ከብዙ ዘመናት በሁዋላ ከወዳጄ ምእዝ ጋራ ትናንት በስልክ ተገናኘን፤ ላንድ ሰአት ተኩል ያክል ስናወጋ የተረዳሁት ነገር ፤ጊዜ ብዙ እንዳልቀየረን ነው፤
“የት ልትጋብዛት ነው ያሰብከው?” ሲል ጠየቀኝ፥
“ራቅ ያለ ሰፈር ልወስዳት ነው ያሰበኩት፤ እኛ ሰፈር ያሉት ሬስቶራንቶች ሁሉ ያውቁኛል”
“በሬስቶራንቶች ውስጥ ያሉትን አስተናጋጆች ሁሉ ትጀነጀናለህ እሚባለው ሀሜት እንዴት ታየዋለህ”
“ከውነት የራቀ አይደለም”
“ደግ አደግህ፤ ፈጣን ሎተሪ የሚደርሰው ደጋግሞ በመፋቅ ነው” አለና አበረታታኝ፤
“አለባበሴ ምን ቢሆን ትመክረኛለህ?’ አልሁት፤
“ሮዝ ሸሚዝ ፤ ቀይ ክራባት”
“ሱሪስ?”
“ሱሪ መታጠቅም እንዳትዘነጋ”
“ከድዴ በቀር የቀላ ነገር የለኝም፤ ቀይ ነገር የግድ ነው? “
“በባላንታይን ያለ ቀይ ማክበር ጥምቀትን ያለ ሎሚ እንደማሰብ ነው”
“ወይን ጠጅ ሹራብ አለኝ፤ በላዩ ላይ የቤትናም ባንዲራ ጣል ባደርግበት ይደብራታል?”
“አግኝታ ነው?! አንዲያውም በልክህ ካገኘህ የቼ ጉቢራን ኮፍያም አድርግ! ሴቶች ጀግና ይወዳሉ፤ የጀግና መታሰቢያም ይማርካቸዋል! ትልቅ አናት ያለው ወንድማ ልባቸውን ይነካዋል ፥ትልቅ አናት የትልቅ ልብ ፍንጭ ነው ትል ነበር ዮዲት ጉዲት!
“ሌላ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል? “
“አውራት! ጁንታው፤ ኢኮኖሚው! ኖ ሞር ምናምን ከሚሉና የመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ለጊዜው በሰባት ክንድ ራቅ! መረቅ መረቁን አጫውታት፥ በመሀል በመሀል የሷንም አስተያየት አድምጥ! ታዲያ ጨዋታ አማረልኝ ብለህ ያንድ ሰው ተውኔት እንዳታደርግባት! አደራ በሰማይ አደራ በባህር! እጅ ካላት እጇን ያዝ! በጨዋታ መሀል ‘ ደረቅ ! አስቀያሚ! ሞዛዛ ካለችህ፤ ጨዋታውን ቀጥል፤ እያወራሀት ካዛጋች ወይም “ በተረፈ “ የሚል ቃል ካፏ ከወጣ ቶሎ ብለህ ሂሳብ ከፍለህ ከፊቷ ጥፋ፤ ባስና ባቡር ብታጣ የፍሳሽ መኪናም ቢሆን ተንጣልጥለህ አምልጥ፤ ብቻ፥ ፈጣሪ በተረፈ ከሚለው ቃል ያትርፍህ”
“አሜን!”
“የሚያስጎርር ነገር ካለህ ጎርርላት፤ አየህ ! አባቶቻችን ከገደሉ ገዳይ ነን ብለው ለመደንፋት አያፍሩም ነበር! ብዙ የቀንድ ከብት የነበራቸው አርቢዎች በህዝብ ፊት በወተት የሞላ ገንዳ ውስጥ ይዋኙ ነበር፤ የከብት አንጀት አንገታቸው ላይ እንደ ሀብል የሚጠመጥሙም ዘላኖችም ነበሩ፤ አንጀባ ላባቶች ከሰራ ለልጆች እማይሰራበት ምክንያት የለም’ ራስን ዝቅ ዝቅ ማድረግ ለጽድቅ እንጂ ለጠበሳ አይሆንም”
“ዘሬን ከጠየቀችኝስ ምን ልበላት?”
“ዘር ካለህ ዘርዝርላት! በዘር ስም ሀብት መቋጠር እንጂ ዘር መቁጠር ችግር የለውም” አለና ተፐላሰፈ፤
“እኔ የማውቀው እስከ ቅደመ አያቴ ድረስ ብቻ ነው” አልኩት፥
“ከቅደም አያት ባሻገር እሚቆጥር አለ እንዴ?”
“እንዳለ በቅርቡ ተረድቻለሁ”
“እስኪ አካፍለኝ”
ዝርዝሩን እንደሚከተለው አቀረብኩለት፤
-“እናትና አባት
-አያት
-ሲኤምሲ
-እንጀራ አያት
-ቅድመ አያት
-ድህረ አያት
-ምንጅላት
-ምንጅልናት
-ፍናጅ
-ቅናጅ
-ቅዳጅ
-አናዳጅ
-ማንትቤ
-ማንቴስ
-ሆሞ ኤሬክተስ ( Homo erectus )
ምኡዝ በረጅሙ ተነፈሰና
“በተረፈ”