ነፃነት ያልነካው ትዳር እና ሀገር መፍረሱ አይቀርም ብዬሻለሁ። አልሰማሽም። አለመስማት የአፍራሾች ምልክት ነው። የማይሰሙ መንግስታት ሀገራቸውን፣ የማይሰሙ ባለትዳሮች ትዳራቸውን ያፈርሳሉ።
የቤቴ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነሽ። ሲበዛ ትጠረጥሪኛለሽ። ጥርጣሬሽን ለማረጋገጥ ንብረቶቼን ያለፍቃዴ ትበረብሪያለሽ፣ ልብሶቼን ትፈትሻለሽ፣ ቴክስቶቼን ከፍተሽ ለማንበብ ትሞክሪያለሽ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም እንዲህ ነው። ያለ ፍቃዳችን ይበረብረናል።
አዳሜ ስድስት ወር ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀብን ብሎ ይነጫነጫል። እኔ የዓመታት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ “ትዳር ” መስሎኝ የገባሁ ምን ልበል?
ሲጀመር ትዳራችን ውብ ነበር። ወይም ይመስል ነበር። እንደ አባዱላ ሂሳብ በስህተት የተሞላሽ መሆንሽን ለማወቅ ግን ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም።
አዎ ነፃነቴን ስትገድቢ መንገድ ወጥቼን ባልዘጋም ሳላናግርሽ ዘግቼሽ የማደር መብት አለኝ። ይሄንንም አልፈቀድሽልኝም። ምን ይዘጋሃል ብለሽ ጀምረሽ ሳልወድ ታናግሪኛለሽ። በቤቴ ያለሽ የመንግስት ካርቦን ኮፒ የምትመስይኝ ለዚህ ነው። መንግስታችንም እንዲህ ነው። ስናነገርም አይወድም። ዝም ስንልም አይወድም። እንዲሁ ባጠቃላይ አይወደንም ማለት ሳይቀል አይቀርም።
ሰሞኑን ደሞ ብሶብሻል። ለነገሩ አንቺ ብቻ አይደለሽም፤ መንግስትም ብሶበታል። እንዴት “ዱላህን ተወኝ ” ያለን ሕዝብ “የዱላ አዋጅ ” ያወጡበታል? ዱላ ስህተት ነው። እንኳን ዱላ አባ ዱላም ስህተት ነው። ሀገር እና ትዳር በስህተት አይመራም። ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል። ቁጭ ብሎ ለመነጋገር አዕምሮ ያስፈልጋል። አየሽ፣ ከዶላር እጥረቱ በላይ የአዕምሮ እጥረቱ ያሰጋናል። የማሰብ ክራይሲስ ከከረንሲ እጥረት ይከፋል።
ሰዓት እላፊ አይቻልም ብለሻል—እንደ አዋጁ። ከሌላ ሴት ጋር መልእክት በማንኛውም መልኩ መለዋወጥ ክልክል ነው ብለሻል፣ ልክ እንደ አዋጁ። እርስ በእርስ መቃቃር የሚፈጥሩ ምልክቶችን በእጅህ ፣በፊትህ ቁጣም ሆነ በዐይኖችህ አታሳየኝ ብለሻል፤ ልክ እንደ አዋጁ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጄ ነሽ። ይሄ ሕዝብ የሚያሳዝነኝ ለዛ ነው— እንኳን የመንግስት፣ የአንዲት ሚስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን ያህል እንደሚከብድ ስለማውቅ።
ጥሩ ትዳር ካገኘ የትኛውም ሰው ለትዳሩ ለመገበር ዝግጁ ነው። ጥሩ መሪ ካገኘም የትኛውም ሕዝብ ለመመራት ዝግጁ ነው። ስንጋባ እድሜ ልክ አብረን ለመኖር ዝግጁ ነበርን። እንደ ባለፈው ምርጫ መቶ ፐርሰንት መርጬሽ ነበር። እርግጥ አንቺ እንደ መንግስት ድምፅ አላጭበረበርሽም ነበር። እኔ ግን ተጨበርብሬያለሁ። እንዲህ መሆንሽን አላወኩም ነበር። ከመቶ ፐርሰንቱ በኋላ በኔ እና አንቺ ቤት እና በሀገራችን የሆነው አንድ ነው። በሌላ ሴት ቀይራት ቀይራት ይለኛል። ሕዝቡንም እንዲሁ መንግስትን በሌላ መንግስት የመቀየር ፍላጎት የጫነበት መንግስት ነው። ግን ትልቁን ቁጣ የሚቆጡት ተሳሳቾቹ ናቸው። አንቺም ትጮሂያለሽ። መንግስትም ይጮሃል። መጮህ የተሳሳቾች ስልት ይመስለኛል። ስህተቱን ድምፅ ለመንሳት ያለው አማራጭ እሱ ሳይመስለው አይቀርም። እኔ አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ደርሰናል ብዬሻለሁ። ሕዝብም መንግስትን እንደዛ ይለዋል አሉ። አሁንም ግን ጊዜ አላችሁ።
የመጀመሪያ እድላችሁ ረጋ ብሎ መነጋገር ነው። ረጋ ብሎ ያነጋገራችሁ ላይ ሁሉ መጮህ ማቆም አለባችሁ። የሰው ልጅ ትልቁ ስጦታ ነፃነት ማግኘቱ ነው።
ሀገር እንደ ቤት ነው። በዘልማድ አስተሳሰብ ስንሄድ መንግስት ባልን ይመስላል። ባህላዊው ባል በመሆኑ፣ ሚስቱ የሆነውን ሕዝብ በገባ በወጣ ቁጥር ይደበድባል! ጥሩ ባል ለቤቱ የሚያስብ ነው። አዕምሮ ያለው ባል ሚስቱ ላይ እጁን አያነሳም። የነፃነት ጥያቄ ነፃነትን በመንሳት አይመለስም፤ተመልሶም አያውቅም! ሊመለስም አይችልም!
****
****
“ያንቺው” ማለት የሚከብደኝ ያንቺ ባል!
ግልባጭ:- በዚህ ከቀጠለ መገልበጡ ለማይቀረው መንግስት!