከምጽዋ ወደ መሀል ኤርትራ ለመጓዝ መንገዱን ስንጀምር በቅድሚያ የምናገኘው የሳሆ ህዝብን ነው። ይህ ህዝብ በስተደቡብ በኩል ከሚጎራበተው የአፋር ህዝብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የኢኮኖሚ መሰረት አለው። ሁለቱም በከብት እርባታ ነው የሚተዳደሩት። ሁለቱም ኩሻዊ ቋንቋ ነው የሚናገሩት። በአለባበስ ግን ሳሆን ከአፋር በቀላሉ መለየት ይቻላል። ለምሳሌ የሳሆ ተወላጅ የሆነ ሰው አፋሮች የሚታጠቁትን “ጊሌ” የሚባለውን ረጅም ቢላዋ አይታጠቅም። የሳሆ ሰው የሚያሸርጠው ሽርጥም ከአፋር ሽርጥ ረዘም ይላል። ከዚህ በተጨማሪም ሳሆ ብዙ ጊዜ ከእጁ ጦር አያጣም። ታዲያ የሳሆ ቋንቋ በትግራይ ክልል ጉሎ መኸዳ ወረዳ የሚኖረው የኢሮብ ህዝብ ከሚናገረው ቋንቋ ጋር ተመሳሳይ ነው። ኢሮብና ሳሆ የሚለያዩት በሚከተሉት እምነትና በኢኮኖሚ መሰረታቸው ነው። ሳሆ ሙሉ በሙሉ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው። ኢሮብ ግን በአብዛኛው ክርስቲያን ነው። ከዚህ ውስጥ የሚበዙትም ካቶሊኮች ናቸው። በሌላም በኩል የኢሮብ ህዝብ አራሽ ገበሬ ይበዛዋል። ከላይ እንደተገለጸው የሳሆ ህዝብ በከብት እርባታ ነው የሚተዳደረው።

ሳሆን ስናልፍ ደግሞ ትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ በስፋት የሚኖርባቸውን የአከለ ጉዛይ፣ ሰራዬ እና ሐማሴን አውራጃዎችን እናገኛቸዋለን። በኤርትራ ውስጥ ካሉት ብሄረሰቦች መካከል ብዙ ቁጥር ያለው (50 % የሚሆነው) ይህ ትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ ነው። ይህ ህዝብ በባህሉም ሆነ በቋንቋው ከኛው የትግራይ ህዝብ ጋር ይመሳሰላል። ህዝቡ በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ መሆኑም ከትግራይ ህዝብ ጋር ያመሳስለዋል። ይሁንና ቋንቋው ባለፉት በርካታ ዘመናት ከጣሊያንኛ፣ ከዐረብኛ እና ከትግረ ቋንቋዎች ጋር በመወራረሱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነገረው ትግርኛ የተለየ ዘዬ ሊሆን በቅቷል።

አጅግ በርካታ የሆኑ የኤርትራ ከተሞች ያሉት በዚህ ክልል ነው። ጊንዳዕ፣ ነፋሲት፣ ሰገነይቲ፣ ደቀምሐረ፣ መንደፈራ (አዲ ዑግሪ)፣ አዲኳላ፣ ሰንዓፈ፣ ደባሩዋ ወዘተ… እዚህ ነው የሚገኙት። በመሀከላቸው ደግሞ አስመራ ጉብ ብላ ትታያለች። ከከተሞቹ መካከል የሚበዙት በጣሊያን ዘመን የተቆረቆሩ ናቸው። በሰራዬና በአከለ ጉዛይ አውራጃ ውስጥ ግን የጥንቱ የአክሱም ዘመነ መንግሥት ታዋቂ ከተሞች የነበሩትን እንደ “ሀውልቲ” እና “መጠራ” የመሳሰሉ መንደሮችን ማግኘት ይቻላል። በነዚህ ከተሞች ፍርስራሽ ስር ገና ያልተነካ ድልብ የአርኪዮሎጂ ሀብት አለ። ወደፊት ቆፈረን የምናወጣቸውን ማቴሪያሎች የህዝቦቻችንን አንድነት የሚመሰክሩ ቋሚ ቅርሶች አድርገን ልጆቻችንን እናስተምራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
——-
ኤርትራን በኢትኖግራፊ ጉዞ እንዲህ ቃኝተናታል። ነገር ግን በዚሁ አናበቃም። ወደፊትም በተሻለ ዝግጅት ተመልሰን እንዘይራታለን። ለአሁኑ በዚሁ ይብቃን!!
ሰላም!!
—–
ነሐሴ 30/2006

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

One Comment

  • ruarodan@gmail.com'
    ፍጹም ኣረፋይኔ commented on June 29, 2018 Reply

    ውድ አፈንዲ! እሰይ! እሰይ! እንኳን ደስ አለህ! እነሆ ጎህ ቀደደ ። እንግዲህ ምጣና ናፍቆትህን ተወጣ። ከመጀመሪያዎቹ ደራሾች ትሆናለህ ብዬ አስባለው። እንደ ሙሽራ “መጺኻለይዶ መጺኻለይዶ ክጽበየካ” እያለች አስመራ ሽኮር (ባንተ አባባል “አስመራ ቀሽቲ”) ትቀበልሃለች ። ስለ ፍቅር ፣ ሰላም ፣ አብሮነት ፣ በፍቅሯ ነደህ ዘምረሃል ፣ለፍፈሃል ፣ ከትበሃልም ፣ለዚያውም በሹክሹክታ ሳይሆን በአደባባይ። ኤርትራ ደግሞ እጆችዋን ዘርግታ፣ መርሓባ ብላ፣ በፍቅር ወደ እልፍኟ ታስገባሃለች። እናማ ና! ናኝባት።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...