Tidarfelagi.com

የሞተን ፈረስ ጥቅም ላይ ስለ ማዋል

ሰሞኑን የምር የሚያሰለጥን ስልጠና ውስጥ ነበር የከረምኩት።
ከትምህርቶቻችን አንዱ ፤ ‹‹የሙት ፈረስ አስተዳደር›› በሚል ርእስ የተቀመጠ ነበር።
አስደማሚው አሰልጣኛችን ይህንን ትምህርት የጀመረው የሚከተለውን በመጠየቅ ነበር።
‹‹ፈረስ እየጋለባችሁ ነው እንበል። በፍጥነት እየጋለባችሁ ሳለ ፣ ፈረሱ ላይ እንዳላችሁ የፈረሱን መሞት ተረዳችሁ። በዚያች ቅፅበት ምን ታደርጋላችሁ?››
ተንጫጫን።
‹‹የለም…እያንዳንዳችሁ መልሳችሁን እጃችሁን እያወጣችሁ ንገሩኝ!›› አለ አሰልጣኛችን።
ከብዙዎቹ መልሶች ጥቂቶቹ እነዚህ ነበሩ።
‹‹ ከሞተማ ምኑን ይጋለባል…!?ጥያቄው ችግር አለበት!››
‹‹ በረሃ ላይ ነኝ…?በረሃ ከሆንኩ አርጄ እበላዋለሁ››
‹‹እንዲነቃ እቀጠቅጠዋለሁ››
‹‹ፀሎት እጀምራለሁ››

‹‹አታወሳስቡት›› አለ መምህራችን። ‹‹ፈረስ እየጋለባችሁ ነው። እየጋለባችሁ እያለ ፈረሱ እንደሞተ አወቃችሁ። መጀመሪያ የምታደርጉት ነገር ምንድነው?››
ሁሉም መልስ የሚለውን እጁን እያወጣ ከተናገረ በኋላ አንዱ ሰልጣኝ ብቻ፤ ‹‹ዘልዬ እወርዳለሁ›› ሲል አሰልጣኛችን ‹‹ቢንጎ! ትክክለኛው መልስ ይሄ ነው…!ከፈረሱ ላይ ዘሎ ወርዶ ራስን ማዳን›› አለ።
‹‹ጠለቅ›› ያለ ምላሽ ይጠብቁ የነበሩና በመልሱ ተራነት የተበሳጩ ጥቂቶች፤ ‹‹ታዲያ ይሄ ምኑ ይደንቃል…?ለምን ቁምነገር ብሎ ጠየቀን…?ምን ለማለት ፈልጎ ነው?›› ብለው መንጫጫት ሲጀምሩ የመምህራችን ‹‹ፓወር ፖይንት ፕረዘንቴሽን›› ተከፈተ።
ወዲያው ፈጠን አለና፤ «የምንጋልበው ፈረስ መሞቱን ከተረዳን ማድረግ ያለብን የመጀመሪያ እና ወሳኝ ነገር ከፈረሱ ላይ መውረድ ነው። ይሄ መቼም ግልፅ እና ቀላል መልስ ይመስላል አይደል!?» አለን።
ብዙዎቻችን ጭንቅላታችንን በአዎንታ ከታች እላይ ነቀነቅን።
አሰልጣኛችን ቀጠለና፤ ‹‹ ምን ያደርጋል! በየእለት ስራችን የምንጋልበው ፈረስ ሲሞት ….መቼም የሞተ ፈረስ ምን እንደሚወክል ተረድታችሁኛል… የምናደርገው ግን እንደዚህ ነው… ˝ አለና የሚከተለውን ነገረን ።
1. ጋላቢውን መቀየር
2. አዲስና ጠንካራ አለንጋ መግዛት
3. “ለዘመናት ስንጋለብ የኖርነው እንዲህ ነው” ብለን ችላ ማለት
4. የሞተውን ፈረስ ሁናቴ የሚያጠና ኮሚቴ ማቋቋም
5. በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ሙት ፈረስ እንዴት እንደሚጋልቡ ልምድ ለመቅሰም ጉብኝት ማዘጋጀት
6. የሙት ፈረስ አገላለብ መስፈርትን ማሻሻል
7. የሞተውን ፈረስ ‹‹ለማዳን›› ግብረ ሃይል ማቋቋም
8. የሞተው ፈረስ እንደሞተ ፈረስ እንዳይቆጠር ‹‹የሙት ፈረስ›› ትርጓሜን መቀየር
9. የሞተ ፈረስ እንዴት እንደሚጋለብ የሚያማክር ‹‹ኮንሰልታንት›› መቅጠር
10. የሞተውን ፈረስ ከሌሎች የሞቱ ፈረሶችን ጋር በማጣመር ፍጥነቱ እንዲጨምር ሁኔታዎችን ማመቻቸት
11. የሞተ ፈረስ በሕይወት ካለ ፈረስ እንደሚረክስ ለማሳመን ወርክሾፕ ማሰናዳት

በሉ እንግዲህ ፤እናንተም ይሄን ዝርዝር ከነጋ ጠባ ኑሯችሁ ጋር አዛምዱ።

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...