Tidarfelagi.com

የሱፍ አበባ ነኝ

የብርሃን ጥገኛ ነኝ… እኔዬ ከብርሃን ውጭ ውበት የላትም… ብርሃን ሳጣ ይጨንቀኛል… ቅጠሎቼ ይጠነዝላሉ… ቅርንጫፎቼ ይኮሰምናሉ… የሱፍ አበባ ነኝ… በሕላዌ ገመድ ለተንጠለጠለችው ኑረት ጨለማና ብርሃን የማይዘለሉ ሃቆች ቢሆኑም እኔ ግን በብርሃን ፍቅር እንደተለከፍኩ አለሁ… ልክፍቱ “..መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ ስላልኩ የሚለቅ አይደለም… ስለት ብገባ፣ ማሕሌት ብቆም፣ ደጀ ሰላሙን በአራት እግር ተንበርክኬ ብሳለም፣ በጸሎት ላቤን ባፈስ፣ በውጣ ውረድ በጠበል ባሳር ወዜ ቢገረጣ…” የሚለቅ ልክፍት አይደለም… የደም ስሬ ውህድ ነው… የሁለንታዬ መሰረት ነው… ከሕላዌ የተቀባሁት ሜሮን ነው።
~~

በኑረት ውስጥ የብርሃን ዕድሜ የጽልመትን እርዝማኔ እንደማይስተካከል አውቃለሁ… ይህ ግን ተስፋ አያስቆርጠኝም… ጸሐይ ስትጠልቅ ስራዋን አቁማ ሳይሆን ቦታ ቀይራ እንደሆነ ይገባኛል… እናም መምጣቷን ተስፋ በማድረግ ሌላ ብርሃን ውስጥ መዝለቅን እመርጣለሁ… የሱፍ አበባ ነኝ…
ዙሪያዬን ጽልመት ሲወርሰው በቀሪው ጭላንጭል ላይ እመሰጣለሁ… አዕምሮዬ የጨለማን ክብደት ሲነግረኝ በፍርሃት አልቆዝምም… ከብርሃን ማጮለቂያ ፉካ ላይ ዓይኖቼን እጥላለሁ እንጂ… ጨለማውን ያየው በአንዳች የብርሃን ቅንጣት አንፃር ቆሞ እንደሆነ ልቤ ትነግረኛለች… አዎን – ጨለማውን ካየበት ቦታ ቆሜ በምትኩ ብርሃኑ ላይ አፈጣለሁ… የሱፍ አበባ ነኝ።
~~

ከብርሃን ጋር እዞራለሁ… ከብርሃን ጋር እሽከረከራለሁ… ዱካው ሲርቀኝ እንኳ በሰጠኝ ወጋገን እንጂ በጥላው እርዝማኔ ላይ አላተኩርም… አንገቴን ከብርሃን አፋፍ አሰጋለሁ… ዓይኖቼን ከብርሃን ወጋገን ላይ አንከራትታለሁ… ጸሐይ ስለጠለቀች አብሮ የሚጠልቅ እምነት የለኝም።
~~

ሁሌም ቢሆን ምርጫ አለ… በጎ አልባ በመሰሉኝ አማራጮች መሃል ሳይቀር ምርጫ አለ… ጸሐይ ስትጠልቅ ጨረቃ ላይ የመመሰጥ ምርጫ አለ… ጨረቃ ስትሰወር ከዋክብቱ ላይ የመታደም ምርጫ አለ… ከዋክብት ሲጠፉ ወጋገኑን ሙጥኝ የማለት ተስፋ አለ… ብርሃን ላይ ተመስጦ ጨለማን ያለማየት ዕድል አለ… “Keep your face to the sunshine and you cannot see the shadows. It’s what the sunflowers do.” ― Helen Keller
~~

ብርሃን የከባቢዬ ውጤት አይደለም – የውስጤ ነጸብራቅ እንጂ… በውጫዊ ሁነት በጎነት ላይ የቆመ አይደለም – በራሴ ነፃ ፍቃድ የሚዳኝ እንጂ… ብርሃኔን ነጠቁኝ ብዬ የማልጮኸው ለዚህ ነው… መስኮቴ ላይ ቆሙ ብዬ የማልነጫነጨው ለዚህ ነው… ስለግል ድክመቴ ዳፋ ሌሎችን የማልሰዋው ለዚህ ነው… የብርሃኑ ማብሪያና ማጥፊያ እጄ ላይ ነው… ብርሃን ውስጤ ነው… ብርሃንነት ተፈጥሮዬ ነው።
~~

ኀቤሁ ለዓይን እንዘ ቅሩባን
ቀራንብተ ኢይኔጽር ዓይን።

ወደ ውጭ ማተኮር የውስጥን መዘንጋት
ልማዱ ሆነና ለሰው ልጅ ሰውነት
ብዙው ነገር ከፋ
ብዙው ነገር ጠፋ።
ይኸው ከፊታችን
ቅንድብ ጎረቤቱ ካጠገቡ ሳለ
ዓይናችን ቅንድቡን ከቶ መች ልብ አለ።
———-
ኤፍሬም ስዩም (ተዋነይ – ገጽ 72)
~~

ስለ ብርሃን ሳዜም የጨለማን ኑረት ክጄ አይደለም… በብርሃን ፍቅር ስወድቅ ጽልመትን ዘንግቼ አይደለም… መሆንን ከመቀበል ጀምሬ እንጂ… የሆነን ስለመሆኑ ብትቀበል ሁነቱ ከሆነው አይዘልም… ወዳለመኖር ያፈገፍጋል እንጂ… የሆነን በለምን ሙግት መጣባት ግና የሁነት ጥልቀቱን ያንረዋል… ጫናውን ያከብደዋል።
~~

ግብሬ የጨለማን ግርዶሽ በብርሃን ፋና ማጥፋት ነው… ጨለማን በጨለማ ላይ ማሰልጠን አይደለም… “Darkness cannot drive out darkness: Only light can do that. Hate cannot drive out hate: Only Love can do that.” Martin Luther King
~~

ወጋገኔ እንዲበዛ ነው ስለጭላንጭሌ አብዝቼ የማወራው… ብርሃኔ እንዲወለድ ነው በሌለበትም የምዘምረው… ስለ ጨለማ ኑረትህ በአደባባይ ባልጮህ ስላላመመኝ እንዳይመስልህ – ስለብርሃንህ ስተጋ ነውና ዝምታዬ የሚጎላብህ… ስለ ግፉዓን ባልናገር ጸጥ ብዬ አይደለም – ስለ በደልህ ካሳ ፍቅርን ስዘራ ድምጽ አጥፍቼ እንጂ… የሱፍ አበባ ነኝ… ጨለማን ለጨለማነቱ ትቼ ከብርሃን ጋር የምጠፋ… ጽልመትን በብርሃን መንሽ ከጽልመት ካባው የማፋታ… ‘ጨለማን በመርገም ፈንታ ቁራጭ ሻማ የምለኩስ’… የብርሃን ልክፍተኛ።
~~

“… ከአድማስ እየራቀ – ምነው ይሄ መንገድ ያባክነኛል
በየት በኩል ብሄድ – ወደረ’ፍት ሃገሬ ቶሎ ያደርሰኛል
ቀስተደመና ነው – የለበስኩት ጥበብ – የያዝኩት ዓርማ
አልጠላም ወድጄ – የነፍሴ ላይ ፋኖስ – እንዳይ ጨልማ…” ቴዲ አፍሮ
~~

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመን ኮሎኝ ውስጥ በአንድ አይሁዳዊ እስረኛ እንደተፃፈ የሚገመት አንድ ግጥም በምድር ቤት ግድግዳ ላይ ተጭሮ ተገኘ… ግጥሙ በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የሰነበተ ሰው የጫረው ግጥም አይመስልም… ዙሪያውን በሚዳሰስ ጽልመት ውስጥ የማቀቀ ሰው የከተበው አይመስልም… 6 ሚሊዮን አይሁድ እንደ ሰም ሲቀልጡ ያየ ሰው ክታብ አይመስልም… ምናልባትም ሊያይ የናፈቀውን ብርሃን ሳያይ ያሸለበ ሰው የተስፋ እንጉርጉሮም ነው… በዙሪያው ሁነት ያልሞተ ብርታቱ ግና ዛሬም ድረስ ለብዙዎች የብርሃን ጸዳል ይረጫል።
~~

“I believe in the sun
even when it is not shining
and I believe in love,
even when there’s no one there.
And I believe in God,
even when he is silent.
I believe through any trial,
there is always a way
But sometimes in this suffering
and hopeless despair
My heart cries for shelter,
to know someone’s there
But a voice rises within me, saying hold on
my child, I’ll give you strength,
I’ll give you hope. Just stay a little while.
I believe in the sun
even when it is not shining
And I believe in love
even when there’s no one there
But I believe in God
even when he is silent
I believe through any trial
there is always a way.
May there someday be sunshine
May there someday be happiness
May there someday be love
May there someday be peace….”
– Unknown Author
~~

“እየፈነጠቀች ባልሆነችበት ጊዜም ቢሆን በፀሐይ መውጣት አምናለሁ፣ ሰው የለኝም በምልበት ጊዜም ቢሆን በፍቅር መኖር አምናለሁ፣ ዝም ባለበት ጊዜም ቢሆን በፈጣሪ አምናለሁ”
~~

ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!

—————-
ሰላም!!
—————-

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...