ድሮ በሃይለስላሴ ዘመን ያዲሳባ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች፤ ባህል ማእከል ውስጥ፤ የስነፅሁፍ ምሽት አዘጋጅተው፤ጃንሆይን በንግድነት ይጠሩዋቸዋል።
ጃንሆይ የተማሪዎችን ጥሪ አክብረው፤ካባቸውን ደርበው ፤ ከች ይላሉ:: ከዛ ኮከብ ተማሪዎች ተራ በተራ እየተነሱ ረጅጅምምም ግጥም ያቀርባሉ።
በጊዜው ስለፍቅር፤ ስለውበት መግጠም እንደ ቅንጦት ይቆጠራል ፤ እነ ሃይሉ ገብረዮሀንስ እልል ያለ ያቁዋም መግለጫ፤ እነ ኢብሳ ጉተማ ደግሞ ቅልጥ ያለ የማነነት ፖለቲካ በግጥም ያቀርባሉ።
አጤ ሀይለስላሴ ፤የተማሪዎችን ግጥም በጥሞና ቢያደምጡ ኖሮ ወይ ገጣሚዎችን ያስረሽናሉ፤ አለያ በግጥሞች ውስጥ የተገለጡ ችግሮችን ሊፈቱ ይችሉ ነበር፤ ባጭሩ የስድሳስድቱ አብዮት አይከሰትም ነበር፤ ግን ጃንሆይ በአካል ልደት አዳራሽ ሆነው፤ በአሳብ ወደ ቤተመንግስታቸው ይመርሻሉ ፤( ትናንት ራስ እምሩ “ እረፍት ያስፈልግሃል” ሲለኝ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? ቅድም ወጥ ቤቶች ምሳ ላይ የበላሁት ፖም፤ መተሀራ ውስጥ የተመረተ ነው ያሉኝ እውነታቸውን ነውን? ወይስ ሊሸውዱኝ ነው? የራስ መኮንን ድልድይ ስር ያለው ውሃ እያደር የሚያንስበት ምክንያት ምንድር ነው? … እያሉ ያስባሉ፤ በዚህ አይነት፤ አንዲት መሰመር ግጥም ሳይሰሙ ወደ ቤተመንግስታቸው ይመለሳሉ) ፤አብዮተኛ ገጣሚዎች በበኩላቸው ፤ጃንሆይን ልክ ልካቸውን ነገርናቸው ብለው እየሸለሉ፤ ወደ ዶርማቸው ይመለሳሉ።
በኛ ጊዜ ዩንበርሲቲ ግጥም ስናነብ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊን አክብረን ጠርተናቸው ነበር፤ እሳቸው ግን ቢዚ ነኝ ብለው በተወካይነት ታጋይ ጌታቸው አሰፋን ላኩልን፤ ያኔ ግጥም የሚሞክሩ ተማሪዎች ከሰኞ እስከ ሃሙስ ድረስ ግጥማቸውን ለባህል ማእከሉ ይልካሉ፤ግጥም ገምጋሚ ኮሚቴ ሚዛን የደፉ ግጥሞችን ለአርብ ንባብ ይመርጣል፤ እድለኞች አምስት ግጥም ልከው አራት ያልፍላቸዋል ፤ አንዳንዶቻችን፤ አምስት ግጥም ልከን፤ አንድ ይመረጥልናል፤ምንም እማይመረጥላቸው እድለቢሶችም ነበሩ፤
አንዳንዴ በሰላም እየተካሄደ ያለ የስነፅሁፍ ምሽት ፤ አንድ ከገጣሚነት ወደ ታዳሚነት እንዲሸጋገር የተፈረደበት ተማሪ “ እኔ የላክሁት ግጥም ከዚች ልጅ ግጥም አንሶ ነው የጣላችሁብኝ ? ወይስ ምርጫው በቁንጅና ነው?”፤ብሎ ሊበጠብጠው ይችላል።
አንድ ቀን አንዱ ተማሪ ፤ሊያነብ ወደ መድረክ ወጥቶ የተናገረው አይረሳኝም:-
“ ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ግጥም አስገብቼ ነበር ፤ ለምን እንደሆነ ባላወቅሁት ነገር ምክንያት ኮሚቴው አንዱን ግጥም አሳልፎ አንዱን ጣለብኝ ፤ ለማንኛውም የወደቀው ግጥም ኮፒ፤ በእጄ ስለሚገኝ ፤ ስእሱን በማንበብ እጀምራለሁ”
ያኔ የምንፅፈው ግጥም ጮርቃ ነበር፤ከካፌ፤ከጥናት፤ከፍሬሽማ ተረብ፤ ከበግ ተራ ፍቅር የዘለለ ሀሳብ አልነበረንም።
በየሳምንቱ አርብ ምሽት፤ለሶስት ሰአት ያክል የትምርት ጣጣችንን ረስተን በግጥም ስንንሳፈፍ እንቆያለን፤ በመጨረሻ ፤ በሚቆንስ የጫማ ጠረን እና በግስላ ሲጃራ ግማት የታፈነውን አዳራሽ ጥለን ለመውጣት ስንተራመስ ፤ የመድረክ መሪው፤
“ አንዴ! ከመሄዳችሁ በፊት…. አንድ ለጥበብ ራሱን የሰጠ ወጣት በመካከላችን ይገኛል፤ ይህ ወጣት ከኮተቤ እዚህ ድረስ በእግሩ መጥቶ ባምስተኛው በር በኩል ፤ ዘበኞችን ሸውዶ ገብቶ ፤ግጥም ላንብብ እያለ ነው፤በጭብጨባ ተቀበሉት፤” ይለናል።
ለመሄድ ያቆበቆበው ተማሪ፤ ርስበራስ ፤እንደ ዛፍና ሀረግ ተዛዝሎ ቆሞ በትግስት ያዳምጣል ፤ የኮተቤውን ልጅ ከግጥሙ ይልቅ ያምስተኛውን በር የሚጠብቁ ዘበኞችን መሸወድ መቻሉን እያደነቅን ወደ ዶርማችን እንበታተናለን።
አሁን ግጥም በጃዝ ይባልና ህዝብ ይጠራል፤ይሁን እንጂ ጉዳዩ በግጥምና በጃዝ የተወሰነ አይደለም ፤የሆነ ቄስ ወይ ሼክ ወይ ፓስተር ስብከት ይሰብካል፤ በማስከተል: መጋቢ ሀዲስ፤ በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ኩምክና ያቀርባሉ፤በማስከተል፤ አቶ ታየ ቦጋለ ፤ነጭ ሱፍ በነጭ ሼሚዝ በነጭ ካልሲና በነጭ ጫማ ለብሰው፤ከጠመኔ የተሰራ ሃውልት መስለው፤ ዲስኩር ያደርጋሉ፡፤ ዲስኩራቸውን “ቀሪውን የተደበቀ ታሪክ መፅሀፌ ውስጥ ታገኙታላችሁ” በማለት ያሳርጋሉ።
ከስምንት ወር በፊት፤ አንዱ የጃዝና ግጥም አዘጋጅ ፤ በምሽቱ ላይ ሰርፕራይዝ አለን፤ የሰርፕራይዙ እንግዳ ስም “አብ” በሚሉ ሁለት ፊደሎች የሚጀምር ነው ብሎ በራዲዮ አስተዋወቀ ፤ የሰርፕራይዙ እንግዳ አብይ አህመድ ይሆናል ብለን የገመትን ሰዎች የዝግጅቱን አዳራሽ አጣበብነው ፤የሰርፕራዙ እንግዳ አብነት አጎናፍር ነው መሆኑን ለመረዳት ሶስት ሰአት መጠበቅ ነበረብን።