ማሰብ መቻል ልዩ ፀጋ ነው። ሃሳብን መርጦ መተግበር ደግሞ ሰው በራሱ ላይ የሚያመጣው በረከት ነው። ማንም ለሆዱ የሚስማማውን ምግብ እንደሚመርጠው ሁሉ ለአዕምሮውም የሚመጥን ሃሳብን መመገብ ራስን መጥቀም ነው። ንፁህ ምግብ ሰውን ከበሽታ እንደሚከላከለው ሁሉ ንጹህና መልካም ሃሳብም ሰውን አፍራሽ ተልዕኮ ካለው ተግባር ያቅበዋል። አንድ ሰው ጀግና አሳቢ የሚባለው የተሻለ ሃሳብን መርጦ ለራሱም ለሌላውም የሚተርፍና የሚጠቅም አዲስ ሃሳብ መስራት ሲችል ነው።
“Mind Your Mind” የተባለ መፅሐፍ፡-
‹‹አዕምሮ 24 ሠዓት ቀንና ሌሊት በፈረቃ እንደሚሠራ አምራች ኢንዱስትሪ ሃሳብ የሚያመርት ፋብሪካ ነው። ምርቶቹም ሃሳቦች ናቸው።›› ይለናል።
መፅሐፉ ሲቀጥልም፡-
‹‹እያንዳንዱ ሰው እያሠበ ሃሳቦችን ያመርታል። ይሄም ልክ በሃሳብ ውቅያኖስ ውስጥ እንደምንኖር ዓይነት ነው። በተከታታይ አንድ ሃሳብ እናነሳና ያ ሃሳብ በአዕምሯችን አልፎ ይሄዳል። እንደገናም ሌላ እናስባለን። ይሄም ልክ ዓሣን ከውቅያኖስ አጥምዶ እንደመያዝ ነው። አሁንም መንጠቋችንን እንጥላለን ሌላ ዓሣ እንይዛለን።›› ሲል የማሰብን ተከታታይነትና ዘላለማዊነት ይገልጻል።
ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ማሰቡን ሊያቆም አይችልም። ሰው ሊያደርገው የሚችለው ነገር የሚያስበውን መምረጥ ብቻ ነው። በገዛ ሃሳቡ የታሠረ ብዙ ሰው ባለባት ዓለም ሃሳቦቹን መምረጥ የሚችል ጀግና እና ነፃ አሳቢ ማግኘት ከባድ ነው። ሃሳብ መምረጥ መቻል ነፃነት ነው። የትኛውን ሃሳብ መቀበል እንዳለብንና የትኛውን ሃሳብ መቃወምና አለመቀበል እንደሚኖርብን መወሠን መቻል በራሱ ነፃነት ነው። ነጻነት ግን ያለዕውቀት ከሆነ ዋጋ የለውም። ነፃነቱን ነፃነት የሚያደርገው ስለነፃነቱ ያለን እውቀት ነው። ነፃነት በራሱ ነፃ አይደለምና ገደብና ወሰኑን ማወቅ ነፃነትን በነፃነት ማጣጣም እንዲቻል ያደርጋል። አለበለዚያ እውቀት የሌለው ነፃነት ራሱን የቻለ ባርነት ነው። ምክንያቱም ባልተፍታታ ሃሳብ የሚገመድ ነፃነት እንዝላልነትን ይፈጥርና ፈሩን የለቀቀ ጥፋት ያመጣል። ስለዚህ ነፃ አዕምሮ መፍጠር የሚችል ብልህ ሰው ራሱን በሃሳብ ያሳድጋል። በብዝሃ ሃሳብ ደምቆ የተሻለ ሃሳብ ይመርጣል። የአዕምሮ ነፃነቱን ይጠቀምበታል፣ ሃሳብ የመምረጥ ነጻነቱን ይጎናፀፋል። ሃሳብ መምረጫ ወንፊቱን ያበጃል።
አዎ! ሰው ሕሊናውን ወንፊት አድርጎ መስራት መቻል አለበት። ሃሳቡን እያበጠረ ገለባ ሃሳቡን የሚያስወጣበትና ጠቃሚውንና ፍሬ ሃሳቡን የሚያስቀርበት የሕሊና ወንፊት መስራት ይገባዋል። ሃሳብ እንደስንዴ አንክርዳዳድ ካልተጣራ ንጹሁንም ሃሳብ ያበላሻል። የአብዛኞቻችን ሰዎች አዕምሮ ሃሳቦችን ወዲያው ይቀበላል። ነገር ግን የማይፈልጉትን ያስወጣል። ይሄም ሰዎች ለሆነ ሃሳብ አዕምሯቸውን ሲጠቀሙበት ሌሎች ደግሞ ይሄንኑ ሃሳብ ምንም ሳያስቡበት መቅረታቸው እንደምክንያት ይጠቀሳል። ይሄም የሚያሳየው ሰዎች የተለያየ የሃሳብ ማጣሪያ እንዳላቸው ነው። የሕሊና ወንፊቱ መለያየቱ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ተፅዕኖው ግን ቀላል አይደለም። መልካሙ የሕሊና ወንፊት መልካም ሃሳብን አጥርቶ ሲያስቀር፤ ቀዳዳው ወንፊት ደግሞ መልካሙንም ክፉውንም ቀላቅሎ አንድም ሳያጣራ ያፈስሳል። ባለቀዳዳው ወንፊት ምን ማጣራት እንዳለበት ችሎታ ስለሌለው የመጣውን ሃሳብ ሁሉ ያስናግዳል። ለምንም ሃሳብ ምላሽ ይሠጣል። ሃሳቡን የሚገመግምበት ሠዓት የለውም። ምላሽ ለመስጠት ይጣደፋል እንጂ ሃሳቡን በአራት አቅጣጫ ለማየት አይደፍርም።
ብዙዎቻችን ሃሳብ ላይ ብዙ አልተራመድንም! ብዝሃ ሃሳብ አላከበትንም። በማንበብም ሆነ በመወያየት የተለዩ ሃሳቦችን አላስተናገድንም። ያም የሕሊና ወንፊታችን ብቁ እንዳይሆን አድርጎታል። ሕሊና የማያውቀውን ሃሳብ አያጣራም። ማወቅ ቀዳሚ ነገር ነው። ማወቅን በማንበብ፣ በመማርና ከሰዎች ጋር በመወያየት ልንጎናፀፈው የምንችለው ችሎታ ነው። ብዙ የሃሳብ ሊቆችን ሐገራችን አምጣ ብትወልድም የወላድ መካን ሆናለች። የእነሱን ፈለግ ተከትሎ ሃሳብን በሃሳብ ማሳደግና ማሸነፍ የሚችል ትውልድ አልቀረፅንም። የ60ዎቹ ትውልድ በሃሳቡ ተከፋፍሎ መሟገቱ መልካም ጅምር የነበረ ቢሆንም አጨራረሱ ግን ያማረ አልነበረም። በታሪካችን ብዙ ውብ ጅማሬዎቻችን ፍጻሜያቸው ያማረ አይደለም። ያ ትውልድ እርስበርሱ መተላለቁ በሃሳብ አለመብሰሉን ያሳብቃል። በኢዝም ኢዝም.. ርዕዮትዓለም ተከፋፍሎ መከራከሩ መልካም የነበረ ቢሆንም እኔና የእኔን ሃሳብ ካልተከተልክና ካልመሰልክ ግን ትወገዳለህ ማለቱ የሃሳብ ከፍታ ላይ አለመድረሱን ያስመሰክራል። ዛሬም የያ ትውልድ ዳፋ ለዚህኛው ትውልድ ሰበብ ሆኖ ሃሳብን በተሻለ ሃሳብ ከመርታት ይልቅ በጥይት ለማሸነፍ ስንገዳደል እንታያለን። እውነትን ያሉ ሲሞቱ፤ ውሸትን ያሉ ሲኖሩ የምናየው በእኛው ሐገር አይደለምን?
ሃሣብ ላይ ብዙ አልሠራንም። ሃሳብን በሃሳብ ጠረጴዛ ላይ ማታገል አልሆነልንም። በሃሳብ ያን ያህል ከመሬት ከፍ ከሰማይ ዝቅ አላልንም። በሃሳብ ረቅቀንና ርቀን አልተንሳፈፍንም። እንደውም ከነበርንበት ዘመን ወደኋላ ተስፈንጥረን ኋለኞች ሆነናል። አባቶቻችን ካወጡን የሃሳብ ተራራ ተንሸራትተን ተፍገምግመን ወድቀናል። ፊተኞች ኋለኞች፤ ኋለኞች ፊተኞች እንዲል ቅዱስ ቃሉ ጥንት አያቶቻችን በሃሳብ ቀድመው ከፍ ከፍ እንዳላሉ ዛሬ እኛ በሃሳብ ዝቅ ብለን ከሌሎች ሐገራት ጭራ ሆነን አንገት ደፍተናል። አዲስ ሃሳብ መስራት፣ ሃሳቡን ማርቀቅ፣ ሃሳቡን ማጎልመስ፣ ሃሳቡን በተሻለ ሃሳብ መጣል፣ ሃሳቡን በሃሳብ ማድመቅ የሚያስችል ባህል አልፈጠርንም። በሃሳብ መለያየት ጤንነት ከመሆኑ ይልቅ በሽታ ሆኖብን በወረረሽኝ እየጨረሰን ነው። ባህላችን አሳቢን የሚያሸማቅቅ፣ አዲስ ነገር ፈጣሪን አንገት የሚያስደፋ፣ ባለሞያን የሚያሳፍር ሆኖ ከቆየ ዘመናት አልፈውብናል። አዲስ ሃሳብን መርምሮ ለመቀበል ልምድ ስለሌለን አዲስ ሃሳብ የሚያመነጭን ሰው ጠላት እናደርጋለን። ጠላት አድርገንና ነፃነቱን ብናከብርለት ኖሮ እሱም አንድ ነገር ነበር። ምን ያደርጋል ታዲያ! እኛ ግን በሃሳቡ የተለየውን ሰው ጠላት አድርገን አናበቃም፤ ከዚህ ዓለም እንገላግለዋለን። አይ እርግማን!
ለዚህም አይደል ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም በስንኛቸው፡-
‹‹በቁልቁለት ጉዞ ሁሉም ተጣመደ፣
ተያይዞ ነጎደ፤ እየተካካደ፣
ዳገት ላይ ሰው ጠፋ፤ አቀበት ከበደ፣
ሁሉም በሸርታቴ፤ ቁልቁለት ወረደ።›› ….. የሚሉን።
…..
እኔም በመጨረሻ በሃሳብ መፍገምገማችንንና ከተራራው ሃሳብ መውደቃችንን በቁጭት ስንኝ እንዲህ ብዬ ሃሳቤን ልቋጨው አልኩ፡-
……….
ሃሳብም አሳቢም አጣን!
‹‹ሃሳብን በሃሳብ ድባቅ የሚመታ፣
በህሊና ቴስታ፣
ሃሳብ የሚረታ።
ጀግና አሳቢ አጣን፣
የላቀ ሃሳብም አጣን፣
በሃሳብ ገረጣን፣
በአዲስ ሃሳብ ጠኔ…
በድህነት ነጣን።
ሃሳብ የሚደፍር..
አሳቢም፣
አዲስ ሃሳብም፤
አጣን፣
ከሃሳቡ ዓለም ከሰውነት ወጣን፣
ሃሳብን በሰው ነፍስ..
ለውጠን እየቀጣን፣
እርስበርስ እየተቀጣጣን!
የሃሳብን ቂም
በሕይወት ተወጣን፤
ኦ አምላኬ!
ሃሳብን በጥይት!
ከሚደፍር ሰው አውጣን!!››
…..
በሃሳብ እንሸናነፍ የዕለቱ መልዕክት ነው!
ቸር ሃሳብ!
___________________________
ሐሙስ ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.
2 Comments
በጣም የሚገርም ጹሁፍ……በተለይ ይህች ምስኪን ሃገር ለገባችበት ውጥንቅጥ አንድ የሚረባ ነገር የያዘ ድንቅ ጹሁፍ…
ምርጥ መልዕክት፡፡