ፖለቲካ ለመጻፍ አስብና “ አንተ በርገርህን እየገመጥህ ድሃውን ህዝብ ታበጣብጣለህ “ እንዳልባል እሰጋለሁ፤ ተዋናይና ሼፍ ዝናህብዙ የሚሰራውን ጭልፋ የሚያስቆረጥም ሽሮ እየበላሁ እንደማድር ብናገር ማን ያምነኛል?
አድምጡኝ፤ ከዛሬ ሃያ አመት በፊት ለአመት በአል ሜዳ ላይ ለተሰበሰበ ህዝብ የሚቀርቡ ጭውውቶቸ ትዝ ይሉኛል ፤ የጭውውቱ ገጸባህርያቱ ጉዋደኛሞች ናቸው፤ ወይም አባትና ልጅ ሊሆኑ ይችላሉ እንበል ፤ ደህና ሲያወጉ ይቆዩና ጭውውቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው ድንገት ይጣላሉ፤ ደራሲው በጭውውቱ መጠናቀቂያ ላይ ተአማኒነት የጎደለው ጠብ ነስንስ ያደርግበታል፤ ወድዶ አይደለም፤ ድራማው መጠናቀቅ አለበት ፤ መድረኩ ላይ መጋረጃ የለም፤ መብራት የለም፤ ሰለዚህ ያለው አማራጭ ተዋናዮችን አባራሪና ተባራሪ አድርጎ ከመድረክ ማሰናበት ነው።
እና ምርጫ ሲመጣ ትዝ የሚለኝ ይሄ ነው ፤ በፖለቲከኞች መካከል በወዳጅነት ሲካሄድ የቆየ ውይይት ምርጫው ማጠናቀቂያ ላይ ወደ ውረፋ ውንጀላና ማሰፈራሪያ ይቀየራል፤ ከዚያ ጉልቤው ድኩማኑን ወደ ቃሊቲ ወይም ወደ ዮሴፍ ቤተክርስትያን ጉዋሮ ያባርረዋል፤ ዘንድሮ ይሄ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
በምርጫ ውድድር ውስጥ መሸናነፍ ያለ ነው፤ ሽንፈትን በጸጋ መቀበል የሚለው ፉገራ እንኩዋ ይለፈኝ ፤ ሽንፈትን በቀጋ እንጂ በጸጋ የተቀበለ ህዝብም ሆነ ዜጋ ኖሮ አያውቅም ፤ ( ከንጦጦ ወይም ከብሄረ ጽጌ የተሻለ የጫካ ተሞክሮ ለሌላችሁ ለከተማ ልጆች፤ ቀጋ ማለት ጥቂት ፍሬና ብዙ እሾህ ያለው ተክል ነው ፤ በጥጋብ ዘመን እንደ ጦር መሳርያም ያገለግላል)
የታጠቀ የነቃ ህዝብ ያቸንፋል ይላል ሌኒን ፤ አንድ ድርጅት ትጥቅ ይኑረው እንጂ እንኩዋን ነቅቶ ተኝቶም ቢሆን ማሸነፉ አይቀርም፤ አውሮፕላን ማረፍያውን፤ ስልኩን ፤ ራዲዮኑን የመሳርያ ግምጃ ቤቱን የተቆጣጠረ ድርጅት ምን አቅብጦት ይሸንፋል? በአህጉራችን በተለይም ባገራችን ምርጫ ከተቃዋሚና በገዢው ፓርቲ የተሻለውን የመምረጥ ገዳይ አይደለም፤ ምርጫው በ(ሞት-እስር- ቶርቸር) እና በሕይወት መካከል ነው፤እና የመጀመርያውን የሚመርጡ እጅግ ጥቂት ናችው።
ተቃዋሚ ሆነህ ስትወዳደር ራእይህ አማናዊ( ሪያሊስት) ይሁን፤ መንግስት እሆናለሁ ሳይሆን የረባ መቀመጫ አግኝቸ የገዥውን ፓርቲ ስልጣን እገድባለሁ ብለህ አቅድ ፤ ህልምህ በተጋነነ ቁጥር ሽንፈትህም በዚያው ልክ መራር ይሆናል።
ስለህልም ሰለምኝታና ሰለ መንቃት ከተነሳ ላይቀር ጋዜጠኛ ወዳጄ የነገረኝ የፓርላማ ገጠመኝ ባዲስ መልክ ልገርብ
አንዴ ሻለቃ አድማሴ የሚባሉ ሽማግሌ ተቃዋሚ ነበሩ፤ ብዙ ጊዜ የኢህአዴግን ፖሊሲ አምርረው ይቃወማሉ፤አንዳንዴ ደሞ የፓርላማው መሰኮት ትንሸ ሰፍቶ አደረ ብለው ሊቃወሙ ይችላሉ፤ መለስ ዜናዊ በሽግግር መንግሰቱ ጊዜ ከኪሮስ አለማየሁ ጎፈሬ ትንሸ አነስ ያለ አፍሮ ነበረው ፤ ሻለቃ አድማሴ በተቃውሞ በወጠሩት ቁጥር በንዴት ሲነጨው ፤ ጠጉሩ ሟሟንደጨው።
የሆነ ጊዜ ላይ አንድ የኢህአድግ የገጠር ካድሬ በውል አበሉ ካዛንቺስን ሲያርስበት አድሮ ወደ ፓርላማው ይመጣል፤ ክርክሩ በሚጦፍበት ሰአት አጅሬ ጠረጴዛው ላይ እንደ ኩባያ ተደፍቶ ህልሙን በሲዝን እና በኢፕሶይድ ከፍሎ ይኮመኩማል፤ በመሀል ጭበጨባ ሞቅ ሲል ብትት አለና እጁን ተፈቀደለት ራዳር ውጭ ዘርግቶ ተንጠራራ፤ በጊዜው አፈ ጉባየ የነበረው ዳዊት መነጽር ደራርቦ የሚጠቀም ቢሆንም በመንጠራራትና እጅ በማውጣት መካከል ያለው ልዩነት መለየት ተስኖት ፤
“ እሺ እዚያ ጋ እጅህን ያወጣኸው፤ አስራ አምስት ደቂቃ ሰጥቸሃለሁ” አለው
ካድሬው አይኖቹን ባይበሉባው ፈትጎ ሲያማትር ያለበት ሁኔታ ከበድ ያለ መሆኑን አረጋገጠ፤ ከዚያ ደነገጠ፤
ብቻ እውር ድንብሩን
“ ቅድም ሻለቃ አድማሴ የተናገሩት ነገር ጸረ ዲሞክራሲ በመሆኑ ልንታገለው ይገባል ባይ ነኝ” ብሎ ቀባጠረ፤
የሚገርመው ደሞ፤ ዚያን ቀን ሻለቃ አድማሴ ያለወትሮአቸው” ሳይለንት ሞድ “ ላይ ነበሩ ‘
ይህን ሲሰሙ ብድግ ብለው እጃቸውን በተማጽኖ ዘርግተው
” የ ኢትዮጵያ ህዝብ ፍረደኝ ፤ አሁን ምን ተናገርሁ” ብለው ጮሁ፤
በማግስቱ ፓርላማው በቲሌብዥን ሲተላለፍ የሻለቃው አቤቱታ ተቆርጦ ቀርቶ ነበር፤
የታጠቀ ድርጅት ተኝቶም ቢሆን ያሸንፋል!