Tidarfelagi.com

የምንችለውን ወይስ የሚገባንን?

የሚቻለውን መሥራት የዐቅም ጉዳይ ነው። የሚገባውን መሥራት ግን የሕግና የሞራል ጉዳይ ነው። ኃይልን ለመጠቀም የሚያስችል ትምህርት ለሚማሩ ሰዎች በጥብቅ የሚነገራቸው ነገር ቢኖር የተገቢነት ጉዳይ ነው። ካራቴ፣ ጂዶ፣ ቦክስ፣ ውትድርና፣ ፖሊስነት የተማሩ ሰዎች ኃይልን ለመጠቀም ቅርብ ናቸው። በእጃቸው ማጠናፈር፣ በእግራቸው መዘረር፣ በጉልበታቸው ማርገፍ፣ በመሣሪያቸው ማንጠፍ፣ ይችላሉ። ነገር ግን በባረቀባቸው፣ በፈላባቸውና በነደዳቸው ቁጥር ኃይል እንዳይጠቀሙ የተገቢነትን ጉዳይ እንዲያስቡበት ይመከራሉ፤ ይሠለጥናሉ። ይቻላል ሳይሆን ይገባል ወይ? ብለው እንዲጠይቁ።

አሁን ባለቺው ኢትዮጵያ ‹ይቻላል› እንጂ ‹ይገባል› ተገቢውን ቦታ አላገኘም። ሁሉም የሚችለውን ለማድረግ ነው የተነሣው። ‹ይህንን ማድረግኮ ይቻላል፤ እነ እንትናን መቀስቀስኮ ይቻላል፤ እንዲህ አድርገን ልናሳያቸውኮ እንችላለን፤ እንዲህ ብሎ መከራከርኮ ይቻላል፤ እንዲህ አድርጎ ምላሽ መስጠት ይቻላል፤ እንዲህ ሠርቶ መበሻሸቅ ይቻላል› የሚሉ ነገሮችን ነው የምንሰማው። ባለ ሥልጣኑም፣ ፖለቲከኛውም፣ አክቲቪስቱም፣ ጸሐፊውም፣ ጋዜጠኛውም ምን ማድረግ እንደሚችል እየነገረን ነው። ሁሉም የጉልበቱን ልክ እያሳየን ነው። ‹ይህንን ማድረግ ተገቢ ነው?› ብሎ የሚጠይቅ ግን ብዙም የለም።

ሁላችንም የምንችለውን ብቻ ካደረግን የሚተርፍ አይኖርም። የሚያኗኑረን ተገቢውን ብቻ ለማድረግ ያለን የአእምሮ መለኪያ ነው። ኃይልንና ጉልበትን ከማን አለብኝነት የማቀቢያው መንገድ ‹ተገቢነት› ነው። ይህ ደግሞ ከሕግና ከሞራል አንፃር የሚታይ ነው። ለጊዜው ዐቅም ወይም ሥልጣን ወይም ዕድል የላቸውም ብለን በምናስባቸው ወገኖች ላይ ‹እንችላለን› በሚል ስሜት ብቻ የምናከናውነው ተግባር ሌላ ‹እችላለሁ ባይ› ይፈጥራል። የማሸነፊያው ኃይል ሐሳብ መሆኑ ይቀርና ጉልበት ይሆናል። ጉልበት ማጠራቀም ደግሞ ሐሳብን ከማጠራቀም ይልቅ ቀላል ነው። ሂደታችንም ያረጀን ጉልበታም በአፍለኛ ጉልበታም የመተካት ሂደት ይሆናል። የሰው ልጅ ዛሬ ዛሬ ዛፎችን የማይቆርጠው፣ እንስሳትን የማያድነው፣ በካይ ጋዝ ወደ አየር የማይለቀው ዐቅም አንሶት አይደለም። ይህን ሁሉ ማድረግ ይችላል። ግን አይገባውም።

ማኅበረሰብን በሰላምና በጤና የሚያኑዋኑረው ‹ተገቢነት› ነው። ይህን ነገር መናገር፣ መጻፍ፣ ማሠር፣ መግደል፣ መከልከል፣ መውሰድ፣ መስጠት፣ ተገቢ ነው ወይ? የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው? ያኗኑራል ወይ? በዜጎች ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ምንድን ነው? የሚሉት ጉዳዮች መታየት አለባቸው። ማድረግ የምችለውን ሁሉ ማድረግ፣ መናገር የምንችለውን ሁሉ መናገር፣ መጻፍ የምንችለውን ሁሉ መጻፍ፣ ማባረር የምንለውን ሁሉ ማባረር፣ ማፍረስ የምንችለውን ሁሉ ማፍረስ፣ መገንባት የምንችለውን ሁሉ መገንባት አለብን? ተገቢ ነው?

የሰው ልጅ አካላት በሦስት መልክ ይገለጣሉ። በአንድ በኩል ለሕዝብ ሁሉ የሚገለጡ የአካል ክፍሎች አሉ። በሌላ በኩል ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚገለጡ የአካል ክፍሎች አሉ። ሦስተኛዎቹ ደግሞ ለማንም የማይገለጡ የአካል ክፍሎች ናቸው። በፎቶ ግራፎቻችን ላይ በብዛት የምናገኛቸው ለሕዝብ ሁሉ የሚገለጡትን የአካል ክፍሎቻችንን ነው። እነዚህ የአካል ክፍሎች ብዙ ጊዜ ልብስ አይለብሱም። ቢለብሱም በአደባባይ ልብሳቸው ሊወልቅ የሚችል ነው። ለቅርብ ሰዎቻችን ብቻ የምናሳያቸው የአካል ክፍሎችም አሉን። እነዚህ ብዙ ጊዜ በልብስ ተሸፍነው የሚውሉ ናቸው። እነዚህን ለሰው ሁሉ መግለጥ የጤናም፣ የሞራልም፣ የባሕልም፣ የሥነ ምግባርም ቀውስ ያመጣል። ሦስተኛዎቹ በቆዳችን ተሸፍነው የሚኖሩ የሰውነት ክፍሎች ናቸው። እነዚህን ለማየት የውስጥ አካልን የሚያሳዩ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ። በቀዶ ጥገና ለማየትም የተለየ ሞያና ሥነ ምግባር ይጠይቃሉ። እነዚህ በቆዳ ተሸፍነው የሚኖሩ የሰውነት ክፍሎቻችንን ከፍተን ብንተዋቸው በሰውዬው ላይ አደጋ ይከሠታል። መጨረሻውም ሞት ነው።

የሰው ልጅ ጉዳዮችም እንዲሁ ናቸው። ለሁሉም የሚገለጡ አሉ። ለተመረጡ ብቻ የሚገለጡ አሉ። ለማንም የማይገለጡም አሉ። አሁን በሀገራችን እያየን ያለነው ግን ከዚህ በተለየ ነው። ሁሉንም በአደባባይ የመዘርገፍ አባዜ ውስጥ ወድቀናል። ይህንን የምናደርገው ደግሞ ‹ማድረግ እንችላለን› በሚል ጉልበተኛ ስሜት ነው። ‹ማድረግ ተገቢ ነውን?› በሚል የጠቢብነት መንፈስ አይደለም። ከሕዝብ ሁሉ ጋር የምናደርጋቸው ነገሮች አሉ፤ ከተመረጡ ወገኖች ጋር መነጋገር፣ መከራከር መወያት ያለብን ነገሮችም አሉ። አንዳንድ ነገሮች ግን ስሜታችንን ቢገፋፉትም፣ ውስጣችንን በል በል ቢለንም፣ ጉልበታችን ቢሞግተንም፣ እንኳን ይዘን መኖር ያሉብንም ነገሮች አሉ። ይገለጡ ቢባሉ እንኳን በተገቢው መንገድ ለመያዝ የሚችሉ ሰዎች ያስፈልጉናል። ተገቢነት ይህን ይጠይቃልና።
እስኪ የሀገራችን ኃያላን – የምትችሉትን ሁሉ ማድረግ ተውና የሚገባችሁን ብቻ አድርጉ።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...