Tidarfelagi.com

የማንን ሃሳብ፣ በማን ጭንቅላት እያሰባችሁ ነው?

የማንን ሃሳብ፣ በማን ጭንቅላት እያሰባችሁ ነው?
( ብዙ ጭንቅላቶች ቢኖሩም፣ ብዙ ሀሳበች የሉም)

የሰው ልጅ አሳቢ ፍጡር ነው ቢባልም አብዛኛው ግን አይደለም፡፡ ብዙሃኑ ታስቦ ያለቀ አሳብ እራሱ ላይ ጭኖ የሚሄድ መንገደኛ ነው፡፡ ግቡ መሄዱ እንጂ መድረሱ አይደለም፡፡ “ለምን” የሚባል ጥያቄ ጠላቱ ነው፡፡ በሰዎች ምላስ ጣዕምን ይለካል እንጂ፣ የራሱ ምላስ(የጣዕም ልኬት) የለውም፡፡ ኬክ ጣፋጭ ነው! አዎ ነው!! እንትን ነውር ነው! አዎ ነውር ነው!! የእንትና መፅሐፍ አሪፍ ነው! አዎ በጣም ብዙ ሰው ይወደዋል አሪፍ ነው! እንዲህ ነው ብዙሀኑ-ገደል ማሚቱ!

የያዛችሁትን ሀሳብ ለምን ያዛችሁ ? ብዙሀን ስለተከተሉት? ብዙሃን ስለተከተሉት በቡዝሀን ሀሳብ ብቻ ትክክል ሆኖ የሚያውቅ ሀሳብ አለ፡፡ ትክክል በመሆኑ ብዙዎች የተከተሉት ሀሳብ ይኖር ይሆናል፣ ብዙሃን ስለተከተሉት እውነት የሆነ ሀሳብ ግን በፍፁም! የያዝከውን ሀሳብ ትጠይቃላችሁ? ለምን እንዲህ አመንኩ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ ወይስ ለምን ከሚባል ጥያቄ እስከ አለም ጥግ ትሸሻላችሁ፡፡
ሃሳባችሁ ማን ሰራሽ ነው? ሃይማኖት ሰራሽ? ማህበረሰብ ሰራሽ? ቤተሰብ ሰራሽ? ነው ቅልቅል? ግርር ብሎ ማሰብ ትልልቅ ሰዎችን ፈጥሮ አያውቅም- ባለህበት እርገጥ እንጂ፣ ወደ ፊት! የለውም፡፡ ታላቅነት “ለምን” በምትል ጥያቄ ውስጥ ነው የሚወለደው፡፡ ነፃ መሆን፣ ወይም የብዙሃኑ ቡችላ መሆን የግለሰቡ ምርጫ ነው፡፡ እንደተመረጠልህ መኖር ወይስ እንደመረጥከው መጓዝ፡፡

ትልቁ ጥያቄ- የያዝከውን አቋም የመፈተሸ ድፍረት አለህ ወይ? ለሃይማኖትህ መልስ የምትሰጠው ከሰባኪያን ከለቀምከው ቃል ነው ወይስ የሀይማት መፃሕፍትህን መርምረህ ከደረስክበት? መፀሐፍቱን ስታነብስ አራት ነጥብ እያደረክ ነው የምታነበው ወይስ ጥያቄ ምልክት ታስቀምጣለህ በመሃል? ያለመጠየቅ ሙቀት ይሻልሀል፣ የመጠየቅ ገነት? ሳይጠየቁ የኖሩ አዲስ እውነት አፍጦ በመጣባቸው ጊዜ ያብዳሉ፡፡
“ ያልተመረመረ ህይወት ዋጋ ቢስ ነው” ይላል ጋሽ ሶቅራጥስ፡፡ የኛው ሌሊሳ ደግሞ፣ “ ሕይወትን ሂስ ማድረግ የማይችል ዘመን የፈጠራ መንፈስ አይኖረውም” ይላል በአፍሮ ጋዳ መፅሐፉ፡፡ ዘመን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ሂስ የማያዳረግ ሰውም እንደዛው ነው፡፡ እርግጥ በመመርመር የሚመጡብህ ቅጣቶች አሉ፡፡ አንደኛው የለውጥ ስቃይ ነው፡፡ የቀደመ አስተሳሰብን መለወጥ ለብዙዎች ስቃይ ነው፡፡ አንዳንዱ እዚህ ድረስ መጥቼ እንዴት እመለሳለው ብሎ፣ በጀመረው የስህተት መንገድ መንጎድ ይመርጣል( አዲሱ መንገድ ትክክል እንደሆነ ቢያውቅም፣ የኖረበትን መንገድ መልቀቅ ሞቱ ነው)፣ ሌላኛው በስቃይም ቢሆን አዲሱን እውነት ይቀበላል፡፡
ታዋቂው የክርስቲያን ፈላስፋ የሆነው፣ “ቅዱስ ኦውግስቲን” የመጀመሪያ እምነቱ “Manicheism” የሚባል እና ከክርስትና ጋር ምንም እህል ውሃ የሚያባብል ግንኙነት የሌለው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን እምነቱን ትቶ ወደ ክርስትና ለመለወጥ፣ በብዙ ጭንከት እና ውዝግብ ውስጥ ካለፈ በኋላ በ387 ተጠምቆ ክርስቲያን ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ክርስትናውን የማይለውጠው አቋሙ አደረገው፡፡ ምን አልባት ትንሽ እድሜ ቢሰጠው… በለመደው ውዝግብ እና ጭንቀት ውስጥ አልፎ ሌላ ሃይማት ውስጥ ልናገኘው እንችል ነበር፡፡ ይሄ ሰው ቀድሞ ያመነበትን( ያወቀውን ነገር ከመቀየር ምን ያህል እንደሚከብደው ማሳያ ሊሆነን ይችላል) እናንተ የየትኛው ዘመን ሃሳብ ባሪያዎች ናችሁ? ለየትኛው ሰው? ለየትኛው ድርጅት?….

መንግድህ እያሳየህ ያለው ከሌሎች ባትሪ የሚወጣው ብርሀን ነው ወይስ የራስህ ባትሪ አለህ? ስንት ሃይማት መርምረህ ያንተ ሃይማት ልክ መሆኑን አወክ? ስንት ማህበረሰብ አይተህ አንተ ያለህበት ማህበረሰብ አስተሳሰብ ልክ መሆኑን አመንክ? የስንት ህዝብ ባህል ፈትሸህ፣ የባህልህ ተገዢ ሆንክ? “ባህላችን” ስትል ምን ማለትህ ነው? ሙሉ ለሙሉ እንከን የማይወጣለት ባህል አለኝ ነው የምትል ወይስ ባህሉ “የአንተ ስለሆነ” ብቻ ልክ ነው? የትኛው ባህልስ ነው ልክ? ባህል እንደሚሻሻል እንደሚለወጥ ታምናለህ ወይስ ለአያቶችህ መንፈስ የመታመን እዳ በላይህ ላይ ጭነሃል?

የማን ሆናችኋል? ማን እየሾፈራችሁ፣ ማን እየዘወረን ነው? “ መሬት አየር ሰማይ” የሚለው አዲሱ የሌሊሳ መፅሐፍ ላይ፣ እንዲህ የሚል ገፀባህሪ አለ፤ “ እኔ ነኝ ሀገሬ” እንዲህ ሲል ይቀጥላል ይሄ ገፀባህሪ፤

“………. ሀገር ብቀይር አንጎሌ ማሰብ አያቆምም፣እግሬ መራመድ፣ ጨጓራዬ መፍጨት፣ ልቤ ማፍቀር፤…እኔ ከሌለሁ ሀገር የለም… አዎ! እኔ ነኝ ሀገሬ፡፡ ….”
እናም፣ አንተ ነህ አገርህ፣ አንቺ ነሽ አገርሽ! እራስን ያላከተተ መንገድ ሁሉ…. ፈረሱን ከልክሎ “ያውልህ ሜዳው ጋልብበት” የማለት ያህል ነው፡፡ ምንም ፈረስ በሌለበት፣ ፈረስ ካልጋለብኩ እንደማለት ነው፡፡

ጥያቄው የማንን ጭነት ተሸክማችኋል ነው፡፡ የራሳችሁን ሸክም ነው የሌላውን የተሸከማችሁት? …… ሸክማችሁ የከበደ እናንተ ሸክማችሁን ጣሉ….! የራሳችሁን ሸክም ብቻ ተሸከሙ፡፡ ማንነታችሁንና ዘመናችሁን በማይመጥን ሸክም ትከሻችሁን አታጉብጡ፡፡
“እኛ” ብላችሁ ከማውራታቹህ በፊት፣ “እኔ” ማለትን ልመዱ፡፡ ብዙ ያማሩ ጭንቅላቶችን፣ ብዙ ያማሩ ቡድኖች ውስጥ ገድለን ቀበርን እኮ- ያ አይበቃም?! ብዙ ሃሳብ ያላቸው ጥቂት ሰዎች እንጂ፣ ጥቂት ሃሳብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ምን ይረቡናል? በእኛ ውስጥ የሚጨፈለቀው እኔ ለራሱም ለሌላውም የሚፈይደው የለውም፡፡ እንዲያ ማለት አብዝተህ እራስህን ውደድ አይደለም፣ የሌሎችን ህልውና ጨፍልቅ አይደለም! – የራህን ጫማ አድርግ ማለት ነው፡፡ ያባትህ ጫማ ያንተ አይደለም- ላንተም አይደለም! መንገድ ላይ ከርፈፍ ከርፈፍ እያልክ ከመሄድ ውጪ የሚያተርፍልህ የለም፡፡ አንቺም የእናትሽን ጫማ አውልቀሽ ጣዪ፡፡ ማን እንደሰራው ከማታውቂው፣ ከሚያወለካክፍሽ ጫማም እራስሽን ጠብቂ፡፡

በመጨረሻም፣ እራሳቸውን ችለው የሚያስቡ ጭንቅላቶች ያብዛልን እያልን ወደራሳችን እንሄድ ዘንድ ወደድን……

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...