Tidarfelagi.com

የባል ገበያ

“እንዴት ተጣበሳችሁ?” ብላ ዛሬም አፋጠጠችኝ። ምን ቀን አቅለብልቦኝ ቋንቋውን የምማረው ለቪዛ መሆኑን እንደነገርኳት እንጃ……

“እስቲ መጀመሪያ አንቺ ንገሪኝ።” ጥያቄዋን ሽሽት እንጂ የሷን የጠበሳ ታሪክ የመስማት ጉጉት ኖሮኝ አልነበረም። እንኳን ተጠይቃ እንዲሁም ምላሷ ሞት አያውቅም።

“እኔማ ዴቲንግ ሳይት ላይ ነው የጠበስኩት። …… እኛ ክላስ ከሰላምና ከኤልሳ በስተቀር ሁሉም በ ‘balshemeta.com‘ ዴቲንግ ሳይት ነው የጠበሱት። …” አፀደ ስታወራ መወራጨቷ እና ቅብጥብጥነቷ ልትበር የምታኮበኩብ ያስመስላታል። …… ያንጨፈረረችው ፀጉሯ ሳይቀር እየፈጠነች ከከንፈሯ ከምታግተለትላቸው ቃላት ጋር ብን ትን ይላል። ቢሆንም ወሬዋ ጆሮና ቀልቤን ጠለፈው…… በዴቲንግ ሳይት የውጪ ሀገር ሰው መጥበስና ወደውጪ ሀገር ለመውጣት መታተር የኔ ብቻ ታሪክ ነበር የመሰለኝ።

“እና ሁላችሁም ቋንቋውን የምትማሩት አግብታችሁ ከሃገር ለመውጣት ነው?”

“አወና! አንቺም እንደዛው አይደል?”

“እ…ሱ…ማ ነው! በተመሳሳይ መንገድ ለተመሳሳይ ዓላማ አንድ ክፍል መገኘታችን ገርሞኝ ነው።” አልኳት

የምፅፍልሽ ዶሮ ፣ ሽንኩርት ፣ ቄጤማ፣ መከለሻ…… ስለሚሸመትበት የበዓል ገበያ አይደለም። በቆዳ ቀለም፣ በእድሜ፣ በዜግነት፣ በኑሮ ደረጃ ፣ በቁመት፣ በውፍረት……… ብቻ ባሻሽ መስፈርት ባል የሚሆን ወንድ ስለሚሸመትበት የገበያ ማዕከል እንጂ…… ለመገበያየት የሚያስፈልግሽ አውድማው ላይ ዘው ብሎ መዝለቅ ብቻ ነው።… …
‘balshemeta.com dating site ‘ ይሰኛል መደብሩ። (ሄዋኔ ይሄን ፅሁፍ አንብበሽ ስትጨርሺ የጎልጉል ፍለጋ ሳጥን ውስጥ ‘ፈልግ‘ን እንደምትጠነቁዪ በመጠርጠር በዚህ ተረክ ውስጥ የተጠቀሰው የሳይቱ ስም ተቀይሯል። …… ሃሃሃሃ)

የዳሌ ቁጥርሽ ሳይቀር ስለራስሽ የጠለቀ ጥያቄ እና የመልስ ሳጥን ይከታተልልሻል። … … ይሄ ብቻ በቂ አይሆንም። ባልሽ እንዲሆን የምትፈልጊውን ሰው ገላው ላይ ያለ የማሪያም ስሞሽ ጭምር በመጥቀስ መስፈርትሽን ታኖሪያለሽ። …… አክለሽ አምስት ቄንጠኛ ፎቶግራፎችን ትለጥፊያለሽ። (በእርግጥ የፎቶው ቄንጥ ግዴታ አይደለም።) አከተመ። ገበያው ውስጥ መሰስ ብለሽ ገብተሻል። …… በተለያየ የዓለማችን ክፍል ካሉ ወንዶች(አብዛኛዎቹ አዛውንቶች እና ለአዛውንትነት የቀረቡ ናቸው) መልዕክቶች ይደርሱሻል። …… የመረጥሽውን ታናግሪያለሽ።

በተመሳሳይ መንገድ አንድ አሜሪካዊ አግብታ የሄደች ወዳጄ (እንደመታደል ሆኖ እኩያዋን ነው ያገኘችው።) በጠቆመችኝ መሰረት በአንድ ያበደ ቀን ሸመታው መሃል ዘመትኩ። …… ከእብድ እስከ ስድ፣ ከአይንአፋር እስከ አደንቁር፣ ከአዋቂ እስከ ልብ አውላቂ፣ ከአስተዋይ እስከ ደም–አፍይ… …… ሳምንታት ከፈጀ አሰልቺ የንግግር ልውውጦሽ በኋላ ከሁለት ሰወች ጋር በቋሚነት ተግባብቼ ማውራት ስለቻልኩ ከሳይቱ ወጥቼ በቫይበር እና በፌስ ቡክ ማውራት ጀመርኩ። አንደኛው ፎቶግራፍ ካለመለጠፉም በላይ እንዳየውም ሆነ እንዲያየኝ ፍላጎት የለውም። የሚፅፍልኝ ቁምነገር ግን ችላ እንድለው አላደረገኝም።

አንደኛው ፈረንሳዊ ጎልማሳ ነው። ከእርሱ ጋር በስካይፒ አወራን። መወሰን ስለነበረብኝ መረጥኩ።…… ከወራት በኋላ ልቀበለው ቦሌ አየር ማረፊያ ተገኘሁ። ……

በአካል የማያውቁትን ሰው ፍቅረኛዬ ብሎ አስቦ ለመቀበል መሄድ የሆነ የማያውቁት ሰው ቀብር ላይ ተገኝቶ ከሬሳው ቀድሜ ጉድጓድ ውስጥ ካልተነጠፍኩ ብሎ ለያዥ ለገናዥ እንደማስቸገር ያለ የቂልነት ዓይነት ስሜት ነበር የፈጠረብኝ። …… ሳየው ምንድነው የማደርገው? አቅፈዋለሁ? እስመዋለሁ? ኸረ ከነጭራሹ በአካል ሳየው ባላውቀውስ? …… በአካል ስንገናኝ ቢያስጠላኝስ? …… እሱስ ካገኘኝ በኋላ ባስጠላው? እኔን ለማግኘት አህጉር ማቋረጡ ቢፀፅተውስ? ………

ክብ ፊቱንና አፍንጫና አይኑን ያጣበበ ሰፊ ጉንጩን እንዳየሁ አወቅኩት። …… ሳይደናገር ሻንጣውን እየገፋ በፈገግታ ወደኔ አቅጣጫ ቀረበ። ሲስቅ ጉንጩ ይንጠለጠልና ሊወድቅ እየመሰለኝ ልደግፍለት መዳፌን ማቅረብ እየቃጣኝ ከብዙ የመተቃቀፍ ሰላምታ በኋላ ሆቴል ደረስን። …… በእርግጥ ከጠበቅኩት ክብደት በላይ አንድ ጎረምሳ ያህል ጨምሮብኛል።(ወደ 30 ኪሎ የሚሆን)

ከፊት ለፊቱ ሲታይ ጥቅጥቅ ብሎ ሙሉ የሚመስለው ፀጉሩ የመሃል አናቱ አመላለጥ የሚቀመጠው በቂጡ ሳይሆን በአናቱ አስመስሎታል።……

አብረን በነበርንባቸው ሳምንታት ለመላመድ ጊዜ አልፈጀብንም። ቁጥብ፣ ስነስርዓታም እና ፈገግታም ነው። ሳቄ ሊያመልጠኝ እየታገለኝ ልለምደው ያልቻልኩት የአልጋ ላይ ባህሪውን ነበር። … …… ጉዳዩን እየከወነ እንደላንቲካ ተኮሳትሮ ሲያፈጥብኝ ከፀበኛው ጋር መንገድ ላይ ድንገት የተፋጠጠ እንጂ ፍቅር እየሰራን አይመስልም። በየመሃሉ የመሳደብ አይነት ምላሱን ብቅ ጥልቅ የማድረግ ልምዱ ሳቄን ያታግለኛል። …… ወደ ሀገሩ ሊመለስ በረራው ሰዓታት ሲቀሩት እንደተለመደው በምላሱ ‘እየተሳደበ‘ ሲተጋ … የጠጣሁት ወይን ተደምሮ ሳቄን መቆጣጠር አቃተኝ። ……… ይሄኔ ተበሳጨ። …… ብስጭት ግን በእንግሊዘኛ አይመስጥም። …… ‘ኤጭ‘ ሳይባል ብስጭት ምኑን ብስጭት ሆነ? ‘ኤድያ‘ ካልገባበት ምኑን ተበሳጨ?

ትጋቱን አቁሞ ታሪክ ይሉት ትንግርት አወጋኝ። …… ከአመታት በፊት በአደጋ የዘር ፍሬውን ላጣ ጓደኛው የቀኝ ፍሬውን መለገሱን እና ከዚያ ወዲህ ለመርካት እንደሚቸገር የነገረኝን ቀልድ ነው ብዬ እንዳላልፍ እንባ ካዡ አይኖቹ የምሩን መሆኑን ተረድቻለሁ።…… የሰማሁትን እርግጠኛ መሆኔን በመጠራጠሬ ነክቼ ‘ይሄንን ነው የለገስከው?‘ ማለት ሊቃጣኝ ስዳዳ… … ገበያ እንደቀረበ ቲማቲም ፍሬዎቹን ለቀም አድርጎ ሰብስቦ

“አየሽ አንዱ ፍሬ የለም። እንቺ ነክተሽ አረጋግጪ! ” አለኝ። ‘ንኪ‘ ያለኝ የሎሚ ፍሬ ይመስል ቀለል አድርጎ

“አንዳች መዓት ይንካህ!” አልኩኝ በሆዴ እየዘገነነኝ…… ለአራት ሳምንታት አብሬው የነበርኩት ሰው ሳይሆን የሆነ የሚሸክክ ፍጡር ሆነብኝ። …… ምኑ እንደዘገነነኝ አላውቅም። ፍሬ— አልባ መሆኑ? አሁንም አሁንም አፍንጫውን እየሞዠቀ ቆለጡን እየነካካ ማለቃቀሱ? ብቻ የሰውነቴ ቆዳ ሽፍ እስኪል ሸከከኝ…… ጥዬው ብሄድ ደስ ባለኝ።

የባል ገበያ (ክፍል ሁለት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...