ለመጀመርያ ጊዜ ሲኒማ የገባሁት አስራንደኛ ክፍል ሳለሁ ይመስለኛል፤ እሁድ ቀን ደብረማርቆስ ውስጥ ነው፤ ብቸኛው ሲኒማ ቤት ተከፍቶ ካስራምስት የማንበልጥ ሰዎች ታድመናል፤ ፊልሙን በቴክኒክ የሚቆጣጠረው ሰውየ የጤና እህል ማለቴ እክል ገጥሞት አልመጣም፤ ስለዚህ፥ የሲኒማ ቤቱ ዘበኛ ጋሽ ይትባረክ ሰውየውን ተክተው ለመስራት ወሰኑ፤ ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ በጊዜው የነበረው የፊልም ፐሮጀክተር ከገጠር ወፍጮ ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ ከዚያ ውስጥ የባውዛ መብራት የሚመስል ነገር እንደዝሀ እየተመዘዘ ይወጣና ግድግዳው ላይ ተአምር ይሰራል፤ ያን ቀን፥ ጋሽ ይባረክ ያለሙያቸው ያልሆነ ነገር ሲነካኩ ምን የመሰለውን የህንድ ፊልም ባፍጢሙ ዘቅዝቀው ማሳየት ጀመሩ፤ እነ አሚታብ ፥እነ ኩማር፥ እግራቸው ወደ ጣራው ተሰቅሎ፥ አናታቸው ወደ ምድር ተዘቅዝቆ ግድግዳው ላይ ውርውር ይላሉ፤ ታዳሚው ‘የዛሬው ፊልም ደሞ ካቀራረቡ ጀምሮ ለየት ያለ ነው” ብሎ በጽሞና መከታተሉን ቀጠለ፤ እኔ የሆነ ችግር እንዳለ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም፤ እልል ያልሁ አይናፋር ስለነበርሁ ደፍሬ ለመናገር አልቻልኩም፤ ቢቸግረኝ አጠገቤ ያለውን አብሮአደጌን አንተነህ ይግዛውን በክርኔ ጉስም አደረኩትና “ እረ ባብማይቱ ይህን ነገር አንድ እንዲሉት ንገራቸው” ብየ አንሾካሾክሁ፤
አንተነህ በታላቅ ደምጽ” ጋሽ ይትባረክ” ብሎ ተጣራ፤
“ ምናባህ ሆንህ?” አሉ ጋሽ ይትባክ፥
“ ትንሽ ድምጽ ይጨምሩበት! ድምጽ ይጎድለዋል” 😀
ቆይቶ ቆይቶ
ዘመን አልፎ ዘመን መጥቶ
የሆነ ሰንበት ላይ አዲሳበባ ዩኒበርሲቲ ውስጥ ወደሚገኘው ሚውዝየም ከባልንጀራየ ጋራ ጎራ አልሁ፤ አስጎብኚው ድብርት የጎበኛቸው ሽማግሌ ናቸው፤ አንዱን ጦርና ጋሻ የተሰቀለበት የግድግዳ መአዘን ተደግፈው ሲያንጎላጁ አገኘናቸው ፤ ከዛ ኮሌታቸውን ይዘን ቀስቀሰናቸው ስናበቃ ጉብኝቱ ተጀመረ፤
“ይሄ የንጉሱ አልጋ ነው” አሉን፤
“የትኛው ንጉስ?”
“እሱን እንግዲህ ርግጠኛ አይደለሁም፤ የወርድና የቁመቱን ሰብሰብ ማለት በማየት የቀዳማዊ ሀይለስላሴ መሆኑን መገመት ይቻላል” ሲሉ መለሱ፤
ከጥቂት ቆይታ በሁዋላ አንዱ ክፍል ውስጥ ደርሰናል፤
“እስቲ ስለዚህ ወንበር ይንገሩን” አላቸው ባለንጀሬ፤
“ይሄ ወንበር!? ይሄ ወንበርማ እንግዲህ እንደምታዩት አራት እግር አለው፤ ሙሉበሙሉ ከንጹህ ቀርቀሀ የተሰራ ነው”
አስጎብኛችን ስለ ወንበሩ በረጃጅም ሳሎች የታጀበ የአርባ ደቂቃ ገለጻ አደረጉልን፥
“ምን ያህል እድሜ አስቆጥሯል ? ” ስላቸው፥
“ከተገዛልኝ ሳምንት አልሞላውም! አስጎብኝቼ ሲደክመኝ አረፍ እልበታለሁ”