(ልጆቻችሁ፣ ልጆቻችሁ አይደሉም?)
ካህሊል ጅብራን “The Prophet” በተባለ ስራው “ስለ ልጆች ንገረን” ለሚል ጥያቄ በነብዩ አንደበት ይናገራል።
“your children are not your children”
ምን?
ልጆቻችሁ ልጆቻችሁ አይደሉም? እና የኛ ካልሆኑ የማን ናቸው? ነው ወላጆቻችን ናቸው? አትቀልዳ ካህሊል። እስቲ ትንሽ አብራራው።
“They are the son and daughter of life’s longing for itself,
They come through you but not from you”
የሕይወት ዓላማ ቧንቧዎች ናችሁ በለና?! የፍሰቱ ማስተላለፊያ እንጂ፣ የፍሰቱ ባለቤት አይደለንማ? ምክንያት ውጤትን “የእኔ ነህ” ማለት አይችልም? ብንሰማህም የምናደምጥህ አይመስለኝም። ተው እንጂ ያደግንበትን?
“You may give them your love but not your thought”
እንዴዴዴ! ምን ይላል ሰውዬው! እኛ እኮ ለልጆቻችን ከፍቅራችን ቀድመን ሃሳባችንን መስጠት ነው የለመድነው። የምንመኘውን፣ መሀን ፈልገን ያልቻልነውን ልጆቻችን ትከሻ ላይ ነው መስቀል የለመድነው። አላየህም ስንት እኛን የመሰሉ ልጆች ደጋግመን እንዳፈራን። የዘመን ግብዓት ከሚያመጣው መጠነኛ ለውጥ ውጪ በአባትና በልጅ መካከል ምን ልዩነት አለ? ምንም! ከመቶ ዓመት በፊት የነበረ ስህተት ዛሬም ይደገማል። ሃሳብ እንደ አደራ እቃ ታሽጎ ሳይበረዝ ሳይቆረስ ለልጅ ልጅ ይተላለፋል። የአያቶቻችንን ሃሳብ እንድንቀበለው እንጂ አሻሽለን እንድናሳድገው አልተማርንም። ለውጥ ያደረግንበት እንደሆነ የዘመን መበላሸት ምልክት ተደርጎ ይነገረናል። ጎፈሬውን በፍሪዝ ከቀየርን የስምንተኛው ሺ በር ላይ መድረስ ማሳያ ተደርጎ ይነገረናል።
በተራችን ወላጅ ስንሆን የተሰጠንን ሃሳብ ለልጆቻችን እንሰጣለን። ከፍቅራችን ቀድመው ሃሳባችንን እንሰጣቸዋለን። ልጆቻችን መሆን የሚፈልጉትን ሳይሆን እንዲሆኑ እንደምንፈልገው እንቀርፃቸዋለን። የምኞታችንን ጥብቆ በልጆቻችን ገላ ላይ እንሰፋለን። ብንሰማህ ጥሩ ነበር። ግን ወላጆቻችንን እንጂ እራሳችንንም እንዳንሰማ ተደርገን ነው ያደግነው።
እናም እኛን የሚወልዱ ልጆች እየወለድን በድሮ መንገድ፣ በድሮ አካሄድ ዛሬም እናዘግማለን! አንተ ግን ቀጥለሃል…
“ …they have their own thoughts. You may house their body but not their soul”
ልጆች የራሳቸው ሃሳብ አላቸው? ይሄ ለኟ እንግዳ ነገር ነው እውነት! ልጆች ሃሳብ ይዘራባቸዋል እንጂ የራሳቸው ሃሳብ ያበቅላሉ?… ወላጅ ዘራሽ ሃሳብ ሳይሆን ወፍ ዘራሽ ሃሳብ ይኖራቸዋል እያልክ ነው እንዴ?
አየህ! እኛ ግን ስጋቸውን ብቻ ሳይሆን ነብሳቸውንም የማንነታችን ባሪያ አድርገናል። በየመንደሩ ገብተህ ብታይ ከሰፈሩ ለየት ያለ ሀሳብ የሚያስብ ልጅ አታገኝም። ካለም ሳይዘገይ ተለይቶ እንዳያሰብ ይደረጋል። ከዘገየም “እብድ” ተብሎ ይገፋል። ሳይወድ ቡድኑን ይቀላቀላል። ወይ ወዶ እብደቱን ይቀጥላል። …… የተለያዩ ሰዎች ልዩነት አይገባህም። አሳመረችም አስመሮምም ተመሳሳይ አስተሳሰብ ነው ያላቸው። በቀለ እና በቀለች የፆታ እንጂ የሀሳብ ልዩነት የላቸውም።
(ይቀጥላል)