Tidarfelagi.com

የባል ገበያ – (ክፍል ሶስት)

“ሸሚዝ በከረቫት አይነት ሁሌ ሲጠነቀቁ አትመኛቸው። ወይ እጃቸው እስክትገቢ ነው አልያም የሆነ የሚያካክሱት አልባሌ አመል አለባቸው።” ያለችው ሳቢ ትዝ አለችኝ። …… ሳቢን የማውቃት በሀብቴ ነው።

ሳቢ ፈረንጅ የማግባት ፍቅር እንጂ ከሃገር የመውጣት ፍቅር አልነበረም ዴቲንግ ሳይት ላይ የጣዳት። እንኮኮ አድርጌሽ ልዙር የሚል ፈረንሳዊ ጠበሰች። …… ፊልም ላይ እንደምታየው እና እንደምትመኘው ውሃ ካልጠበስኩልሽ የሚላት ዓይነት ሆነ። …… ወደኢትዮጲያ መጥቶ እንዳያት የጋብቻ ጥያቄ አቀረበላት። ተጋቡ። …… እፍ አሉ። …… ከፍቅራቸው ምጥቀት በአንድ ቆርኪ ውሃ ገላችንን እንታጠብ አሉ። …… ሁሉም ፍፁም መሰለ። ……

እየቆየ ሳቢ አንድ ነገር እየከነከናት መጣ። ባሏ ከርሷ ጋር ባለው ወሲብ ደስተኛ አይደለም። … …… ጭራሽ ባያደርግም ደስተኛ ነው። የምታየው እንደዛ ቢሆንም በአፉ ደስተኛ እንደሆነ ይነግራታል። …… ሁሉን ለሚሆንላት ባሏ ደስታ መሆን ያለመቻሏ ህመም እየሆነባት ሳለ እንደተለመደው በሷ ቆስቋሽነት ካላቡ በኋላ እሷ ወደ መታጠቢያ ቤት ስትገባ እሱ ወደ ላይብረሪው ጋውኑን ደርቦ ሄደ።

…… ሳቢ ግራ ተጋባች። ምን ብትሆንለት ደስተኛ እንደሚሆን በማሰብ ናወዘች። …… ልታናግረው ፈልጋ ወደ ላይብረሪው እግሯን አነሳች። …… በሩን ከፍታ ያየችው መዓት ሲኦል ደርሶ መልስ ሆነባት። …… ሰው ብላ ያገባችው ባል ከሀገሩ ይዟት ከመጣ ውሻው ጋር የሚዳራ እንስሳ ሆኖ አገኘችው…… ራሷን ሳተች። …… ፈረንጅም ውሻም ጠላች። …… ራሷን ለመሆን ብዙ ከፈለች።……
……
……
በስመአብ! አሁን ይሄን ቀፋፊ ታሪክ ለምን አስባለሁ?

አውሮፕላኑ አርፏል። …… ሰወች እየወጡ ነው።……

ከመፍራቴ የተነሳ ባይመጣ ተመኘሁ። ውስጤ የሳልኩትን ስዕል ከሚያፈርስብኝ ቢቀር አለምኩ። …… በቃ ሁሌ እየጠበቅኩት ብኖር…… ለካንስ የሰቀሉትን ተስፋ ከመጨበጥ በላይ የሚያስደስተው ጥበቃው ነው። …… ወይም ጉዞው……

ሻንጣ እየገፋ የሚመጣ አስቀያሚ ሰው ባየው ቁጥር ‘እርሱ ባልሆነ‘ እላለሁ።…… ለአይኔ የሞላውን ‘እሱ ይሆን?‘ ብዬ አፈጣለሁ። … ከማርጀቱ የጎበጠ ነጭ ሲመጣ ባልሆነ ብዬ አይኔን ጨፈንኩ። ሳገኘው እንደምጠመጠምበት ነው የማስበው። …… ይሄ ሰውዬ ቢሆንስ? ሆ! ከአዛውንት ጋር እንጥልጥሎሽ ልጫወት? አይሆንም!

“እኔ አውቅሻለሁ። የቆምሽበት ድረስ ራሴ እመጣለሁ።” ነው ያለኝ ምስሉ የሌለኝን ሰው እንዴት እንደምቀበለው ስጠይቀው።

ስለእውነት ጥበቃዬን አቁሜ መሄድ ሁሉ ቃጥቶኝ ነበር። ……

“ሄላ……ኦህ ማይ ዲር ጋድ! እንዴት ነው የተለወጥሽው?” አለኝ የማውቀው የመሰለኝ ድምፅ

“እንዴ? መውደድ?” ተቃቀፍን። ……

“እንዳላግዝህ ሰው እየጠበቅኩ ነው።” አልኩት ሻንጣዎቹን እያየሁ። በሰላምታ ባጠፋሁት ደቂቃ ያለፈኝ ሰው ካለ ዙሪያ ገባዬን እያየሁ።

“ኢትስ ኦኬ!” አለኝ በእጄ የያዝኩትን ፅጌሬዳ እያየ ፈገግ ብሎ ቀጠለ
“ፍቅረኛሽን መሆን አለበት።”

“እ” አልኩኝ ቶሎ ካጠገቤ እንዲሄድ እየፈለግኩ። እኔ ምን እንደሚመስል ያላወቅኩትን ሰው እንዲያይብኝ አልፈለግኩም። ያውም መውደድ… …

“ፍቅርን ድጋሚ በማግኘትሽ ላንቺ ደስተኛ ነኝ።” አለኝ ሳይንቀሳቀስ

‘ጥለኸኝ ስትሄድ የቀበርከኝ ነበር የመሰለህ?‘ ልለው ነበር ያሰብኩት… … እሱን ማቆያ ስለመሰለኝ

“አመሰግናለሁ።“ ብዬው ፈንጠር ብዬ ቆምኩ። አይኖቼን ስራ ሰጠኋቸው።

“Am here” አለኝ መውደድ ፊቴ ቆሞ።

“መውደድ ሰው እየጠበቅኩ ነው አልኩህ አይደል? ምን እየሆንክ ነው?ለምን አትሄድልኝም።” ጮህኩበት

“እመኚኝ እኔን ነው እየጠበቅሽ ያለሽው።…… ” ሊያሳምነኝ ያወራናቸውን ሁሉ ነገሮች ሲነግረኝ…… አንድ የሆነ የተዛባ ነገር የተፈጠረ መሰለኝ…… ወይም አይኔ አልያም ጆሮዬ ካልሆነም ህልም ነው…… መውደድ? አይሆንም!! አይሆንም!!

የባል ገበያ – (ክፍል አራት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...