Tidarfelagi.com

የታጋቹ ማስታወሻ

ከፀሀይ በታች አሮጌ ነገር የለም ፤ ፀሃይ ራሷ በየሰኮንዱ ትታደሳለች፤
ከእንቅልፌ ተነሳሁ፤ ተንጠራራሁና አይኔን ባይበሉባየ ጠራርጌ ከእምብርቴ በታች ያለውን ቃኘሁት፤ አጅሬ ከኔ በፊት ቀድሞኝ ተነስቱዋል ፤ የዛሬው ደግሞ የተለየ ነው፤ እስክንድር ነጋ ንግግር ባደረገ ቁጥር ባንዲራ ይዞ ከጀርባ እሚቆመውን ሰውየ ራሱ እንዲህ አይቆምም ! ጠበቆ ጠብቆ ምንም የተዘጋጀለት ነገር እንደለሌለ ቁርጡን ሲያውቅ ተኛ! ምስኪን!

ያልጋ መውረጃ የለህም ? የሚል አንባቢ አይጠፋም!
ሲጀመር አልጋ ራሱ የለኝም ፤ በርግጥ እንደ ጎማ የሚነፋ ፍራሽ አለኝ ፤ የገዛሁት ሰሞን አንዴ ከተነፋ እስከ ሌሊት ሙሉ ያገለግል ነበር፤ አሁን ቀሳ ከወጣሁ በሗላ ግን ወፈርኩ፤” ወፈርኩ” የሚለው ቃል አነሰ ! ስጋየ ገነፈለ ብል ይሻላል ፤ ሁለት የቁም መስታውቶች ገጣጥሜ ካልሆነ በቀር ሙሉ ሰውነቴን ለማየት እያዳገተኝ ነው፤ ለሶስት ሰአት ያክል ከተኛሁበት ተንፍሶ ምንጣፍ ይሆናል ፤ እንደፈረደብኝ ተነስቼ እንደገና እነፋለሁ፤

ቁርስ መስራት ይጠበቅብኛል? ባለፈው “ አንድ ብርጭቆ ሩዝ በሁለት ብርጭቆ ውሃ ለሃያ ደቂቃ ከቀቀሉት ሁለት ብርጭቆ ሩዝ ያገኛሉ “ የሚል አነበብኩ፤ እንደዛ ከሆነ ለምን በደንብ አላባዛውም ብየ አንድ ብርጭቆ ሩዝ ባራት ብርጭቆ ውሃ ቀቀልኩ፤ ከሃያ ደቂቃ በሗላ ሩዝ ጣል ጣል ያለበት ሙቅ ውሃ ጠጣሁ፤

አንድ ቀን ደግሞ እንቁላል ጠበስኩ፤ከዛ ወደ አፍንጫየ አቅርቤ ባሸተው ምንም መአዛ የለውም፤ ትንሽ ቅመም ነሰነስኩበት፤ ይህም ሆኖ አፍንጫየ ላይ አቅርቤ ስምገው ምንም የለም ፤ ወድያው ሼፍ ዮሀንስ ጋ ደውየ የጠቆመኝ ቅመም ችግር እንዳለበት ነገርኩት ፤ “ ርግጠኛ ነኝ ፌስ ማስክህን ሳታወልቅ ነው ያሸተትከው? “ አለኝ፤ ውነቱን ነው ፤ ፌስማስኬን አድርጌ ከመዋል ማደሬ የተነሳ እንደ ፊት ቡግር ሁሉ ማውጣት ጀምሯል፤
ምግብን ሼፍ ዮሀንስ ይስራት! ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው ምግብ ስለደበረው እማይሞክረው አዲስ ነገር የለም፤ ባለፈው ሰይፉ ሾው ላይ ከሞሪንጋ ዱቄት ምን የመሰለ ላዛኛ ሰርቶ አስደምሞኛል፤ ይሄ ልጅ በዚህ አይነት ምርምሩን ከቀጠለ ሳያስበው ክትባቱን ሁሉ ሊያገኘው ይችላል፤

ምግብ ሲነሳ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ፤ ይዲዲያ የሚባል ዝነኛ ነቢይ ትዝ አላችሁ ? ሚያዝያ ላይ ኮሮና ይጠፋል ብሎ ተንቢዮ ነበር፤ ከዛ ወረርሽኙ እየባሰበት ሲመጣ ሚያዝያ እንዲራዘምለት ጌታን በፀሎት ጠየቀ ፤ በቀደም ቃለመጠይቅ ላይ ምን ሲል ሰማሁት “ መፅሀፍ ቅዱስን በጣም ከመውደዴ የተነሳ አንዱን ገፅ ቀድጄ በልቼ አውቃለሁ” ፤ እምደንቅ ነው ባክህ! እኔ በዚህ ምስክርነትህ ላይ የታየኝ ነገር ቢኖር ለመፅሀፍ ቅዱስ ያለህን ፍቅር ሳይሆን ለምግብ ያለህን ፍቅር ነው፤ ኪሎህ ራሱ ይሄንን ይመሰክራል፤ ለማንኛውም ክንዳችሁ ላይ የመፅሀፍ ቅዱስ ጥቅስ የተነቀሳችሁ ሰዎች ይሄን ሰውየ ተጠንቀቁት !

ለነገሩ ምግብ ላይ እኔም የዋዛ አደለሁም፤ ይሄው ፤ ገና ከምኝታየ ከመነሳቴ የፍሪጁን በር ከፍቼ ቆሚያለሁ ፤ የሚሳዝን አጭሬ ከተፍ አለልኝ!
አንድ ስሃን ሩዝ
ሁለት ሱካር ድንች
ፍሪጄን የሞላው
ይሄን ሁሉ ሲሳይ፤ ከማን ጋራ ልብላው?

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...