ሰሞኑን በተወዳጁ ድምጻዊ፣ በጌታቸው ካሳ ላይ የደረሰበትን በሰማሁ ጊዜ አዘንኩ። ጋሽ ጌታቸው በሀዘናችንም፣ በደስታችንም ልናስታውሳቸው የምንችላቸውን ዘፈኖች የተጫወተልን ድምጻዊ ነው። አሁን፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚሰራበት ቤት በመዘጋቱ ኑሮው እንደተመሰቃቀለ ሲነገር፣ አቤት ይሔ ነገር የስንቱን ቤት አንኳኳ አልኩ።
የጌታቸው ካሳ፣ ‹ሀገሬን አትንኳት› የሚለውን ዘፈን ከመውደዴ የተነሳ፣ አንድ ‹ምሳሌ በተሰኘው ኢ-ልቦለዳዊ ልቦለዴ ውስጥ ያለ ገጸ-ባህርዬ ዘፈኑንም ዘፋኙንም በሚከተለው መንገድ እንዲገልጸው አድርጌ ነበር።
….ከሰለሞን ጋር፣ ባዶ ሜዳ መግቢያ በር ላይ የጀበና ቡና አፍልታ እምትሸጥ ሴት አለች፣ እዚያ ነው እንድንገናኝ ቀጠሮ የተጣጣልነው።
ቀድሜው ደረስኩ።
የአጋጣሚ ነገር ሆኖ፣ የጀበና ቡና ቤቱ፣ የጌታቸው ካሣን፣ ‹የብዙኃን እናት፣ መመኪያዬ የምንላት› የተሰኘውን ዘፈን ከፍቶ ጠበቀኝ። ይሄ ዘፈን ብቻቸውን አገር ከሚመስሉኝ ዘፈኖች አንዱ ነው። ዘፈኑን ስሰማ ዐድዋ ተራራ ሄጄና ተዋግቼ ድል የመታሁ፣ ማይጨው ዘምቼም የቆሰልኩና አርበኞቹን የሆንኩ ይመስለኛል። ሙዚቃው ዕድሜዬን ያስረሳኛል። እቴጌ ጣይቱ የጣልያኑን የጦር አዛዥ ሲያመናጭቁትና የውጫሌ የስምምነት ፊርማ ውዝግብ ሲፈጥር፣ ቤተ-መንግሥት ተገኝቼ፣ በነጮቹ ድንፋታ ቁጣዬ ነድዶ፣ ‹ዘራፍ የአባ ዳኘው አሽከር!› ብዬ የሸለልኩና የፎከርኩ ይመስለኛል።
ድምጻዊው ይህን ዘፈን የዘፈነው ለእኔና ለቢጤዎቼ ይመስለኝ ከጀመረ ሰነበተ። ወይስ እኔ ነኝ፣ ድሮ፣ በሌላ ሰው ነፍስ ውስጥ አድሬ፣ ግጥሙንና ዜማውን ደርሼ ለድምጻዊው የሰጠሁት? ታዲያ እንዲህ ካልሆነ፣ ለምንድነው የድምጹ ቅላጼ ነፍሴን ውርር የሚያደርጋት? ለምንድነው፣ ሙዚቃውን የሠሩት የዋልያሥ ባንድ አባላት፣ እንደ ጅረት በሚፈስ የሰው ልጅ ደም መሃል፣ እንደ ማገዶ በተበታተነ አጥንት መሃል፣ ሕይወት በተከፈለበት ደም መሃል መንፈሳቸው እየተመላለሰ ሙዚቃውን የተጫወቱት የሚመስለኝ? ይገርመኛል። ከዐድዋ የድል ዘመን ሌላ እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ እነ ገረሱ ዱኪ፣ እነ ዘርዓይ ደረስ፣ እነ በላይ ዘለቀ አብረውኝ በአርበኝነት የነበሩ፣ እነ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ እነ ተመስገን ገብሬና ሌሎችም…በማይጨው ዘመቻ ጊዜ አብረውኝ ሱዳን፣ ሱማሌና ሮም የተሰደዱ፣ ግዞት የተላኩ… ይመስለኝና፣ አሁን ግን ብቻዬን ቀርቼ፣ በአርበኞች ስም ስለ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ምስክርነት እንድሰጥ የተጋበዝኩ አረጋዊ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል።
በአንድ ዘፈን፣ በድምጻዊው ሾፋሪነት አገር እዞራለሁ፤ በየተራራው አደባለሁ፤ በየሜዳው እፎልላለሁ፤ በየሸለቆው እወሸቃለሁ። ትላንትን ዐያለሁ። እናም ሆዴ ይባባል፤ ዕንባዬ ይመጣል፤ በዚህ ስሜት መሃል ስሆን ደግሞ ማንም እንዲያውከኝ አልፈልግም። የብዙኃን እናት።
ዘርዐይ ደረስ ወንዱ በሮም የቆመላት፣
ጀግኖች በጦር ሜዳ ወድቀው የቀሩላት
እኔም በተጠንቀቅ አለሁሽ የምላት
ጥቁሯ አፍሪካዬን አገሬን አትንኳት።
ብዙውን ጊዜ ስለ እዚህ ዘፈን አስባለሁ። ሁልጊዜ ይህን ዘፈን ስሰማ፣ አንድ ቀን፣ እንዴት እንደ ምወደው ለመናገር መድረክ አግኝቼ በደሰኮርኩ፣ ታሪካዊ ፋይዳውን በመረመርኩ እላለሁ። ሞክሬው ግን ዐላውቅም። እንኳንም አልሞከርኩት። ቃላት ከየት አመጣለሁ? ሃሣብ ከየት አመነጫለሁ? እኔ የወደድኩትን ያህል ሌላው ተደራሲ የተሰማኝን እንዲሰማው የማድረግ ብቃቴስ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? እራሴን እጠይቃለሁ።
በልጅነቴ፣ በሙዚቃ ክፍለ-ጊዜ ይህንን ዘፈን ዘፍኜው፣ ከመቶ 90 አግኝቼበታለሁ። በአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ቆይታዬ በሕይወቴ ከተማሪዎች በልጬ የታየሁበት ነጥብም ይህ ነው። ውጤቱ በሌሎች የትምሕርት ዓይነቶች አልተደገመም።
የተቀዳልኝ ቡና አንድም አልተጎነጨሁለት። አቀርቅሬ ነበር። ዘፈኑ ባይከፈት ኖሮ፣ ተከፍቶም የዐድዋን ድልና የፋሽስትን ገድል ባያስታውሰኝ ኖሮ፣ አገባድጄው በነበረና አስተናጋጇን ሌላ ቡና በጥቅሻ ባዘዝኳት። ግና ስሞት፣ በወዳጆቼና በዘመዶቼ ልቅሶ ከምታጀብ ይልቅ፣ አስከሬኔ አፈር እስኪገባ ምናለ በዚህ ዘፈን በተሸኘሁ ብዬ ስመኝ፣ ፈዝዤ ቀረሁ።
One Comment
የኦሮሞ ፡ህዝብ፡ኢትዮጵያዊ፡ነዉ።100%እስማማለሁ